መቋጫ ያላገኘው የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሰቆቃ

0
1626

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ከዕለት ዕለት እየባሰና እየከፋ መጥቷል። በየትኛውም አጋጣሚና በየትኛውም አካባቢ ያለ ሰው ደኅና ውሎ ስለመግባቱ ከአምላኩ ጋር ከመነጋገሩ በቀር ዋስትና የሚሰጠው አካል ያለ አይመስልም። ነገሩ አንጻራዊ ሠላም ባለባቸው አካባቢዎች የተጋነነ መስሎ ሊታይ ቢችልም፣ እውን ግን በየዕለቱ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ የመገደላቸው ዜና ሳይሰማ ተውሎ አያድርም።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና መሰል ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ በአገር ውስጥ ያሉና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ይህን የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ይከታተላሉ። በክትትላቸው ያገኙትን፣ የሰሙትና ያዩትን፣ እንዲሁም ያጣሩና ያገናዘቡትን ይፋ ያደርጋሉ። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሳምንት በፊት ጦርነት እና አለመረጋጋት በነበረባቸውና ባለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ካደረገው ዳሰሳ ተነስቶ የደረሰበትን ይፋ አድርጓል።

የአዲስ ማለዳው ሳሙኤል ታዴ ይህን የኮሚሽኑን ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ የሕግ ባለሙያና ባለድርሻን በማናገር፣ እንዲሁም ሠነዶችን በማገላበጥ ሰብዓዊ መብቶች በሕገ መንግሥቱ ያላቸውን ስፍራ፣ አሁን ያለውን ሁኔታና ወደፊት የሚጠበቀውን በሚመለከት ነጥቦችን በማንሳት ጉዳዩን የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በሠለጠኑ አገራት የሚኖሩ ዜጎች ስለሞትና ግድያ እንዲሁም ስለሌሎች መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ከማሰብ ወጥተው ሐሳባቸውን በነጻነት መግለጽ፣ የፈለጉትን አቋም በመያዝ ማንኛውንም ነገር በነጻነት የመሞገትና የመተቸት ደረጃ ላይ ከደረሱ ቆይተዋል። በአንጻሩ በድህነት ውስጥ በምትገኘውና አለመረጋጋት በማይታጣባት አፍሪካ፣ የመሠረተ ልማት ፍትሐዊ ተደራሽነት ራሱ ገና ከአትሮንሱ ያልወረደ አነጋጋሪ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያም ከዛ ተርታ ትመደባለች። ሠለጠኑ የተባሉ አገራት ከደረሱበት ደረጃ መድረሱ ቀርቶ፣ አሁን ላይ ለሰው ልጅ ቀዳሚና መሠረታዊ የሆነውን በሕይወት የመኖር ዋስትናና አካላዊ ደኅንነትን ማስጠበቅ እንኳ ፈተና እየሆነ መምጣቱ ይስተዋላል።
አሁን ላይ ባለው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ውስጥ ስለዜጎች ሰብዓዊ መብት በሰፊውና በዝርዝር ተጠቅሶ ይገኛል። በዚህም መሠረት በአስራ አራተኛው አንቀጽ፣ ‹ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገረሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት አለው› ይላል።

አስራ አምስተኛውና ተከታዩ አንቀጽም እንዲሁ፣ ‹ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለው ገልጾ፣ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፤ በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበትም የመጠበቅ/ጥበቃ የማግኘት መብት አለው› በማለት ይገልጻል።

ሆኖም ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሕገ-መንግሥቱ ላይ ከተቀመጡ መብቶች ተቃራኒ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል።

ሪፖርቶች ምን አሉ?
በተለይም በ2010 ከተደረገው ለውጥ በኋላ፣ በዜጎች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰትና ሰቆቃ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ብዙዎች ይገልጻሉ። ሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎችን የሚያስፈጽሙ አካላት አቅመ ደካማ መሆን፣ በዜጎች ላይ የሚደርሰው ሥቃይ ከብዙ አቅጣጫዎች እንዲሠነዘርና አጠቃላይ ችግሩንም የባሰ አንዲሆን እንዳደረገውም ይስማማሉ።

ከሰሞኑ መጋቢት 2/2014 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርትም፣ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃና ግፍ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

