ለወደፊት ትልቅን መመኘትና ማለም ጥፋት አይደለም። የሚቀድመውና ለነገም መሠረት የሚሆነው ግን ዛሬ ነው። የነገ ሕልምም ሆነ ግብ ስኬታማ እንዲሆን እንቅስቃሴ መጀመር ያለበት ዛሬ ነው። ተስፋን አሻግሮ ማየት ባያስኮንንም፣ አሁን እንደ ሲኦል አስፈሪና የከበደ ችግር ውስጥ ለምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ‹ወደ ውጪ አገር ስንዴ መላክ› ትልቅና ሊሳካ የማይችልበት ምክንያት የሌለው ሕልም ቢሆንም፣ ዛሬ ያለውን ፈተና ማለፍ ሊተኮርበት እንደሚገባ ኤርምያስ ሙሉጌታ በጽሑፋቸው ያነሳሉ።
በኤርምያስ ሙሉጌታ
በአፍሪካ ላቅ ሲልም በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው፣ እንዲያው አነሰ ቢባል አድገው ተመንድገው ጭራቸውን ለመያዝ አዳጋች ከሆኑ አገራት መስተካከላቸው የማይቀር ዕድገቶችን ኢትዮጵያ እንደምትጎናጸፍ እየተሣማ ነው፤ ስንሰማም ባጅተናል።
በእርግጥ እኛ የኢሕዴግ ዘመን ሰዎች ለእንደዚህ ዓይነት ቃልኪዳኖች እምብዛም አዲስ እንሆናለን ተብሎ አይታሰብም። እንዲያውም በአንድ ወቅት ግንባሩ ኢሕአዴግ ሰፋፊ ዕቅዶችን ያቅድና (ያው መንግሥትም አልነበር? የመንግሥት ወጉ ነው እና ዕቅድ ያወጣል) የበጀት ዓመቱን ጉዞ ይጀምራል። ኢትዮጵያም ታዲያ በአስተዳዳሪዋ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊው ኢሕአዴግ ዘዋሪነት የተተነበየላትን የበጀት ዓመት ፍጻሜ ለማየት መሾሯን ትቀጥላለች።
የቀናት ዑደት ታዲያ የበጀት መዝጊያ ላይ ደርሶ የታሰበው ዕድገት እና የተተነበየው መመንደግ በየት በኩል እንደታየ ለሕዝብ እንደራሴው ለማስረዳት በደፈረው መንግሥት፣ አስቀድሞ በካድሬዎቹ በኩል ‹‹ዕቅዱ ተለጥጦ ነው እንጂ ማሳካት የሚቻልበት አቅም አለ/ነበር እና ተሳክቷል›› የሚሉ መረጃዎች ከተማዋን በስፋት መሙላት ጀምረው ነበር። የተገባው ቃል ኪዳንም ቀቢጸ ተስፋ ሆኖ ቀረ። ኢትዮጵያም አዲስ በጀት ዓመት በአዲስ ዕቅድ እና በጀት ጀመረች፤ ሌላ ዓመት። በዚህ ጉዳይ መቀለድ የማይደክመው ሕዝብ በርካታ ቀልዶችን በጦማሪዎቹ አንደበት ሲያስነግር እና ሲያስፈግግ እንደነበርም አይረሳም።
ታዲያ ይህ በተስፋ ብቻ በሰማይ ያለችውን ላሙን ለማየት እንደቋመጠ እና ወተቷን ለመጠጣት እንዳንጋጠጠ እንጥፍጣፊ እንደናፈቀው ከሰማይ የሚፈጠፈጡ ቱጃሮች እና ፖለቲከኞች ተጭነው የሚገድሉት ሕዝብ በእጅጉ እየበረከተ ይመስላል። በፖለቲካ ውስጥ የሚታየው የመውጣት እና መውረድ የመተላለፉ ፍትጊያዎች ትኩሳታው ሕዝብን እያቀለጠ ዓመታትን የመከራ ለማድረጉ አሁንም ተጨባጭ ምክንያቶችን መዘርዘር በኢትዮጵያ ውስጥ ቀላሉ ሥራ ይመስለኛል።
የሆነው ሆኖ ታዲያ፣ በቅርቡ የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ አዳዲስ አባላትን የመረጠ እና ነባር ተብለው በፊት መስመር ላይ ስናያቸው የከረምናቸውን ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ያገኙታል ተብሎ የተጠበቀውን ስፍራ ሲነፍጋቸው የታየው አገር ማስተዳደር ተራው የደረሰው ብልጽግና፣ በፕሬዘዳንቱ ማለትም በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኩል እንደ ፓርቲ ቃል ገብቷል።
ቃል በቃል ጠቅላዩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ የቴሌቪዥን መስኮት ሲናገሩ ‹‹በቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔ ኢትዮጵያ አንድም ኩንታል ይሁን ስንዴ ወደ ውጭ ትልካለች›› የሚል ቃል ወጥቷቸዋል። የዚህ ጉዳይ አፈጻጸም እንዴት ይሆናል ወይም አይሆንም የሚል ክርክር ውስጥ መግባት አያስፈልገንም፤ ቢያስፈልግም ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያጠኑት እና ሰፊ ትንታኔ የሚሰጡበት ጉዳይ ነው።
ነገር ግን፣ አሁን ላነሳው የፈለግኩት ጉዳይ በእርግጥ ብልጽግና ፓርቲ አሻግሮ የተመለከታት እና እውን እንደምትሆን ኹለተኛ ማሰብ እንኳን አያስፈልገውም የተባለችውን ኢትዮጵያ በተመለከተ ነው።
