-በኢትዮጵያ 102 ቢሊዮን ብር የነዳጅ ዕዳ አለባት
የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈጻጸም እና የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሠራር መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ከነዳጅ ግብይት ጋር በተያያዘ በዋናነት ኹለት መመሪያዎች ተዘጋጅተው ታኀሣሥ 20/2014 በሚኒስትሮች ምክርቤት የጸደቁ ሲሆን፣ መመሪያዎቹ የተዘጋጁት ከአንድ ዓመት በላይ በፈጀ ጥናት መሆኑንና ጥናቱ የተጠናው ከተለያዩ ሰባት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንደሆነ የባለስልጣኑ ኮሚኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ቁምነገረ እውነቱ ተናግረዋል።
ከመመሪያዎቹ አንዱ ለ25 ዓመታት ሲያገለግል የነበረውን የነዳጅ ዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሠራር መመሪያ ለማሻሻል በተደረገ ጥናት፣ በርካታ ችግሮች መኖራቸው የተረጋገጠ በመሆኑ፣ የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሠራር መመሪያ ተሻሽሎ ቀርቧል ነው ያሉት።
ሌላው የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈጻጸም መመሪያ የተዘጋጀውም፣ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ የዓለምን የነዳጅ ዋጋ ተከትሎ በየጊዜው ባለመስተካከሉ ምክንያት ከዓለም፣ ከአፍሪካና ከጎረቤት አገራትም በእጅጉ ባነሰ ዋጋ ሲሸጥ መቆየቱን የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም የኑሮ ውድነቱን በማባባስ በህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳይፈጥር በመስጋት እንደሆነ አመላክተዋል።
የነዳጅ የአገር ውስጥ የመሸጫ ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑ ለኮትሮባንድ አሰራር በር የከፈተ ሲሆን፣ የነዳጅ ህገወጥ ንግድና የነዳጅ ብክነት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አገሪቱ መሸከም ከምትችለው በላይ የዕዳ ጫና ውስጥ እንድተገባ እንዳደረጋትና በነዳጅ ግዥ የተነሳበ የወሩ እስከ 8 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንደምትገባና እስካሁንም 102 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለባት ነው ያሳወቁት።
ስለሆነም አዲሱ መመሪያ ተግባራዊ መሆን የአገሪቱን የዕዳ ጫና ለመቀነስና በኪሳራ እየባከነ ያለው ገንዘብ ለሌሎች የልማት ሰራዎች እንዲውል እንደሚረደርግ ብለዋል።
አክለውም መንግስት ነዳጅን በዝቅተኛ ዋጋ መሸጡ እየጠቀመ ያለው ድሃውን ማህበረሰብ ሳይሆን የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸውን እንደሆነና ድሃው ማህበረሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አሁንም ትልቅ ዋጋ እየከፈለ እንደሆነ መረዳት መቻሉን ገልጸዋል።
ነዳጅ ላይ አንድ ብር ሲጨመር ያለ በቂ ምክንያት ሌሎች ዕቃዎች ላይ እስከ 20 ብር እና ከዚያ በላይ የሚጨምሩ አካላት ብሎም በኢኮኖሚው ላይ የሚሰራው አሻጥር የኑሮ ውድነቱን እያባባሰ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
የእያንዳንዱ ሸቀጥ ዋጋ መጨመር ከነዳጅ ዋጋ ጋር ያለው ቁርኝት፣ ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የሚነዛውን የሀሰት ትርክት ያህል አይደለም ሉት ኃላፊዋ፣ በአሁኑ ወቅት እንኳን የነደጅ ዋጋ ባልጨመረበት ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ አርቲፍሻል የዋጋ ንረት መኖሩን አመላክተዋል።
በዚህ መመሪያ አሰራርም ድሃው ማህበረሰብ ለሚገለገልባቸው የብዙሃን የትራንስፖርት ሰጭ አካላት የታለመ ድጎማ እንደሚደረግላቸውና የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ይደረጋል የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል።
ከዚህ በፊት ሲሰራበት የነበረ የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አስተዳደር ስርዓት እንደነበር ጠቅሰውም፣ ይህም ስርዓት መንግስት የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ ሲቀንስ ለተጠቃሚዎች ዋጋ ከመቀነስ ይልቅ፣ የሚያገኘውን ትርፍ ካዝና ውስጥ በማስቀመጥ፣ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ተጠቃሚዎች ላይ ዋጋ ሳይጨምር ያስቀመጠውን ገንዘብ በመጠቀም ዋጋውን ለማረጋጋት ሲሰራ መቆየቱን ነው የገለጹት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዓለም ገበያ ላይ ያለው የነዳጅ ዋጋ በየቀኑ እየጨመረ በመሆኑና፣ በአሁኑ ሰዓትም የአንድ በርሜል ያልተጣራ ድፍድፍ ነዳጅ እስከ 130 ዶላር እየተሸጠ ባለበት ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ በኢትዮጵያ ሳይጨምር ቆይቷል ነው ያሉት።
ስለሆነም የመመሪያው ዋና ዓላማ በፖሊሲ ያልተደገፈውን ጥቅል የነዳጅ ድጎማ በማስቀረት ወደ የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አስተዳደር ስርዓት እንዲመለስ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነና ተግባራዊ ለማድረግም በአሁኑ ሰዓት የአሰራር መመሪያ ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ አሳውቀዋል።
በሌላ መልኩ ከማደያ በታች ላለው የነዳጅ ግብይት ስርዓት በነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን፣ አዲስ ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱንና በቅርቡ ጸድቆ ተግባራዊ እንደሚሆንም በማብራሪያቸው ገልጸዋል።
ይህ መመሪያ በስራ ላይ ሲውል በተለይም ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ነዳጅ የሚደርስበት ሁኔታ፣ የፈቃድ አሰጣጥ፣ የነዳጅ ዋጋ ግንባታን፣ እንዴት እንደሚያጓጉዙ እንዲሁም እንዴት እንሚሸጡ የሚያብራራ መመሪያ መሆኑም ተገልጿል።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014