ከዚህም ባለፈ የጦርነት ቀጠና በሆኑና ሕወሓት ተቆጣጥሮ በቆየባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች፣ በርካታ አስከፊ ግፎች በዜጎች ላይ መፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በኹለቱም ክልሎች በግለሰቦች ላይ ከፍተኛ የሆነ በጭካኔ የተሞላ ድብደባ፣ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዝርፊያና ሌሎች ድርጊቶች መፈጸማቸውንም ነው ሪፖርቱ የገለጸው።

በዚህም በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን አንዲት የ30 ዓመት ሴትን የመንግሥት ሠላይ ነሽ በማለት ደረቅ እንጨት ተሰባብሮ እስከሚያልቅ እንደደበደቧት፣ በአማራ ክልልም እንዲሁ ጋሸና ከተማ ውስጥ ‹ብር ስጡን› በማለት አንድን ግለሰብ ልብሳቸውን በማስወለቅ ዘቅዝቀው ውኃ ውስጥ ከዘፈቋቸው በኋላ፣ ኹለት እግራቸውን በሚስማር ወግተው፣ ብልታቸውን በካራ ተልትለውታል።

ከኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በተጨማሪ፣ ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊነት ሕጎችም የጭካኔና የማሰቃየት ተግባራትን በየትኛውም ሁኔታ በጥብቅ እንደሚከለክሉ ኮሚሽኑ አስረደቷል። ምርመራ ባካሄደባቸው አካባቢዎችም ብዙ ዜጎች ኢ-ሰብዓዊ በሆነና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ መሰቃየታቸውን፣ መደብደባቸውን፣ መገደላቸውንና መንገላታታቸውን በምርመራው አሳውቋል።

ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሠር አይችልም የሚል ድንጋጌ ቢኖርም፣ ከሕግ አግባብ ውጭ ታሥረው የሚገኙና ሰብዓዊ መብታቸውን የተነጠቁ ዜጎች ስለመኖራቸው ይነገራል። ለዚህም ማሳያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጦርነቱ በተካሄደባቸው በአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች ዓለም ዐቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀልን ሊያቋቁም በሚችል መልኩ የዕገታና አስገድዶ መሠወር ተግባራትን ፈጽመዋል ሲል አትቷል።
ከትግራይ ኃይሎች በተጨማሪም፣ የፌዴራል፣ የአማራና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎችም በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አውድ ውስጥም ቢሆን መጠነ ሰፊ የዘፈቀደ ዕሥር ፈጽመዋል ይላል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው በዚሁ ሪፖርትም ጠቅለል ያሉ መረጃዎችን ሲገልጽ፣ ሕወሓት ከሐምሌ ወር ጀምሮ በአፋርና አማራ ክልሎች ባደረገው መስፋፋትና በከፈተው ጦርነት ሳቢያ፣ ሆነ ተብሎው የተፈጸሙ ግድያዎችን ሳይጨምር ቢያንስ 403 ንጹኃን ሰዎች ሲገደሉ፣ 309 የሚሆኑት ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

እንዲሁም፣ በኹለቱም ክልሎች በተደረገ ምርመራ 346 ሰዎች በሕገወጥ መንገድ የመንግሥት ኃይሎች ሠላይ ናችሁ፣ ገንዘብ አምጡ፣ ንብረት እንዳይወሰድ ተከላክላችኋል፣ ወዘተ. በሚል ምክንያት በጭካኔ ተገድለዋል። የጠፉና መረጃቸው ያልተገኘ በመኖራቸውም የሟቾች ቁጥር ከዚህም የላቀ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

በእነዚህ ክልሎች በዋናነት በትግራይ ኃይሎች በቡድን የተደፈሩ፣ በልጆቻቸው ፊት አስገድዶ መድፈር የተፈጸመባቸው በርካታ ሴቶች ሲኖሩ፣ አብዛኞቹ የሚደርስባቸውን ጫና በመፍራት ራሳቸውን ደብቀዋል። ሆኖም ቁጥራቸው ከ200 በላይ የሚሆኑ አስከፊ የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች መኖራቸው ተገልጿል።

