በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አራት ዞኖች የሚገኙ ከ60 ሺህ በላይ ህጻናትን መንከባከብ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

0
1252

ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋና ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ዞኖች የሚገኙና በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ከ60 ሺህ በላይ ህጻናትን መንከባከብ የሚያስችል ፕሮጀክት በደሴ ከተማ ይፋ ተደርጓል።

ፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት መርሃ ግብር ሲሆን፤ በአራቱ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ላይ ይተገበራል ተብሏል።

ፓዝ ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በአማራ ክልል ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ህጻናት በጦርነቱ ሳቢያ ክፉኛ መጎዳታቸውን ማረጋገጡን የፓዝ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ትርሲት ግርሻው ተናግረዋል።

በአካባቢዎቹ የተደረገው ጦርነት በበርካታ ህጻናትና እናቶች ላይ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረሱን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ መርሃ ግብሩ ከሰሜን ወሎ ዞን ግዳንና ራያ ቆቦ ወረዳዎች፣ ከደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ፣ ከዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ዞን ሰቆጣ ዙሪያና ዳህና ወረዳዎች እንዲሁም ከሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም 60 ሺህ የሚደርሱ ህጻናትና ከ15 ሺህ በላይ የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶች በቀጥታ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል። ከ446 ሺህ በላይ ህዝብ ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ይህ የቅድመ ልጅነት ዘመን እንክብካቤ መርሃ ግብር 500 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፤ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው ቢግ ዊን ፊላንትሮፊ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ነው።

በመሆኑም በአማራ ክልል የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው በአራት ዞኖችና ስድስት ወረዳዎች የሚገኙ ህፃናትና እናቶች በዚሁ የክብካቤ በመርሐ ግብር መካተታቸውን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ያደታ፤ በኢትዮጵያ 59 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት በዕድሜያቸው ልክ መድረስ ከሚገባቸው አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት ያልደረሱ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

ፓዝ ኢትዮጵያ የጀመረው የቅድመ ልጅነት ዘመን፣ የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶች ክብካቤ መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ መጠቆማቸውን ከደቡብ ወሎ ኮሚዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ም/ አስተዳዳሪ ተስፋ ዳኛው በበኩላቸው፤ ፓዝ ኢትዮጵያ የቅድመ ልጅነት ዘመን እንክብካቤው ህፃናት በአካላቸው የጠነከሩ በአዕምሯቸው የጎለበቱ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስችል በመሆኑ፤ በሚመለከታቸው የመንግስት መዋቅሮች ተገቢው ድጋፍና ክትትል ይደረጋለታል ብለዋል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here