ስለሦስቱ ክብሮች

0
1331

መከባበር ለሠው ልጆች እጅግ አስፈላጊ ከሚባሉ አብሮ ለመኖር ከሚያስፈልጉ ባህሪያት መካከል ከዋናዎቹ ተርታ ይመደባል። ክብር ለብዙ ነገሮች እንደሚሠጥ ኹሉ፣ ለሠው ብቻ ሳይሆን ለፍጥረታትም ሆነ የሠው ልጅ ለሠራቸውና ለመሠረታቸው ሥርዓቶችና ሒደቶች መሠጠት እንዳለበትም ይታመናል። በዚህ ክፉ እየተባለ በሚገለጸው ዘመን፣ ታዋቂዎች በሚዘለፉበት፣ አባቶችና ሽማግሌዎች በሚዋረዱበት፣ እናቶች እንዲቀሉ በሚደረግብት ጊዜ ላይ እንደመሆናችን የመከባበር አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለክብር አስፈላጊነት በመዘርዘር በሦስት ከፍለው የሚያብራሩት ታደሰ ብሩ ኬርስሞ(ዶ/ር) አጠቃላይ ስለክብር አሰጣጥና ጥቅሙ ይህን ጽሑፍ አቅርበዋል።

የግለሰብም ሆነ የማኅበረሰብ ሃብቶች ተዳሳሽ (tangible) እና የማይዳሰሱ (intangible) ተብለው በኹለት ሊከፈሉ ይችላሉ። መሬት፣ ቤት፣ ማሳ፣ ከብቶችና ቁሳቁሶች የተዳሳሽ ሃብቶች ምሳሌዎች ሲሆኑ፣ ዕውቀት፣ ሙያ፣ መልካም ሥነ-ምግባር፣ ከሠዎች ጋር ተግባብቶ መሥራት መቻልና የሥራ ተነሳሽነት ደግሞ ተዳሳሽ ላልሆኑ ሃብቶች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

አንድን ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ሃብታም ወይም ድሃ የሚያደርጉት የተዳሳሽ ሃብቶች መኖር ወይም አለመኖር ብቻ ሳይሆን፣ የማይዳሰሱ ሃብቶች መኖር ወይም አለመኖር ጭምርም ነው። አንድ ሠው መሬትና ቤት ባይኖረው እንኳን ሙያና የሥራ ተነሳሽነት ካለው ሃብታም መሆን ይችላል። ተዳሳሽም ሆነ ተዳሳሽ ያልሆኑ ሃብቶች ተጨማሪ ሃብት ለማፍራት በተግባር ሲውሉ ካፒታል ይሠኛሉ። መሬትን ተጠቅመን ተጨማሪ ሃብት ማፍራት እንደምንችል ኹሉ፣ ሙያችንን ተጠቅመን ተጨማሪ ሃብት ማፍራት እንችላለን።

ኤድዋርድ ዴ ቦኖ “The Happiness Purpose” በተባለች መጽሐፉ ውስጥ “ክብር” (respect) እንደ አንድ ተዳሳሽ ያልሆነ ሃብት ይገልፀዋል። እርግጥ ዴ ቦኖ የቢዝነስ ወይም የኢኮኖሚክስ ተመራማሪ አይደለም። የዴቦኖ የምርምር ትኩረት የአዕምሮ ሥራ ውጤት የሆነውን ማሰብን (thinking) ነው። ውጤታማ ማሰብ የሚኖረው ራሱን የሚያከብር፣ ሌሎች ሠዎች የሚያከብር እና ሥርዓትን የሚያከብር ሠው ሲኖር ነው። ዴቦኖ ሦስት ዓይነት ክብሮች አሉ ይላል። እነዚህም (1) ለራስ የሚሠጥ ክብር፣ (2) ለሌሎች የሚሠጥ ክብር፣ እና (3) ለሥርዓቶች የሚሠጥ ክብር ናቸው።

1. ለራስ የሚሠጥ ክብር
ለራስ የሚሠጥ ክብር ለገዛ ራስ ሠብዕና የሚሰጥን ሞገስ፣ ለራስ የሚሰጥን ዋጋ ይወስናል። “ራስን ማክበር” ለሠው ልጅ በተፈጥሮ የተሠጡ መብቶች እንዲረጋገጡ መጠየቅን ያካትታል። ሠው ሠብዕናውን የሚያረጋግጠው ለራሱ በሚሠጠው ክብር ነው። የማሰብ፣ የመናገር፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የመደራጀት፣ወዘተ. መብቶች አሉኝ ብሎ ለመጠየቅ የገዛ ራስን ማክበር ይጠይቃል።

ለገዛ ራሱ ተገቢውን ክብር የማይሰጥ ሠው በራስ መተማመንን ማዳበር አይችልም። በራስ መተማመን ከሕይወት የምናገኘውን የደስታ መጠን ይወስናል። በራስ መተማመን አዳዲስ ነገሮችንና አዳዲስ መንገዶችን እንድንፈትሽ ብርታት ይሰጠናል፤ መኖራቸውን እንኳን የማናውቃቸውን የተፈጥሮ ስጦታዎቻችንን ለማግኘት ይረዳናል። መልካም አጋጣሚዎችን በሚገባ ለመጠቀም ያስችለናል። ከሠዎች ጋር ተግባቢ ያደርገናል። ስለራሳችን ያለን ግምት ከፍ እንዲል ያደርጋል። ያለንን ዕምቅ ኃይል ተጠቅመን ዓላማዎቻችንን ለማሳካት ያስችለናል። እንዲሁም የሌሎችን ሠዎች ሕይወት ወደ መልካም አቅጣጫ ለመቀየር ይረዳናል።