ከአራቱም ማዕዘናት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰማው ጉዳይ በእጅጉ ተስፋ ከማስቆረጡም ባለፈ ተስፋ ሊጣልበት የሚችል አንድ በጎ ጅማሬ እንኳን ማየት ብርቅ የሆነበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። ይህን ደግሞ የገዢው ፓርቲ ሹማምንትም ሆነ ሕዝብ እኩል የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። ከሳምንታት ግፋ ቢልም ከወር በፊት በአገሪቱ ሰሜናዊ ችግር ምክንያት ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ መንግሥት በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የቀድሞዎቹ የሕወሓት ኢሕአዴግ ነባር አመራሮች ከዕስር በተለቀቁ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ‹‹ስለ ፍትሕ ሥርዓት ለማውራት በጣም ገና እና ሩቅ ነን›› በሚል በአደባባይ የፍትሕ ሥርዓቱን ያንኳሰሱበትን ንግግር አንረሳም።
ይህ ንግግር ታዲያ ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲነሳ የነበረ እና በተለይም ደግሞ የተጠያቂነት ጉዳይ በእጅጉ የመነመነ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ፣ በለውጡ ማግሥት መንግሥት ከፍተኛ መዋቅራዊ ማሻሻያ ሠርቷል፣ ተጠያቂነትም ይሰፍናል የሚሉ ቃልኪዳኖችን እስኪበቃን ተግተን ነበር፤ አልሆነም።
እንዲያውም ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል በተባለው መሠረት የፍትሕ ተቋማት ተገንብተዋል በተባለ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ነበር በራሳቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍትሕ ሥርዓትን ለማውራት ገና ሩቅ መሆናችን የተነገረን። ታዲያ በአገረ መንግሥት ግንባታ ረገድ ዋነኛውን ዋልታ ገና መሠረቱን ሳንገነባ ወደ ገነት የምናደርገውን ጉዞ ያቀድነው በየትኛው በጎ ዕሳቤ ነው?
ከጥቂት ጊዜያት በፊት የአገልግሎት ጊዜውን በውል ሳይጨርስ እንዲነሳ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅን በተመለከተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተደረገው ውይይት እና በተለይም ደግሞ ከአንድ የምክር ቤት አባል የተነሳው ጥያቄ ኢትዮጵያን በውል የሚያሳይ ይመስለኛል። የሕዝብ እንደራሴው ሀንጋሳ ኢብራሒም (ዶ/ር) በወቅቱ በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል ከ300 በላይ ወረዳዎችን ተቆጣጥሮ ግብር እየሰበሰበ ባለበትና የአማራ እና አፋር ወንደሞቻችን የሕልውና ስጋት ባለቀቃቸው ሁኔታ እንዴት አዋጁን ለማንሳት እንጠየቃለን የሚል ሐሳብ አንስተው ነበር።
በእርግጥ ይህ ጉዳይ የሁሉም ጥያቄ ቢሆንም ከመንግሥት ወገን ደግሞ ውጫዊ ጫናዎች እንዳሉበትም አይዘነጋም። ነገር ግን፣ ‹‹መጀመሪያ ባልዘፈንሽ፣ ከዘፈንሽም ባላፈርሽ›› እንዲሉ ከጫናውም፣ ከጉንተላውም በቆመጨጨ አመራር መጽናቱ የሚያዋጣ ይመስለኛል (አከራካሪ እንደሆነም አላጣውም)።
ታዲያ ይህ ከቀን ወደ ቀን የተፈናቃይ ቁጥር እያየለባት፣ የዕርዳታው መጠን እየተንጠፋጠፈባት፣ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ቁመና ወገቤን ብሎ ማቃሰት በጀመረበት፣ ዜጎች ተረጋግተው እንዳይኖሩ ከፍተኛ የደኅንነት እና የሕልውና ስጋት ባለበት ሁኔታ የብልጽግና አሻግሮ መመልከት ምናልባትም የኢሕአዴግ ዘመንን ‹‹ዕቅዱ ተለጥጦ ነው›› ዓይነት ዘፈን እንዳይደገም ከወዲሁ ቢታሰብበትስ? የገነት ጉዞውስ እንዲህ በሲዖል ውስጥ ማለፍን ይጠይቅ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
