ነገረ ኮቪድ-19 እና ባህላዊ መድሃኃኒቱ

Views: 429

ዓለም ዐቀፍ ስጋት እና ወረርሽ የሆነው ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መግባቱ የተነገረው ባሳለፍነው ሳምንት መጋቢት 04/ 2012 ነበር። ይህ ጥንቅር እስከተዘጋጀበት ሰዓት ደረስም፣ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ ደርሷል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር በየቦታው የእጅ መታጠቢያ ተዘጋጅቷል። በርካታ ሱቆች ላይ ቫይረሱ ወደ አገራችን መግባቱንም ተከትሎ አላስፈላጊ እና መሠረት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱም የሰሞኑ ዓበይት ጉዳየች ነበሩ።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ እያስተዋልነው ያለው ነገር፣ ‹‹ቫይረሱ ኢትዮጵያን/ኢትዮጵያውያንን ሊጎዳ አይችልም፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃታል›› የሚሉ መዘናጋቶች መኖራቸውን ነው።

እንደውም ከሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ሲዘዋወሩ ከተመለከትናቸው ነገሮች ውስጥ ሰዎች ቫይረሱን ለመከላከል የንጽኅና መጠበቂ መሣሪያዎችን ከከነማ ፋርማሲዎች ለመግዛት፣ የ20/80 እጣ የወጣባቸው ቤቶች ውል እንዲዋዋሉ የተለጠፈውን የሥም ዝርዝር ለመመልከት፣ በሕዝብ ትራንስፓርት ማመላሻ ባሶች ላይም ረዣዥም ሰልፎች፣ ያውም ተሰላፊዎችና ተጋፊዎች ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ተጠጋግተው ተመልክተናል።

ይህን የተመለከቱ ታዛቢዎችም በውጭ አገር ሰዎች በምን ያህል ርቀት እንደተሰለፉ ፎቶዎችን በማውጣት፣ በኢትዮጵያ ከሚታየው ጋር በማነጻጸር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲንሸራሸር ነበር። ምስልን የተመለከትን ጥቂቶች አይደለንም።

እንደውም ከሰሞኑን በአንደኛው ቀን ከገዳም አባቶች የመጣ መልዕክት ነው፣ በመሆኑም ማር፣ ዝንጅብል፣ ፌጦ፣ ሎሚ፣ ነጭ ሽንኩርትና ሌሎችንም በመቀመም ተጠቀሙ። ይህ ለኢትዮጵያ ቫይረሱን መከላከያ ሁነኛ መድኃኒት ነው ተብሎ ሰዎች በስፋት ሐሳባቸውን ሲያስተጋባም ነበር።

በንጋታውም ሰዎች በታክሲ ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ በቤታቸው እና በአካል መገናኘት ያልቻሉም ተደዋውለው ‹‹እንዴት ነው! ትላንት የተባለውን አደረክ፣ ቀመምክ፤ ተመገብክ?›› ነበር ጥያቄው።

‹‹መድኃኒት ነው›› ስለተባለው ቅመማም በርካቶች አወሩበት፣ ተነጋገሩበትም። አንዳንዱ ከተጠቀመውም በኋላ በቤተሰቡ ማሳበብ የፈለገ እንደ ነበር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ‹‹ማታ እኮ እናቴ አዘጋጅታ ነበር። ሳልፈልግ ነበር እንድመገብ ያደረገችኝ›› ያለም አልጠፋ።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጉዳዩ ላይ እንዲህ ሲል ነበር ሐሳቡን ያሰፈረው ‹‹እባካችሁ በአባቶቻችን ሥም አትቀልዱ። ገዳማውያን አባቶች በጸሎታቸው ምድርና ሰማይ ያስታርቃሉ፣ መዓት ያርቃሉ፣ ምሕረት ያቀርባሉ። ገዳም የገቡት መንፈሳዊ ኃይል ፍለጋ እንጂ ፌጦ፣ ነጭ ሽንኩርትና ኮረሪማ ለመደባለቅ አይደለም። የገዳም አባቶች ለኮሮና መድኃኒት ይሄን ፈጭታችሁ፣ በጥብጣችሁ፣ ቀቅላችሁ ጠጡ ብለዋል የሚለው መልእክት እንኳን ከገዳም፣ ከገዳም ሠፈር አይወጣም።›› ሲል ነበር ምላሽ የሰጠው።

አንዳንዶቹም እንደው ፈጣሪ ሲጠብቀን ተፈጥሯዊ ነገሮች ሆኑ እንጂ እንደው ሌላ ነገር ቢሆን ኖሮ ብዙ ሰዎች መጎዳታቸው አይቀርም ነበር። ስለሆነም ሁል ጊዜ ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል እንጂ ማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀን መልዕክት ተቀብሎ ነገሩን መተግበር ምን የሚሉት ነገር ነው ሲል የጠየቀም አልጠፋም።
‹‹አለመታደል ይሁን ወይም ሌላ፣ ይሄ ነው ለማለት ቢያስቸግርም፤ አፍሪካውያን ባለመሠልጠናችን ሐሰተኛ የሃይማኖት ሰዎች የሚናገሩትን በመቀበል ዝም ብለን እንዳሉን የምንሆን አለን።›› የሚሉት አንድ ሐሳባቸውን በግል ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ግለሰብ አስነበቡ። ይህን ያሉት በኬንያ አንድ ‹የሃይማኖት ሰው› ነው የተባለ ግለሰብ፣ የኮቪድ-19 በሽታ ሁነኛ መድኃኒት ነው ብሎ የንጽህና መጠበቂያ ፈሻስ ሳሙና ለአንዲት ሴት ሲያጠጣት የሚያሳየውን ዜና ተምልክተው ነው።

‹‹የሥልጣኔ አንዱ መገለጫ እኮ እንዴት እና ለምን ብሎ የሚጠይቅ ማኅበረሰብ ሲኖር ነው። እንደው ግን ለምን ወደ ኋላ ቀረን? ለዚህስ ማንን እንጠይቅ?›› በማለት ነበር ሐባቸውን በጥያቄ የቋጩት።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com