ጠቅላይ ሚንስትሩ የአገሪቱ የባንክና የፋይናንስ ዘርፍ ህጎች እንዲሻሻሉ መመሪያ መስጠታቸው ተገለፀ

0
678

ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያን የባንክ እና ፋይናንስ ዘርፍን የሚያስተዳድሩ ህጎች ተመልሰው ታይተው እንዲከለሱ እና ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መመሪያ መሰጠቱ ተገለፀ።

ዋዜማ ሬዲዮ ከምንጮቼ ሰማሁ ስትል የዘገበችው ዘገባ እንደሚያመላክተው፣ መመሪያው ከተሰጠ ጥቂት ሳምንታት ያለፉ ሲሆን፤ ብሄራዊ ባንክ እየተለወጡ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ማስተካከያዎች እንዲያደርግና ሀሳብም እንዲያቀርብ ይጠበቃል።

ማሻሻያ ለማድረግ ምክንያት ስለሆኑት ጉዳዮች የዘርፉ ባለሙያዎች እንደተናገሩት የቴሌኮምና ዲጅታል ኩባንያዎች ወደ ፋይናንስ ዘርፉ መቀላቀል በመጀመራቸው ነባሩን ህግ ከአዳዲሶቹ ፍላጎቶች ጋር ማዋደድ በማስፈለጉ ነው።

ኢትዮ ቴሌ ኮም የጀመረው የቴሌ ብር አገልግሎትን ተከትሎ የአገሪቱን የቴሌ ኮም ኢንዱስትሪ የሚቀላቀሉ ኩባንያዎች በተንቀሳቃሽ ስልክ ገንዘብን የማስተላለፍ አገልግሎት ላይ የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል።

ሚያዝያ ወር ላይ አገልግሎቱን የሚጀምረው ሳፋሪ ኮም በተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን ለመስጠት ከመንግስት ፍቃድን እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ነው።

ሆኖም ገንዘብ ማዘዋወር የመሰሉ ሥራዎች ባንክ ነክ በመሆናቸውና ይህ አይነቱ ሥራ ደግሞ ለውጭ ኩባንያዎች የተፈቀደ ባለመሆኑ ግልጽ የሆነ አሰራር በህግ እንዲቀመጥ ያለመ ማሻሻያ ይጠበቃል ተብሏል።

የፋይናንስ ዘርፍን በተመለከተ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ህግም ለውጭ ኩባንያዎች አሁንም ዝግ ያደረገ ነው። ነገር ግን የውጪ ኩባንያዎች በምን አግባብ በፋይናንስ ዘርፉ ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ ወይም እንደማይችሉ የተብራራ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አንዱ ለብሄራዊ ባንክ የተሰጠ የቤት ሥራ ነው።

በቅርቡ የጸደቀው የካፒታል ገበያ አዋጅ በኢንቨስትመንት ባንክና ተያያዥ ሥራዎች ላይ የመሰማራትን እድል ለውጭ ገበያ ክፍት አድርጓል። ይህም ከአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ህግ ጋር የሚናበብበት መንገድም ከማሻሻያው ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መንግስት የውጭ ምንዛሬ ስለሚያስፈልገው የባንክ ሴክተሩን ለውጭ ኩባንያ መክፈቱ እንደማይቀር ፣ ይህም በፖሊሲ አማራጭ እየታየ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

ይሁንና የፋይናንስ ዘርፉን በቅርብ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ለውጪ ኩባን ያዎች ለመክፈት መንግስት ዝግጁ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች የሉም።
እንደባለሙያዎች አስተያየት መንግስት ባረቀቀው የ10 ዓመት የፋይናንስ ዘርፍ ፍኖተ ካርታ ውስጥ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ለመክፈት አስቀምጦት ከነበረው ጊዜ አስቀድሞ እውን ሊያደርገው ይችላል ተብሏ።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4na

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here