አማራ ክልል የግል ትምህርት ቤቶችን ክፍያ የሚቆጣጠር መመሪያ ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

Views: 132

የግል የትምህርት ተቋማት ወላጆችን ሳያማክሩ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ የሚከለክል መመሪያ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
መመሪያው በ2011 ከተለያዩ ክልሎች ተሞክሮዎችን በመቀመር የተዘጋጀ ሲሆን በ2012 የትምህርት ዘመን ጸድቋል። በአዲሱ መመሪያ መሠረት የግል ትምህርት ቤቶች ወላጆችን ሳያማክሩ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አይችሉም የተባለ ሲሆን መመሪያው በበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ በግል ባለሃብቶች፣ በሃይማኖት ተቋማት እና በሌሎችም ተቋማት የተመሠረቱ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል።

የክፍያ ጭማሪ ለማድረግ ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ለመነጋጋር ከተጠሩት ወላጆች 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆኑት ሳያጸድቁት የትምህርት ቤቶቹ የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ የማድረግ ሀሳብ ሊፀድቅ እንደማይችል ተገልጿል። እንዲሁም ማንኛውም የግል ትምህርት ቤት ከርዕሰ መምህር በተጨማሪ የወላጆች እና መምህራን ሕብረት (ወመሕ) ሊኖረው ግዴታ ነው፤ በተለይ ወመሕ ትምህርት ቤቱን እና ማኅበረሰቡን የሚያገናኝ ድልድይ በመሆኑ ለትምህርት ቤቶች ቁልፍ እንደሆነ በመመሪያው ተቀምጧል።

በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በቂ የሆነ የትምህርት ግብዓት ሳያሟሉ በደንበኞች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕዝቡን እያማረሩ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን የግል ትምህርት ቤቶች በቂ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ፣ በቂ በሙያው የተመረቁ መምህራን፣ የስፖርት ሜዳ ሊያሟሉ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የተሻሉ ትምህርት ቤቶችን ለማበረታታት፣ ደከም ያሉትን ደግሞ ድጋፍ በማድረግ ወደ ትክክለኛ ደረጃ (ስታንዳርድ) እንዲመጡ ለማድረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ እየሠራ እንደሆነም አስታውቋል። በግል ትምህርት ቤቶች የሚነሳው የመጻሕፍት ችግር በመንግሥት ትምህርት ቤቶችም ያለ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ቢሮው እየሠራ እንደሆነ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com