ከሰሞኑ 55 አባላትን የያዘው የኤርትራው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት (‘ፐብሊክ ዲፕሎማሲ’) ልዑክ የኢትዮጵያንና ኤርትራን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግና ሕዝባዊ ሥር ለማስያዝ በሚል በኢትዮጵያ አራት ከተሞች መዘዋወሩ ይታወሳል። ይፋዊ ጉብኝቱንና ባሕላዊ ትርዒት ማቅረቡን የካቲት 8/2011 ከባሕር ዳር የጀመረው ልዑኩ በአዳማና ሐዋሳ ተመሳሳይ ኹነትን መፈጸሙም አይዘነጋም። ማጠቃለያውን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ያደረገውና ከ25 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያንን አሳትፏል የተባለው የየካቲት 14/2011 ኹነትም የልዑኩ ጉዞ መዝጊያ ሆኗል።
‘ፐብሊክ ዲፕሎማሲ’ ለምን?
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ትምህርት ቤት ኃላፊና መምህር እንዳለ ንጉሴ “ዲፕሎማሲ የሰውን ልብና አዕምሮ መግዛት ነው” ይላሉ። ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት እንዳለ አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ከሚከተሏቸው ግንባር ቀደም ሰላማዊ ስልቶች አንዱና ተመራጩ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። ዲፕሎማሲ በሦስት መልኮች እንደሚታይ በመጥቀስም ፖለተካዊ ዲፕሎማሲ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ዲፕሎማሲና ፐብሊክ ዲፕሎማሲን ይጠቅሳሉ። የፖለቲካ ዲፕሎማሲው ሰላም ላይ የሚያተኩር እንደሆነና ይህንንም ምዕራፍ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንዳለፉት የሚገልፁት ኃላፊና መምህሩ የምጣኔ ሀብት ዲፕሎማሲው ደግሞ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ትብብሮችን እንደሚመለከት ያስረዳሉ። ተመራጩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲው መሆኑን በመጥቀስ መሰረቱ ሕዝብ ላይ ስለሚሆን አዋጭ እንደሆነ፣ ቀደሞ የነበሩ የዲፕሎማሲ ሒደቶች በድብቅና በውስን ግለሰብና ባለሥልጣናት መካከል የሚደረጉ በመሆኑ ችግር የመፍጠር ዕድላቸው ከፍ ያለ ስለመሆኑ አብራርተዋል። ዲፕሎማሲው የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ ላይ ሲመሰረት ግን ሕዝቡ ስላለውና ስላየው እውነት መስካሪ ስለሚሆን ለፖለቲከኞችና ውስን ግለሰቦች የተሳሳተ ውሳኔ እንዳይጋለጥ አጋዥ ስለመሆኑም ይመሰከርለታል።
እንደእንዳለ ገለፃ ጠላት ናቸው ብለው የሚፈርጁንን አገራት ለማሸነፍም የሚያዋጣን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ነው። በሕዝብ መካከል መተማመንን ለመፍጠር አጋዥ የሆነው ይኸው የዲፕሎማሲ ዓይነት ጠንካራ ሲሆን ፖለቲካውን ማረጋጋት፣ ምጣኔ ሀብቱንም ማሳደግ እንደሚያስችል ያብራራሉ። “ምክንያቱም ሕዝቡን በግንኙነቱ ላይ አሳተፍከው ማለት ለሁሉም ነገር መነሻ ነው” የሚሉት መምህሩ የሕዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሰረት ስለመሆኑ ያምናሉ።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑኩ ጉዞ በኹለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሆነ የሚገልጹት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው ልዑኩ በተገኘባቸው ከተሞች ሁሉ ሕዝቡ በደስታ አቀባበል ሲያደረግላቸው እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ማጠናከር (ፐብሊክ ዲፕሎማሲ) ለሌሎችም የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የምጣኔ ሀብት፣ ፖለቲካና መሰል ትስስሮች መሰረት መሆኑን በመጥቀስም ከሰፊው ሕዝብ የሚጀመር ግንኙነት በጎና አዋጭ ነው ይላሉ።
የልዑኩ አባላት ዕይታ