እንዲሁም፣ በርካታ የጤናና የትምህርት ተቋማት፣ ባንኮችና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች በአፋርና አማራ ክልሎች ወድመዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 አንስቶ ተኩስ አቁም እስከታወጀበት እስከ ሰኔ 21/2013 ድረስ ባሉት ወራት ውስጥ፣ በትግራይ ክልል የደረሰውን አስመልክቶ ጥቅምት 23/2014 ባወጡት የጣምራ ምርመራ ሪፖርት፣ መቀሌ 29፣ በአክሱም 100፣ በቦራና አምደውሃ ከ70 የሚበልጡ ሰዎች፣ በኹመራ 15 ሰዎች፣ ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎችም እንዲሁ በውቅሮ፣ በጥቅሉ ከ280 የሚልቁ ንጹኃን ተገድለዋል።
እንዲሁም ብዙ ልጃገረዶችና ሴቶች ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ከእነዚህም ውስጥ በቡድን የተደፈሩ፣ በአፋቸውና በመቀመጫቸው የተደፈሩ፣ እንዲሁም ባዕድ ነገር ወደ ብልታቸው እንዲገባ የተደረጉና ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ጥቃት የተፈጸመባቸው ይገኛሉ።

በተጨማሪም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከመኖሪያው ተፈናቅሏል። ትምህርት ቤቶች እና ጤና ተቋማት ወድመዋል። መኖሪያ ቤቶችና የእምነት ተቋማት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ይህም ሕወሓት ክልሉን ዳግም ከተቆጣጠረ ጀምሮ እስካሁን ያለውን ሳይጨምር ነው።
ሰሞኑን በቤንሻጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልል ተፈጽሟል የተባለው፣ የተገደሉ ሰዎችንና አንድን በሕይዎት የነበረ ሰውን ከነነፍሱ በእሳት ሲቃጠል የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስልም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ገደብ ማለፉን ማሳያ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ኢ-ሰብዓዊ አያያዝን በተመለከተም፣ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት እንዳለው በሕገ-መንግሥቱ በግልጽ ተቀምጧል።

ይህን ድርጊት የፈጸሙት ‹የመንግሥት የፀጥታ አካላት ናቸው› መባሉ ደግሞ፣ የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅና መብታቸው እንዲከበር የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት የሚባለው መንግሥት፣ በተቃራኒው ደኅንነታቸውን ካለማስጠበቅ አልፎ ራሱም የዜጎችን መብት የሚጥስ አካል ሆኗል በማለት ቅሬታቸውን ደጋግመው የሚያሰሙ በርካቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይህን በማስመልከት በሠጠው ማብራሪያም፣ ድርጊቱ የተፈጸመው የካቲት 23/2014 በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ መሆኑን አስታውቋል። በዛም በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ታጅበው ወደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች ቦታዎች በሚሔዱ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች ከባድ መሣሪያ ተኩሰው ከ20 ያላነሱ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን የገደሉና 14 የሚደርሱትን ደግሞ ያቆሰሉ ሲሆን፣ በዕለቱ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል ተኩስ ተከፍቶ ከታጣቂ ኃይሎች ከ30 ያላነሱት ተገድለዋል።

በማግስቱ የሸሹትን ለመያዝ በተደረገ ፍተሻ ተጠርጣሪዎች እንደተያዙና 10 ሰዎችም እንደተገደሉ፣ በዚህም የተገደሉትን አስከሬንና ከተገደሉት ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ሌላ አንድ ተጠርጣሪም በሕይወት ሳለ ወደ ጫካ ተወስዶ ከአስከሬኖቹ ጋር በእሳት እንዲቃጠል ተደርጓል ነው ያለው ኮሚሽኑ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ‹‹የመንግሥት ሕግ አስከባሪ አባላት ራሳቸው በግልጽ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች ሆነው መታየታቸው፣ ሰዎች በሕጋዊ ሥርዓት ላይ የሚኖራቸውን እምነት የሚሸረሽርና ለተጨማሪ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚያጋልጥ ነው። በመሆኑም መንግሥት የምርመራውን ሒደትና ውጤት በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግና ፍትሕን ለማረጋገጥም የሟች ቤተሰቦችን ሊክስ ይገባል›› ብለዋል።

ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ በዜግች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚደርስ የሚታወቅ ነው። በወለጋና ምዕራብ ኦሮሚያ የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በርካቶችን ለአሰቃቂ ሞት፣ ለመፈናቀልና ለርሃብ ዳርገዋል።
በተለይ ደግሞ በቅርቡ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ የተፈጸመውን ግድያ አስመልክቶ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ግድያው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ያለፍርድ የተፈጸመ ነው ሲል ማሳወቁ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ባወጣው መግለጫ፣ አገሪቱ ላይ የሕግ የበላይነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መግባቱን ጠቅሶ፣ ዜጎች በዚህ መልኩ ክቡር የሆነ ሕይወታቸውን እንዲያጡ ምንም ዓይነት ምክንያት ተገቢነትም የለውም ሲል ነበር የገለጸው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ፣ አይሲዲ ቀበሌ በመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች በተፈጸመው አሰቃቂና ከዳኝነት ውጭ የሆነ ግድያ (Extrajudicial killing) ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉ በአፋጣኝ በሕግ ተጠያቂ ይደረጉ ሲል ለመንግሥት ጥሪ አቅርቧል። በተጨማሪም፣ በመላ አገሪቱ በተደጋጋሚ በታጠቁ ኃይሎች ማለትም በመንግሥት ታጣቂ ኃይሎችና የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች በሚደርሱ ጥቃቶች በርካታ ንጹኃን ሕይወታቸውን ማጣታቸውን እና ጉዳዩም እጅግ አሳሳቢና መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባው መሆኑን አመላክቷል።

ኢሰመጉ አክሎም፣ መንግሥት እነዚህን ሰብዓዊ መብቶች የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበት፣ ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሠነዶች እንደሚደነግጉና የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትም በአንቀጽ 13 ላይ ይህን የመንግሥት (የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት) ኃላፊነት በግልጽ ማስቀመጡን ገልጿል።

በሕግ አምላክ!
መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ እየሞከረ እንኳ አይደለም ሲሉ የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

አጥፊዎች ማንነታቸውና ያሉበት ቦታ በግልጽ እየታወቀ፣ ለሕግ እንዲቀርቡ እናደርጋለን ከማለት ውጭ ተገቢው ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ባለመቻሉ በንጹኃን ላይ የሚያደርሱትን ግፍ እንደ ትክክለኛ ነገር እየቆጠሩት ይገኛልም ነው የሚሉት ባለሙያዎች። በዚህም የጥቃት ፈጻሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በንጹኃን ላይ የሚፈፀመው የመብት ጥሰትም በዚያ ልክ እየተባባሰ መሔዱን ጨምረው ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ሰብዓዊ መብቶች ሕግ ሳይቀመጥ፣ ጥበቃና ሽፋን ሳይሰጣቸው ዜጎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚያገኟቸውና የሚከበሩላቸው መብቶች ናቸው።

መንግሥት እነዚህን መብቶች ከመጠበቁ በፊት ራሱ ሰብዓዊ መብቶችን ሊያከበር ይገባል ያሉት ባለሙያው፣ በሌሎች አካላት እንዳይጣሱ ከመከላከል ባለፈም እንዲከበሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት አለበት ሲሉ ያስረዳሉ። አንድ ሰው በሕይወት እንዲኖር ምቹና ደኅንነቱ የተረጋገጠ መኖሪያ ያስፈልገዋል የሚሉት ባለሙያው፣ ይህን የሚያረጋግጠውም መንግሥት መሆኑን ነው ያነሱት።

በዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌም ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ዋነኛ ኃላፊነት የተጣለው የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም መንግሥት በዜጎች ላይ ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት ቀድሞ መከላከል አለበት ብለዋል። ጥቃት ቢፈጠር እንኳን በፍጥነት ማስቆምና አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ የግድ እንደሚልም ነው የሚገልጹት።

መንግሥት የተፈጠረውም ሆነ የመንግሥት ዋነኛ አስፈላጊነት የዜጎች መብት ሳይሸራረፍ ተፈጻሚ እንዲሆን ለማድረግ ነው ያሉት ባለሙያው፣ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ‹መንግሥት ያስፈልጋል ወይ?› የሚል ጥያቄ ያስነሳል ባይ ናቸው።
ግጭት ባለባቸውም ሆነ በሌለባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መኖሩን ካነሱ በኋላም፣ በተለይ ሕግ አውጭ አካላት ያወጧቸው ሕጎች ተፈጻሚነታቸውን መፈተሽና መከታተል እንደሚገባቸው አስምረውበታል።

