የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ኪራይ ሥምምነት አካሄደ

0
953

አርብ መጋቢት 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር የኦፕቲካል ፋይበር ኪራይ ሥምምነት ተፈራረመ፡፡

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ እና የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሶውሳ ናቸው፡፡

ሥምምነቱ በመጀመሪያ ምዕራፍ 4097 ኪ.ሜ፣ በኹለተኛው ምዕራፍ 2078 ኪ.ሜ እንዲሁም በሶስተኛው ምዕራፍ 2904 ኪ.ሜ የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ኪራይን ያጠቃልላል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ሥምምነቱ ኹለቱ ተቋማት በጋራ ተባብረው እንዲሰሩ መሠረት የሚጥል ነው፡፡

ተቋሙ ከኃይል ማመንጨት እና ማስተላለፍ ባሻገር የቴሌኮም ዘርፉን ዲጂታል ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

ሥምምነቱ ለሳፋሪኮም እንደ መልካም ጅማሮ የሚታይ ነው ያሉት አሸብር የጋራ ተጠቃሚነትን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡

የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሶውሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ እያሳየች ያለውን አወንታዊ ዕድገት አድንቀው ሥምምነቱ ከተቋሙ ጋር ያለንን በጋራ የመሥራት ፍላጎት የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

ኩባንያቸው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረው፤ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማቅረብም እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመጀመሪያው ምዕራፍ የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ኪራይ በዓመት እስከ 140 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እስከ 15 ሺህ ኪ.ሜ የሚሸፍን የኦፕቲከል ፋይበር መስመር ባለቤት ሲሆን ኢትዮ-ቴሌኮም 8745 ኪ.ሜ በኪራይ እንዲሁም ደግሞ ተቋሙ ለውስጥ የመረጃ ልውውጥ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡
_________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here