የአማራ ክልል ተቋራጮች ማኅበር መንግሥት የግንባታ ዋጋ ማሻሻያ የማያደርግ ከሆነ የግንባታ ሥራዎች ይቆማሉ ሲል ገለጸ

0
598
በክልሉ የሚሠሩ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች በክልሉ ያሉ ተቋራጮችን ተሳታፊ ያደረጉ አይደሉም ብሏል

የአማራ ክልል ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር መንግሥት የግንባታ ዋጋ ማሻሻያ የማያደርግ ከሆነ የግንባታ ሥራዎችን ለማቆም እንደሚገደድ ገለጸ።

ማኅበሩ በክልሉ ባለው ነባራዊ ኹኔታ በግንባታ ላይ ያሉ እና ግንባታቸው በተለያዩ ምክንያቶች የዘገዩ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም የማኅበሩ አባላት የሆኑ ተቋራጮች ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸውን ተከትሎ፣ የክልሉ መንግስት ችግሩን በመረዳት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ደብዳቤ መጻፉን አመላክቷል።

ማኅበሩ፣ የግንባታ ግብዓት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶች በበቂ ኹኔታ ገበያ ላይ አለመኖራቸው፣ እንዲሁም የነዳጅ ዋጋ ንረትና ዕጥረት መከሠት የዘርፉ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆናቸውን አስገንዝቧል።

በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ መከሰት፣ የዶላር ምንዛሪ ማሻቀብና የግንባታ ሠራተኛ ዋጋ መጨመር፣ በትግራይ ወራሪ ኃይል የተነሳ በክልሉ ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተዳምሮ፣ ተቋራጩች ባልተለመደ መልኩ ገበያ ላይ የተከሰተውን ግሽበት መቋቋም የማይችሉበት ኹኔታ በመፈጠሩ፣ ብዙ ግንባታዎች በታቀደላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለመቻላቸውን ነው ማኅበሩ የገለጸው።

የአማራ ክልል ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሙሉቀን ቢተው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹትም፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ብዙ ተቋራጮች ማሽናቸው ተቃጥሏል፤ ሠራተኞቻቸውንም አጥተዋል። በዚህም ብዙዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር የማይችሉበት ኹኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ችግሩ እንደ አገር ቢሆንም በክልሉ ከነበረው ጦርነቱ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል ያለው እንደሚጎላ አንስተው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሔድ የሲሚንቶ አቅርቦት ዕጥረት መኖሩንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያሉ አብዛኛዎቹ የግንባታ ሥራዎች ቆመዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ጋር በመነጋገር ችግሩን ይፈታልናል የሚል ዕምነት በመኖሩም ማኅበሩ ደብዳቤ ጽፎ ለክልሉ መንግሥት ማስገባቱን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊትም ችግሩ እንዲፈታ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጨምሮ በየጊዜው ለተለያዩ አካላት ደብዳቤ ቢጻፍም አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ነው የጠቆሙት።

ስለሆነም፣ አሁን ላይ ማኅበሩ የጻፈው ደብዳቤ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ፣ ብዙ ግንባታዎች የመቋረጥ ዕጣ ፈንታ እንደሚገጥማቸውና የማኅበሩ አባላት የሆኑ ተቋራጮችም ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገቡ መሆኑን አስገንዝቧል።
በሌላ በኩል፣ በክልሉ የሚሠራው የመልሶ ግንባታ ሥራ የክልሉን የግንባታ ሥራ ተቋራጮች ያቀፈ አለመሆኑ ተመላክቷል።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት በሰጡት ማብራሪያም፣ በሸዋና በወሎ ያሉ ተቋራጮች የበለጠ መጎዳታቸውን አንስተው፣ የመልሶ ግንባታ ሥራው በክልሉ የሚገኙ የግንባታ ሥራ ተቋራጮችን ያቀፈ ቢሆን ችግር ውስጥ ያሉ ተቋራጮች እንዲያገግሙ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

የተጎዱት ተቀምጠው እየተነጋገሩ ያሉት ከአንድ የማይታወቅ የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ከሚባልና በአዲስ አበባ ከተቋቋሙ ማኅበር ጋር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ለአብነትም ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት ከአማራ ክልል ተቋራጮች ጋር ቢገናኝ በቀጥታ ተጎጅዎችን ያገኛል ሲሉ ሐሳባቸውን ሠጥተዋል።

በዚህም፣ ማኅበሩ የመልሶ ግንባታ በጀቱ በክልሉ ላሉ ተቋራጮች ይሰጥ የሚል ጥያቄ ለክልሉ መንግሥት ማቅረቡን ጠቁመው፣ ይህ ከሆነ ተቋራጮች እንዲያገግሙና ትናንት ያቆሙትን ሥራ እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ ከአማራ ብሔራዊ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here