ከኤርትራው ልዑክ መካከል አንዱ ድምፃዊ እስጢፋኖስ አብርሐም በሐዋሳ የነበረውን ቆይታ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኤጀንሲ ሲናገር የሰላሙ ተጠቃሚ ሕዝቡ ስለሆነ ለሰላም መሥራት ድንበር ሊኖርው እንደማይገባ ጠቅሷል። በፖለቲካዊ ምክንያት የተፈጠረውን ቀውስና ጦርነት ሕዝቡ መስዋዕት ከፍሎበታል የሚለው የኤርትራው ሰው በመስዋዕት የተገኘውን ሰላም የመጠበቁ ዋና ሚናም የሕዝብ እንደሆነ ያምናል። ለዚህም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የበለጠ ዋጋ እንዳለው ያስረዳል።
እስጢፋኖስ ባሕር ዳር በነበረበት ወቅትም ሲናገር የሕዝቡ አቀባበል ደማቅ መሆን የሚጠበቅ እንደሆነ አንስቷል። ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያም በኤርትራም ያለው አንድ ሕዝብ በመሆኑ አቀባበሉ ቀድሞም ደማቅ እንደሚሆን የጠበቀው መሆኑ ነው። እንደድምፃዊው እምነት ሕዝቡ የሰላም ጣዕም የበለጠ እንዲገባውና ሰላሙንም ጠባቂ አንዲሆን በቀጣይ ተመሳሳይ ልዑክ እየመጣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙቱን ማጠንከር ይጠበቃል።
በአፍሪካ ኅብረት የኤርትራ ተወካይ አምባሳደር አርዓያ ደስታ በሐዋሳው የሲዳማ ባሕል አዳራሽ ንግግራቸው “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ አዲስ የመተጋገዝ፣ የመተባበርና የመደጋገፍ ምዕራፍ ስለመከፈቱ አብሳሪ ነው” ያሉ ሲሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማጠናከሩም የቀጣይ ዋስትና ስለመሆኑ አስረድተዋል።
ታዋቂውና አንጋፋው ድምፃዊ በረከት መንግሥተኣብ ልዑኩ ባሕር ዳር በገባ ማግሥት ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገር “በጣም የምናፍቀው ሕዝብ ነበር፣ ለብዙ ጊዜ አብረን ኖረናል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ (በሕይወት ዘመኑ) መድረክ ላይ ወጥቼ የዘፈንኩትም አዲስ አበባ ነበር፣ ከብዙ ኢትዮጵያዊያን እህትና ወንድሞቼ (የኪነ ጥበበ ባለሙያዎች) ጋር አብረን ስንሠራም ነበር፣ ዛሬ ደግሞ ዳግም ለሰላምና አብሮነት መጥተናል” ሲል ተደምጧል። የኪነ ጥበብ ባለሙያው የሕዝቡን ስሜት ማየት እንዳለበትና የሕዝቡ ስሜትም እርቅና ሰላም ስለሆነ ለዚህ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ጥንካሬ መሥራት እንደሚያስፈልግ አክሏል።
ቃል አቀባዩ ነብያት ጌታቸው እንደሚሉት ቡድኑ መቀሌ ያልሔደበት የተለየ ምክንያት የለም።
የከተሞች አመራረጥ
ከዚህ ቀደም በነበረው (ተለምዷዊ) አሠራር አራቱ ዋና ዋና የክልል ከተሞች (ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ፣ አዳማ እና መቀሌ) በሁሉ ነገር ቀዳሚ ሆነው ሲወሰዱ ይስተዋላል። ከገዥው መንግሥት ኢሕአዴግ አራት ብሔራዊ ድርጅቶች መሰረት ጋርም ይሁን በሌላ መንገድ አራቱ ከተሞች ቀድመው የሚነሱና በመንግሥት የተለያዩ ተግባራትም የሚመረጡ አንደሆነ ይታወቃል። ይሁንና የኤርትራው ልዑክ በሦስቱ ክልል ከተሞች ከሔደ በኋላ ማጠቃለያውን አዲስ አበባ ማድረጉና ወደ መቀሌ አለማቅናቱን የሚያነሱ ወገኖች ምንድነው ምክንያቱ ሲሉ ይጠይቃሉ።
አዲስ ማለዳ ይህን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የተለየ ምክንያት ይኖር ይሆን ስትል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርን ጠይቃለች። ቃል አቀባዩ ነብያት ጌታቸው እንደሚሉት ቡድኑ መቀሌ ያልሔደበት የተለየ ምክንያት የለም። የልዑኩ ጉዞ የመጨረሻው አይደለም፣ ይልቁንም ገና መጀመሩ ነው የሚሉት ነብያት ተመሳሳይ ዝግጅቶች በኹለተኛና ቀጣይ ዙሮች በተለያዩ ከተሞች እንደሚካሔዱ ገልጸዋል። የባሕል ቡድኑ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውሮ መሥራት እንደሚፈልግና በመጀመሪው ዙር ግን የተወሰኑ ከተሞች ላይ ደርሶ መመለስን ምርጫው እንዳደረገ አስረድተዋል። ልዑኩ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣም ያሳወቀው ይህንኑ ስለመሆኑ ቃል አቀባዩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከአንድ ወር በኋላ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚያቀና ልዑክ እንደሚኖርና የአገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠነክር እንደሚሠራ አክለዋል።