በሙስና እና ብልሹ አሠራር በኩልስ ቢሆን። እንዲያው አዲስ አበባን ለማሳያነት ብናነሳ ከዝንጆሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ የሚያስብሉ አንዱ ከአንዱ በምንም የማይሻል የአሠራር ሥርዓት ብልሹት በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍቷል። ሕዝብን ማገልገል ከባድ ኃላፊነት መሆኑን ተነግሮን በማለዳ ወደ አንድ የመንግሥት ተቋም ጎራ ስንል በእውን መንግሥት አለ? የሚስብሉ ድፍረትን በተሞላ መልኩ በግልጽ ዕጅ መንሻ የሚጠየቅባቸው አጋጣሚዎች እጅግ ብዙ ናቸው።
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ይህን የመሰለ ዐይን ያወጣ እና ማን አለብኝነት ሲነግስ በእርግጥም ከባድ ፈተና እንደሆነ መንግሥት ራሱ ከማንም በላይ ይረዳዋል። ያቺ በልጆች የተረት መጽሐፍ የምናውቃት ‹‹ዩቶጲያ›› የሆነችው ኢትዮጵያ እንድትመጣ ጉልህ ዕርምጃዎችን ማየት ያለብን ሰዓት ቢሆንም ፍንጭ አላየንም። በርካታ ዜጎች ሲዖልን እየተለማመዱ ባለበት ሁኔታ መዳረሻቸው ገነት እንደሆነ ሲነገራቸው የሚያነሱት ጥያቄ ሰፊ ነውና መንግሥታዊ ልበ ሰፊነት ግዴታ እንደሚሆን መጠቆም ያስፈልጋል።
የኑሮ ውድነቱ፣ መልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ያላባራው ሰሜናዊው ጦርነት እያልን ዘርዝረን በሌላ ወገን ደግሞ የኢትዮጵያን ያለጥርጥር መበልጸግ ስናነሳ በእርግጥም ጉዞው በሲዖል ውስጥ ወደ ገነት እንደሆነ እናያለን። የሲዖልን ጨለማ ለማሸነፍ አይበገሬ ብርሀን መያዝ እንጂ፣ ጨለማን መርገም ብቻ መፍትሔ እንደማይሆን አናጣውም። ምርታማነት ከፍ ብሏል ይባልና ሕዝብን ከሲዖል ያድናል ብለን ስንጠብቅ በአንድ አዳር የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ሰማይ ነክቶ ያድራል። ጉዳዩ እንዴት ነው ሲባል ‹‹ምርቱ ተመርቶ ነበር። ነገር ግን የተፈናቃይ ቁጥር ስለበዛ ለዕርዳታ ውሏል›› ተብሎ ይድበሰበሳል። የእህል ዋጋም ተሰቅሎ ይቀራል፤ አንድ ጫና በሕዝብ ላይ ይሆናል።
ባሳለፍነው ዓመት በርካታ የስንዴ ምርት ተመዝግቦ እንደነበር ተነግሮናል። ታዲያ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እንደተባለችው የዳቦ ቅርጫት ልትሆን ትችላለች ብለን ተስፋችንን ሰንቀን ብንጠብቅ በጸጥታ ምክንያት ለተፈናቀሉ መዋሉን ሰማን። በዚህ ጊዜ ታዲያ ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን የጸጥታው ችግር የማይፈታበት ምክንያት ምንድነው ተብሎ ቢጠየቀም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
በዚህ አያያዝ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደጠቀሱት በሚሊዮኖች ኩንታል የሚለካ ስንዴ ቢመረትም የዳቦ ዋጋ ሰማየ ሰማያትን አልፎ ከመወንጨፍ እንደማይድን መገመት አይከብድም። ምክንያቱ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት የጸጥታ ችግሮች አርሶ ሳይሆን ከመንግሥት የሚሰጠውን ምጽዋት እየጠበቀ የሚኖር ዜጋን መሽቶ በነጋ ቁጥር እያበራከትን ስለሆነ ነው፤ መነሻው ደግሞ የጸጥታ ችግር።
ታዲያ በዚህ ሁሉ ከፍተኛ ማጥ ውስጥ ያለችን አገር ተረክቦ ማስተዳደር በእርግጥም ፈታኝ ቢሆንም፣ ግብን ስናስቀምጥ እንዲያው የሚመስል እና ለተግባራዊነቱ መልፋት በሚያስችል ሁኔታ ቢሆን ይመረጣል። በችግር እና በፈተና ወቅት መልካምን ወቅት አሻግሮ መመልከት በራሱ የጤናማ እና ትክክለኛ ሰብዓዊ ፍጡር መለያ ነው። ይሁን እንጂ በአገር ደረጃ ነባራዊ ሁኔታን መካድ ወይም ሸፋፍኖ ስለመጪው የተድላ ኑሮ ማውራት የዛሬውን አሰቃቂ ሁኔታ አይቀይረውም ወይም ደግሞ እንዳልነበረ አያደርገውም።
በዚህ ብቻም አይደለም ወደ ከነዓን ከመትመሙ በፊት በባቢሎን ግዞት ውስጥ ምን ያህል እንደሚኖር ይህ ሕዝብ ሊያውቅ ይገባል። የታለመችው ‹‹ዮቶጲያ›› እስክትመጣስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ገነትን አጮልቆ መመመልከት ከመጎምጀት ያለፈ ሲዖልን ገነት አያደርግም። ሠላም በመድራችን ላይ ይስፈን! የኢትዮጵያ ሠላም ይመለስልን።
ኤርምያስ ሙሉጌታ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014



