ጨውን ለምርት ግብዓት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ዕጥረት እንዳጋጠማቸው አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። ችግሩ የተፈጠረው ከፍተኛ የጨው መጠን የሚገኝበት የአፋር ክልል ካለው የጸጥታ ኹኔታ ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል።
አዲስ ማለዳ የጽዳት ምርቶችን በስፋት በማምረት የሚታወቀውና መቀመጫውን በአዲስ አበባ ባደረገው ረጲ ፋብሪካ ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች እንዳረጋገጠችው፣ በተለይ ከየካቲት እኩሌታ ጀምሮ ዕጥረቱ የጎላ በመሆኑ ፋብሪካው ጨው መጠቀም አቁሟል።
ፋብሪካው ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት በዋናነት ኤስ ኤል ኤስ (Sodium Lauryl Sulfate/SLS) የሚባል ኬሚካል እና ጨው የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ ያለ ጨው ኬሚካሉን መጠቀም ባለመቻሉ ሲዲኤ (Coconut diethanol amine/CDEA) የሚባል ኬሚካል ኹለቱን ተክቶ እያገለገለ መሆኑን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ሌላ አንድ የጽዳት ምርቶችን በሚያመርት ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያ፣ ለሥራው ብዛት ያለው ጨው እንደሚያስፈልግ ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰው፣ ከ20 ቀን ገደማ በፊት አንድ ኪሎ ጨው በስምንት ብር ነበር የምንገዛው፣ አሁን ግን በዕጥፍ ጨምረን በአስራ ስድስት ብር ነው የምንገዛው ብለዋል።
ችግሩ የተከሰተው አፋር ክልል ካለው ጦርነት ጋር በተገናኘ ነው ያሉት ባለሙያው፣ ዋጋው በዕጥፍ ጨምሮም የምንፈልገውን ያህል የጨው አቅርቦት ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ነው የገለጹት።
የቆዳ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁ ጨውን እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ መሆናቸው የታወቀ ቢሆንም፣ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ችግሩ እንዳላጋጠመው ገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ የኮሚዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ ብሩክ ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩትም፣ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ክረምት ላይ የምርት ዕቅዳቸውን ሲያወጡ የሚያስፈልጋቸው ጨው ስለሚታወቅ፣ ለዕቅዳቸው ማስፋፊያ የሚሆን ጭምር አንድ ጊዜ ነው ተገዝቶ የሚሰጣቸው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከጨው ጋር ተያይዞ ለረዥም ጊዜ በተደጋጋሚ የሚነሳውን ጥያቄ ለመፍታት ጨውን የሚተካ ኬሚካል ለማግኘት ከአንድ የሕንድ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ በመሆን የምርምር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ለዚህም ባለሙያዎች ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን እና የምርምር ሥራውም በቅርብ ቀናት ውስጥ ተጠናቆ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚደረግ ገልጸው፣ ከዚያ በኋላ ጨውን መጠቀም እንደሚቀር አመላክተዋል።
በሌላ በኩል፣ ጨውም ብቻ ሳይሆን ለጽዳት ምርቶች የሚሆኑ ሌሎች የግብዓት ኬሚካሎች ዕጥረትና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታዬ መሆኑን የጽዳት ምርቶችን በሚያመርት እና ምርቶችን ከውጭ አገር በማምጣት በሚያከፋፍል ተቋም ውስጥ ሠራተኛ የሆኑና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ይህም የሆነው በተለይ የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ከፈነዳ በኋላ መሆኑን ጠቁመው፣ ለሳሙና ምርት የሚያገለግል አንድ ኪሎ ግራም ሽቶ 1 ሺሕ 500 ብር ይገባ የነበረው አሁን 2 ሺሕ ብር ሆኗል ነው ያሉት።
እንዲሁም ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት አስፈላጊ የሆነው ኤስኤልኤስ (Sodium Lauryl Sulfate/SLS ) የተሰኘው ኬሚካል ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ላይ ከ170 ብር ወደ 240፣ ክፍለ አገር ደግሞ ከ180 ብር ወደ 250 ማደጉን ተናግረዋል።
በዚህም፣ በአሁኑ ወቅት የጽዳት ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያሳዩ መሆኑን ነው ያነሱት። ለአብነትም ፋብሪካ የተመረተ አንድ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ከ40 እስከ 50 ብር ይሸጥ የነበረ ቢሆንም በቀናት ውስጥ ከ70 እስከ 80 እየተሸጠ ነው ብለዋል። አምስት ሊትር ፈሳሽ ሳሙና እስከ 300 ብር እንደሚሸጥ አንስተው፣ ደረቅ ሳሙና ከ30 ብር በላይ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
አዲስ ማለዳ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ዋጋ ጥናት፣ ክትትል እና ቁጥጥር ዳይሬክተር መስከረም ባህሩ ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ማግኘት አልቻለችም።
ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014