ከዚህ ቀደም በኤርትራዊያንና በአማራ ሕዝብ መካከል መጠራጠር ስለነበረ የልዑኩ ቀድሞ ባሕር ዳር መሔድ አዎንታዊ ጎኑ ከፍ ያለ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች አሉ።
የዲፕሎማሲና ዓለም ዐቀፍ መምህሩ እንዳለ በበኩላቸው የበዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደሚኖሩ በሚታመንባቸው ባሕር ዳር፣ አዳማና ሐዋሳ መጓዛቸው አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ። ስለሆነም ለመጀመሪያ ዙር ጉብኝት የተመረጡት ቦታዎች ጥሩ ናቸው የሚሉት መምህሩ መቀሌ ቢሔዱም ጥሩ ነው፣ ካለው ሁኔታ አንፃር እንዴት ይስተናገዳሉ የሚለውን አናውቅም፣ ከዚያ ባለፈም የፌደራሉ መንግሥት ልዑኩን ወደዚያ የሚልከው ሙሉ እምነት ሲኖረው ነው፣ የእነሱም [ልዑኩ] ፍላጎት ያስፈልጋል፣ ሲነሱ የሚሔዱበትን ቦታ መርጠውም ይሆናል። ዋናው ነገር ግን መጀመሩ ነው እንጂ ትንንሽ ነገር እያወጣን መሔድ በሽታችን ነው ይላሉ። በሔዱባቸው ክልሎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን አግኝተዋልም ተብሎ እንደሚታሰብ ይገልፃሉ። በቀጣይ ዙሮች ወደቀሩት አካባቢዎች ይሔዳሉ ብለው ታሳቢ የሚያደርጉት እንዳለ ዋናው ጉዳይ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ማጠናከር ስለሆነ የትኛውም ቦታ ቢሔዱ ለሁሉም ወገን ጠቃሚ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። ሕዝብን አሸንፎ የሚኖር መሪ ስለማይኖር ሁሌም የሕዝቡ ፍላጎት እንደሚያሸንፍ በመጥቀስም ወደፊት የበለጠ ወደ ተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሱ ትስስሩ እንደሚጠነክር ተስፋ አላቸው።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የኹለቱ አገራት ድንበር ሲከፈት ኹለቱ ሕዝቦች በጎንደር፣ ትግራይና አፋር በኩል ቀድመው ተገናኝተዋል ተብሎም እንደሚታሰብ በመጥቀስ በአንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ ላይ ካልተካሔደ ማለት እንደማይቻል ይመክራሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባጋጠሙ ስጋቶች ነገሮችን እየመነዘሩ ከማየት ይልቅ የትም ሲሔዱ ጥቅሙ ለአገር ነው በሚል እሳቤ ቢወሰድ መልካም መሆኑን በመግለፅም ዲፕሎማሲ ቅንነትንና በጥሩ ማየትን ይጠይቃል ይላሉ። ልዑኩ የመጣው ለአንድ ክልል ሳይሆን ለአገር ጥቅም በሚል በመሆኑ አገራዊ ስዕሉንና ጥቅሙን መመልከቱ እንደሚበጅም ያነሳሉ። በፌደራሉ መንግስሥትና በክልሎች መካከል ያለው ቅራኔና ስጋት ከውጭ ጉዳይ ግንኙነቱ ጋር ይያያዛል ብለውም አያምኑም።
የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊዋ ሊያ ካሳ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት የኹለቱ አገራት የፌደራል መንግሥታት ጉዳይ በመሆኑ ግንኙነቱ በአገር ደረጃ እንደሚመራ ያነሳሉ። የኤርትራው ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማሳደግ መንቀሳቀሱ መልካም ነው የሚልም እምነት አላቸው። እንቅስቃሴው በዚህ ብቻ እንደማይገደብና በቀጣይ ጊዜያት ተመሳሳይ የሕዝብ ለሕዝብ ትውውቅ መርሀ ግብሮች በተቀሩት ከተሞች እየተካሔደ ይበልጥ ትስስሩን ለማጠንከር ይሰራል ብለውም ተስፋ እንደሚያደርጉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011