ሱማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ 1.1 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸው ተገለጸ

0
772

በክልሉ እስካሁን የዘነበ ዝናብ ባለመኖሩ ከፍተኛ የሆነ የቤት እንስሳት ሞት መኖሩን የሱማሌ ብሔራዊ ክልል አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን ኃላፊ በሽር አረብ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም፣ እስካሁንም አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት ማለቃቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ የድርቁ ሁኔታ ምንም ዓይነት መሻሻል እያሳየ አይደለም ብለዋል።

ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ የሞቱት እንሰሳት 57 ሺሕ 731 ግመሎች፣ 328 ሺሕ 447 በጎች፣ 655 ሺሕ 951 ፍየሎች፣ እንዲሁም ከ37 ሺሕ በላይ አህዮች፣ በጥቅሉ ከአንድ ሚሊዮን 121 ሺሕ 762 በላይ የቤት እንስሳት መሆናቸውን ኃላፊው አብራርተዋል። በበረሃማ አካባቢዎች መረጃ ያልሰጡ አርብቶ አደሮች በመኖራቸው የሞቱት የቤት እንስሳት ቁጥር ከዚህም የላቀ እንደሚሆን ነው ያብራሩት።

በተጨማሪም፣ በአካባቢው ያሉ ትናንሽ የውኃ ምንጮችና የውኃ ጉድጓዶች ሳይቀር በመድረቃቸው፣ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለመጠጥ ውኃ ችግር መጋለጡን ገልጸዋል። ሆኖም ችግሩን ለማቃለል ውኃ በቦቴ እየቀረበ መሆኑን ነው ያነሱት።

ከ41 ሺሕ በላይ አባወራዎች ወይም ከ244 ሺሕ 242 ያላነሱ ዜጎችም፣ ዝናብ ቢዘንብና ድርቁ ቢጠፋ ወደ ነበሩበት እንዳይመለሱ ሆነው ተፈናቅለው በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው ይገኛሉም ነው ያሉት። ይህም የሆነው አርብቶ አደር በመሆናቸው እና አሁን ላይ ኹሉም የቤት እንስሳዎቻቸው በማለቃቸው ለመመለስ የሚያስችል ምንም ነገር ስለሌላቸው እንደሆነ አብራርተዋል።

የድርቁ ሁኔታ ሲሻሻል ወደ ቀያቸው መመለስ የሚችሉት ደግሞ ለከብቶቻቸው መኖ መግዛት የሚችሉና የቤት እንስሶቻቸውን ከቦታ ቦታ በመኪና ማንቀሳቀስ የሚችሉ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መሄዳቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች ሳይቀር አቋርጠው የገቡ ዜጎች መኖራቸውን ነው የጠቆሙት።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ3.6 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ላይ የምግብ ዕጥረት ተከስቷል ያሉት ኃላፊው፣ ማዳረስ የተቻለው ግን በ87 ወረዳዎች ለሚገኙ አንድ ሚሊዮን 47 ሺሕ 537 ሰዎች መሆኑን አንስተዋል።
ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚቀርብ ያን ያህል ድጋፍ የለም ካሉ በኋላም፣ ያለው ድጋፍ የተደረገው በመንግሥት አቅም መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የተከሰተው ድርቅ አሁን ላይ በዐስር ዞኖች እና ከ87 ወረዳዎች በላይ፣ እንዲሁም በአንድ ሺሕ 975 ቀበሌዎች በላይ የተከሰተ መሆኑና፣ በተለይም በዘጠኙ ዞኖች ከፍተኛ የውኃ ዕጥረት መኖሩንም አመላክተዋል።
85 በመቶ የክልሉ ማኅበረሰብ የዕለት ምግቡንና ሌላ ወጪውን የሚሸፍነው ከቤት እንስሳት በሚያገኘው ገቢ በመሆኑም፣ ድርቁ በርካታ እንስሳትን በመግደሉና ዋጋ እንዳያወጡ በማድረጉ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ቀውስ መፈጠሩ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ እስካሁን ምንም መሻሻል አለማሳየቱ እና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በድርቁ የተነሳ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ከ300 ሺሕ በላይ ከብቶች ማለቃቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here