ከክርስቶስ ልደት በፊት በግብፅ ሥልጣኔ ዘመን መኖሪያን በጨርቃ ጨርቅ እና በእንስሳት ቆዳዎች በማሸብረቅ የጀመረው ሕንፃን የማስዋብ ጥበብ ከዘመን ጋር እየዘመነ አሁን ላይ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ላይ ደርሷል። ሕንፃን የማስዋብ ጥበብ በሁሉም ቦታ ለአንድ ዓይነት አላማ ይዋል እንጂ ከቦታ ቦታ የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ መሠረት አድርጎ የማስዋቡ ሒደት እንደየአካባቢው ይለያያል። ሕንፃን የማስዋብ ጥበብ የሰዎችን ስሜት ማጥናት፣ ሰዎች ከአካባቢው ጋር ያላቸውን መስተጋብር የማየት፣ የሥራ ቦታዎችም ከሆኑ የሚሠሩትን ሥራ በውበት በመግለፅ መኖሪያንም ሆነ ሕንፃን ወይም የሥራ ቦታን ማስዋብ ነው። ይህም በሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ጥሩ ስሜትን የሚፈጥርና ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ።
ውልደቱን ከወደ ፈርኦኖች ምድር ያደረገው የሕንፃን ውስጣዊ ክፍል የማስዋብ ጥበብ ታዲያ በአገራችን ኢትዮጵያም ቀላል የሚይባል ዕድሜ እንዳላስቆጠረ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ከእድሜ ጠገብ የእምነት ተቋማት ሕንፃዎች ውስጣዊ እና ውጫዊ አካል ለመረዳት እንደሚቻለው የቀደምት ኢትዮጵያዊያን ሕንፃን የማስዋብ ጥበብ አሻራዎችን መመልከት ይቻላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በትምህርት የታገዘ እና በዘመናዊ መንገድ ሕንፃዎችንና የሥራ ቦታዎችን የማስዋብ ሒደት እድገትን እያሳየና የሰዎችንም ቀልብ እየሳበ ይገኛል። ይህንም ተከትሎ አሁን ላይ ቁጥራቸው ላቅ ያሉ በዘመናዊ መንገድ ሕንፃን የሚያስውቡ ድርጅቶች ወደ ገበያ እየገቡ እንዳሉ በዚህ ዘመን ላይ ያሉትን ሕንፃዎችና የሥራ ቦታዎች መመልከት በቂ ማስረጃ ነው። በዘርፉ ግንባር ቀደም ከሆኑትና አመርቂ ሥራን እያስመዘገቡ ካሉ ድርጅቶች መካከል “ቤት ለእምቦሳ” በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። በፈረንጆች 2011 በወጣት የዘርፉ ባለሙያዎች የተቋቋመው ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መኖሪያን፣ ሕንፃዎችን፣ የሥራ ቦታዎችን ውስጣዊ ክፍል እንዴት ማስዋብ እንደሚቻል የቴሌቪዥን መርሐ ግብር በመጀመር ሙያዊ ምክርን ለተመልካች ያደረሰ ድርጅት ነው።
የቤት ለእምቦሳ የሥነ ህንፃ ባለሙያ የሆኑት ፍቅር አበበ እንደሚሉት የሕንፃ ውስጥ ማሰዋብ በብዛት አገራቸን ውስጥ አልተለመደም። ለዚህ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ይህ የሕንፃ ውሰጥ ማስዋቢያ ትምህርት አገራቸን ውስጥ አለመሰጠቱ እንዲሁም ሁሉም የሕንፃ ውስጥ ማሰዋብ ሥራን በአብዛኛው የሚሠራው ከሌሎች አገሮች ጋር ልምድ ልውውጥ በማድረግ የሚሠራ ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙትም ሆቴሎች፣ ሆስፒታሎች እንዲሁም ካፌ እና ሬስቶራንቶች ናቸው። እነዚም ከሌሎች ለየት በማለት ተመራጭ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያግዛል። ሆኖም በእኛ ድርጅት ዋናው አላማችን ደንበኞቻችን እንዲወዱት የማድረግ ሥራ እስከሆነ ድረስ ሁሉንም ሰው ባማከለ ዋጋ እንሠራለን ይህ ማለት ደግሞ ሁሉም አሠራሮች የተለያየ ዋጋ ቢኖራቸውም ደንበኞቻችን በፈለጉት መንገድ ሠረተን እናስረክባለን በማለት የሥነ ሕንፃ ባለሙያው ስለ ሕንፃ ውስጥ ማስዋብ ያላቸውን አስተያየት ገልፀዋል።