ሆኖም ግን፣ አሁን ያለው አገራዊ ችግር በደንብ መጤን ካለበት የአስተዳደር መዋቅሩ ላይ ነው የሚል እምነት አላቸው። መንግሥት ጉዳት ከደረሰ በኋላ ለዚያ የሚሆን ማስተባበያና ማስተዛዘኛ መስጠት የለበትም የሚል ትችታቸውን የሰነዘሩት ካፒታል፣ እየተፈጠሩ ላሉ አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አንድም ማንነትን መሰረት ያደረጉ የፀጥታ መዋቅሮች ሊሆኑ ይችላሉ ነው የሚሉት። በተጨማሪም ለዚህ የዳረገን ሕዝቡ ጋር ያለው የእርስ በእርስ ግንኙነት ማንነት ተኮር ቅራኔ ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው።
ይሁን እንጂ፣ ይህን ሁሉ ተረድቶ የአስተዳደር መዋቅር ማሻሻያ በማድረግ የሚፈጠሩ ችግሮችን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

መንግሥት በአገሪቱ ያለውን የፀጥታ ኃይል የሚመራ ሆኖ ሳለ፣ በአንጻሩ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥሰት የሚፈጸም ከሆነ፣ ችግሩ የት ላይ ነው ብሎ መፈተሽ ይበጃል ብለዋል። እንደ አገር የተፈጠረው ድባብ ዐይን ለዐይን የማያስተያይ ስለሆነም ሕዝቡ፣ ምሁራን፣ መንግሥትና ኹሉም የሚመለከተው አካል ሰብዓዊ መብቶችን ጉዳዬ ብሎ ችግሮች እንዲቀንሱ የሚችለውን ማድረግ እንዳለበትም ይመክራሉ።

አሁን ላይ ከወትሮው በተለየ መልኩ በጣም አስደንጋጭ ወንጀሎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሲፈጸሙ መታየቱም፣ ጉዳዩ ከሕግ ማስከበር በላይ እንደሆነና ምናልባትም የመንግሥት መዋቅሩ ዜጎችን እኩል በማያይ እና ለሰብዓዊ መብቶች ግድ በማይሰጠው መልኩ ተዋቅሮ ይሆን ወይ ያስብላል የሚል ጥያቄ አዘል ሐሳብም አላቸው፤ የሕግ ባለሙያው ካፒታል።

ፖለቲከኞች ዋናውን ነገር ረስተው ‹ምንም› በሆኑና በትንንሽ ነገሮች ላይ ጊዜያቸውን እና አቅማቸውን ማጥፋታቸው ለዚህ ዳርጎናል ሲሉም ይገልጻሉ። የሕግ ባለሙያው ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉም፣ የአስተዳደር መዋቅሩ ሳይስተካከል ስለሕግ የበላይነት ብቻ በተደጋጋሚ ማንሳት ተራ ምኞት ሆኖ እንዳይቀር የሚል ሥጋታቸውን አጋርተዋል።

ሕይወት አዘል ቁጥሮች!
በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ በርካታ ዜጎች በየቦታው አስከፊ በሆነ ሁኔታ ይገደላሉ፤ ይፈናቀላሉ። በጥቅሉም ሰፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል።
በዚህም በጦርነት እና ግጭቶች የተነሳ ከተገደሉት ውጭ፣ በርካታ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው የሰብዓዊ ዕርዳታ እየጠበቁ ይገኛሉ። ከተለያዩ ቦታዎቸ የተፈናቀሉ ከ11.6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአማራ ክልል ብቻ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉ ሲሆን፣ በጦርነት ምክንያት አካባቢያቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ከ300 ሺሕ በላይ ዜጎች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአፋር ክልልም እንዲሁ ከ350 ሺሕ በላይ ዜጎች በጦርነቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ነው የሚነገረው።

አዲስ ማለዳ በአገሪቱ በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸውን ተከትሎ እየቀረበላቸው ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ መረጃ ለማግኘት፣ ከብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ደበበ ዘውዴ ጋር ብትደውልም ‹‹የፈለክበት ሔደህ ክሰስ!›› በማለት መረጃ በመከልከል ስልካቸውን ዘግተዋል።

የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 28 ላይ፣ ‹‹የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት ዕርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር ወይም ኢ-ሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም። በሕግ አውጭ ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምህረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም›› ሲል ይገልጻል።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here