ለእያንዳንዱ ሠው ከራሱ የቀረበ መምህር የለም። ሠው የገዛ ራሱን ያሰለጥናል፤ የገዛ ራሱን ይፈጥራል። ራሱን የሚያከብር ሠው የሚፈልጋቸውን መረጃዎች ራሱ ይመርጣል፤ በዚህም የራሱን የዕድገት ፈለግ ይቀይሳል። ራስን ማክበር ነገሮችን በገዛ ራስ ዓይኖች መመልከትንም ይጨምራል። የሠዎችን እንዳለ መቀበል ሳይሆን የራስ ዕይታ፣ የራስ ግንዛቤ መኖራቸውን መቀበል ይጠይቃል። ራሱን የሚያከብር ሠው የራሱ ዓለም አለው። “ራስ” ሲባል ግለሰብን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ራሱን የሚያከብር፤ የራሱን ቤተሰብ ያከብራል፤ የራሱን ማኅበረሰብ ያከብራል፤ የራሱን አገር ያከብራል።

2. ለሌሎች የሚሠጥ ክብር
ራሱን የሚያከብር ሠው ሌሎች ሠዎችም ራሳቸውን የማክበር መብት እንዳላቸው ይገነበዛል። እኔ ለራሴ የምፈልገውን ክብር ሌሎችም ለየራሳቸው የሚፈልጉት ነው።
ከዚህ በላይ ደግሞ፣ ሠዎች እንዲያከብሩት የሚፈልግ ሠው እሱ ደግሞ እነሱን ማክበር አለበት። ክብር ሠጥቶ መቀበል ያለበት እንጂ፣ በመቀበል ብቻ የሚቆም አይደለም። ስለሆነም፣ እንዲከበር የሚፈልግ ሠው ሌሎችን ማክበር አለበት። እኛ የራሳችን እውነት እንዳለን ኹሉ ሌሎችም ሠዎች የየራሳቸው እውነት እንዳላቸው መገንዘብ ተገቢ ነው። ሌሎችን ማክበር ማለት ብዙኃነትን መቀበል ማለት ነው።
ሌሎችን ማክበር ማለት የሠውን ልጅ ማክበር ማለት ነው። ከዚያም በላይ እኛ የራሳችንን ሕይወት ለኛ በሚመቸን መንገድ መጓዝ እንደምንፈልግ ኹሉ፣ ሌሎችም ሠዎች የየራሳቸውን ሕይወት እነሱ በመሰላቸው መንገድ መምራት ይፈልጋሉ። ዓለም እኛ ብቻ በምንፈልገው መንገድ መመራት የለባትም። ለመኖር ሌሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ያስፈልጋል።

3. ሥርዓትን ማክበር
ሥርዓትን ማክበር ተቋማትን ማክበር ነው፤ ተቋማትን ማክበር ደግሞ ታማኝነት ነው። ሥርዓትን ማክበር በግል ነፃነትና በተቋማዊ ገደቦች መካከል ያለውን ተቃርኖ ያለዝብልናል። ነፃነታችን እንወዳለን፣ ሆኖም ግን እነዚሁ ነፃነቶቻችን ተቋማዊ ከለላ ከሌላቸው ሊከበሩ አይችሉም። ስለሆነም፣ የጋራ ጥቅም ስንል ከግል ነፃነታችን ቀንሰን ለጋራ ደኅንነት የምንሠጣቸው ነገሮች አሉ። ለልጆቻችን፣ ለቤተሰቦቻችን ስንል አሳልፈን የምንሠጣቸው የግል ፍላጎቶች አሉ። ቤተሰብን እንደ ተቋም ማክበር ታማኝነት ነው። ማኅበረሰብን እንደ ተቋም ማክበር ታማኝነት ነው። አገርን እንደ ተቋም ማክበር ታማኝነት ነው።

ተቋምን በድልድይ ብንመስል በድልድዩ የመሻገርን ነፃነት ተግባራዊ ለማድረግ የድልድዩን ጠንካራነት ማረጋገጥ ተገቢ ነው። ሥርዓትን ወይም ተቋማትን ማክበር ለነፃነት መከበር ወሳኝ ነው። ለመከበር፣ ብቃትን ለማሳደግ ራስን ማብቃት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ራስን ማሠልጠን፣ መለማመድ ይጠይቃል። ሥልጠና ሥርዓት ይሻል። ሥርዓት ሳይኖር ሙያዊ ክህነት አይኖርም። ሥርዓትን ማክበር ራስን ለማክበርም ሆኖ ሌሎችን ሠዎች ለማክበር መሠረት ነው።
የጽሑፉን አቅራቢ ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በዚህ [email protected] ኢሜል አድራሻቸው ማግኘት ትችላላችሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here