የቤት ለምቦሳ ሕንፃ ማስዋቢያ ድርጅት ደንበኛ የሆነው የዋው በርገር ሥራ አስከያጅ አብዩ መኮነን እንደሚሉት “ለእኛ የካፌያችንን ዲዛይን በተለየ ሁኔታ የሰራልን ቤት ለምቦሳ ነው። ይሁንና ይህን ለማረግ ያነሳሳን ዋነኛው ምክንያታችን ደንበኞቻችን እኛ ጋር ሊጠቀሙ በሚመጡበት ጊዜ ለዓይንናቸው አመቺ እና ማራኪ እንዲሆን በማሰብ ነው” ብለዋል። ሆኖም የሥራ ቦታችንን በዚህ መንገድ የተሸለ በማደረጋችን ተመራጭ እና ተወዳጅ ስላደረገን በዋው በርገር ሥር ከሚገኙ ስምንት ቅርንጫፍዎች ውስጥ አራቱን ዲዛይን ያረጉልን እነሱ ናቸው ሲሉ አብዩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ የመጣውን የሕንፃ ውስጥ ማስዋብ ሥራን ተከትሎ ዛሬ የካቲት 16/ 2011 ኢንደስትሪዉን የሚቀላቀለውን ማኪ የሕንፃ ውስጥ ማስዋብና የሥነ ጥበብ ማዕከልን እናገኛለን።
የማኪ የሕንፃ ውሰጥ ማስዋብና አርት ጋለሪ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ማራኪ ተጠምቀ ስለ አዲሱ ድርጅታቸው ሲያብራሩም የሕንፃ ውስጥ ማስዋብ ሞያችን ሆኖ ሳለ በተጨማሪ በውስጣችን ያለው የአርት ፍቅር ምክንያት በዋነኝነት ይህን ድርጅት ለመክፈት ካነሳሳን ነገሮች አንዱ ሲሆን በአገራችን በሚገነቡ ሕንፃዎች ውስጥ የተለያዩ ችግሮችን በማስተዋል በግልፅ ከሚታዩት ክፍተቶች ውስጥ ስታንዳርድ ባለመጠበቅ የሚፈርሱ የውስጥ ግንባታዎች ባለቤቱን ለኪሳራ ከማጋለጡም አልፎ በአገሪቷም ላይ ከፍተኛ ውድቀት እየስከተለ መምጣቱ፣ የክፍሎችን አከፋፈል ለተገቢው ነገር የሚመች አድርጎ በበቂ ሁኔታ አለመጠቀም እና የብርሃንና የአየር አለመመጣጠን በብዙ ሕንፃዎች ላይ የሚታይ ችግር ሲሆን የመብራት የወለልና የኮርኒስ እንዲሁም የዕቃና ከለር አመራረጥን ታሳቢ አድርገን እነዚን ችግሮች በጥቂቱም ቢሆን ለመፍታት በማሰብ ነው ድረጅታችንን ያቋቋምው ሲሉ ሥራ አስኪያጅዋ ገልፀዋል።
የሕንፃ ውስጥ ማሰዋብ ሲሠራ የውስጥን ገጽታ ከአካባቢውና ከአገሪቱ የአየር ሁኔታ ጋር በማዋሀድ የአካባቢውን አትሞስፌርን መጠበቅ ዋነኛው የሥራ ድርሻ ከመሆኑ ባሻገር በሕንፃ ውስጥ ለጤና ተስማሚ የሚሆኑ አትክልቶችን በማዘጋጀትና በማቅረብ የሕንፃ ውስጥ የአየር ዝውውር ተስማሚ እንዲሆን ከማድረግ አልፎ ጥሩና ምቹ ስፍራ ለማግኘት የሚረዳን ይሆናል። እንዲሁም ከሕንፃ ውስጥ የጀመርነውን ጥሩና ምቹ ስፍራ ከግቢ ውስጥና በአካባቢውም ጤናማና ተስማሚ ቦታ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፆ እንደሚፈጥር በማመናችን የሕንፃ ውስጥ ውጪን በአትክልት ሥራ የተዋበ ለማደረግ እየተዘጋጀን ነው ሲሉ ሥራ አስኪያጅዋ ጨምረው ይናገራሉ።
የድርጅታቸን ዋና ዓላማ በአገራችን ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ፈቺ ተቋም ከመሆን አልፎ በሌሎች አገራት ውስጥ እውቅና የሚያገኝ ድርጅት መፍጠር እና የአገራችንን የጥበብ ውጤት በተለየ ሁኔታ ለማሳደግ ቀደምት የአባባል ዘዴዎችንና ጥበቦችን ወደ ጥበቡ መድረክ ተመልሰው እንዲገቡ እንዲሁም ሰዓሊው በከፍተኛ ደረጃ የጥበቡ ተጠቃሚና ታዋቂ እንዲሆን በማድረግ በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ሀገር ውጪ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ሀገራችንን በከፍተኛ ሁኔታ ማስተዋወቅ ሲሆን ከሌሎቹ የሚለየው የኛ ድርጅት የተለያዩ የስራ ዘርፎችን በአንድላይ በመስራት የሰዎችን ልፋት በመቀነስ ፍላጎትን የሚያሟላ ሲሆን በምንሰራው ሥራ ላይ የተማረ የሰው ኃይል መኖሩ እንዲሁም ተጠቃሚው የሚፈልገውን ነገር መረጦ የመግዛት እና የማማከር አገልግሎት እንዲኖራቸው ዕድል መስጠታች ነው ብለዋል።
የቤት ውስጥ ማስዋብ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ግለሰቦች በግላቸው የሥራ ቦታቸውን ምቹ ለማድረግ በሚስማማ መልኩ እየስዋቡ እንደሆነ እንመለከታል። የብሉ ሙን ሥራ ፈጠራ ድርጅት መሥራች ኢሌኒ ገብረመድህን በቅረቡ አዲስ ለጀመሩት ብሉ ሰፔስ የሥራ ማዕከል በግላቸው የማስዋቡን ሥራ እንደሰሩት ይናገራሉ። ይህም በአሁኑ ሰዓት የማስዋብ ጥበብ በሰዎች ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነትን እያገኘ እንደመጣ መረዳት ይቻላል።
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011