መንግሥት እንደመንግሥትነቱ ሕዝብን ከስቃይና ጥፋት መጠበቅ ዋናው ተልዕኮው ቢሆንም ይህንን ማስጠበቅ እንዳልቻለ በግልጽ የሚታይ ነው። ለዚህ ድክመቱ የተለያየ ምክንያት እየሰጠ እስካሁን ቢዘልቅም የንጹኃን ዕልቂቱ ግን ማብቂያ እንዳላገኘ እየተመለከትን ነው።
የሰውን ተዘዋውሮ ሠርቶ የመኖር መብትን የሚገድብ ይህን መሠል የደኅንነት ሥጋት የሚፈጥር ክስተት መስማት እየተለመደ ቢመጣም፣ ሕብረተሰቡ አንድ ቀን ይሻሻላል በሚል አሁንም ድረስ በመንግሥት ላይ ያሳደረውን ተስፋ ሙሉ በሙሉ አሟጦ አልጨረሰም። ለዚህም ማሳያው አሁንም ድረስ ተፈጸሙ የሚባሉ ግድያዎችንም ሆኑ ጥፋቶችን መንግሥት እንዲያስቆምለት ሕዝቡም ሆኑ ፖለቲከኞች በቻሉት መንገድ ለመማፀንና ለማስገደድ ሲሞክሩ መታየታቸው ነው።
የሠላም ዕጦቱ እያደር አንገብጋቢ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ሌላ የሕዝብን ቁጣ የሚቀሰቅስ ተግባር በቅርቡ በመንግሥት በራሱ ተፈጽሟል። ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር በተገናኘ ተማሪዎች ዕድሜያቸውን ሙሉ የለፉበት የትምህርት ውጤት ሲመክን ዕያዩ ዝምታን በመመምረጥ ተማሪዎች ባክነው እንዲቀሩ የሚያደርግ ኹኔታ መፈጠሩ ብዙዎችን አሳዝኗል። ችግሩ አሁን ውጤት አላግባብ ተበላሽቶበት በተጎዳው ትውልድ ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን፣ ቀጣይ ተፈትነን ዩኒቨርስቲ እንገባለን ብለው በሚማሩ ታዳጊዎች ላይ የሚያስከትለውም ክፉ ተጽዕኖ እንዳለ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአፋጣኝ እንዲስተካከል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
አሁን በርካታ ቅሬታ እየቀረበበት የሚገኘው የፈተና ውጤት የተማሪውን ተስፋ ብቻ ሳይሆን፣ የወላጆች ልፋት መና የሚቀርበትና ትውልድ የሚመክንበትን መንገድን ለወደፊቱም ስለሚቀይስ የተማሪ ስሜት ከመጎዳቱ በላይ፣ በአጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል የማይባል ነው።
“የገነት ዘውዴ” እየተባለ ይታወቅ የነበረው የቀድሞው ሥርዓተ ትምህርት በተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የትምህርት ሥርዓቱና አስተዳደሩ ላይ ያስከተለው ጥቁር ጠባሳ ሳይደበዝዝ አሁን የባሰ አስከፊ ኹኔታ መከሰቱ ሊያሳፍር ይገባል።
የአንድን ታዳጊ ተማሪ የሕይወት አቅጣጫ ሊወስን የሚችል የፈተና ሥርዓት እንዲህ እንደአልባሌ እንካሰላንቲያ ትልቅ ስሕተት ሲፈጠርበት፣ አስቀድሞም ፈተናውን ማንም ሲሰርቀውና የማንም መዘባበቻ ሲሆን ማየቱ እንደአገር ምን ያህል እንደወደቅን የሚያሳይ ነው። ለተከታታይ ዓመታት መቆጣጠር ሳይቻል ቀርቶ በፖለቲካ ጦስ ምክንያት ይሠራጭ የነበረ የተሰረቀ ፈተናና መልሱ አሁንም ድረስ አልቆመም። ይህም በተማሪው ሥነ-ልቦና ላይ የሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ በቀጣይ ማጥናት የሚጠበቅባቸው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ አስተሳሰብ በምንም ነገር ሊመልሱት የማይቻል ነው።
ፈተና ተሰርቆና ብዙዎች በልጠውት እንዲወድቅ የተደረገ ተማሪ ላይ የሚፈጥረው ክፉ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን አገርን የሚጎዳው፣ ሰርቆ እንዳለፈ አውቆት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብቶ ተመርቋል ተብሎ ኃላፊነት የሚሰጠውም ዜጋ ነው። የራስ መተማመን እንዳይኖረው ከማድረጉ ባሻገር፣ ኹሌም ጥገኛና በመስረቅ የሚያምን ዜጋ ሆኖ አገርን እየዘረፈ እንዲያቆረቁዝ ልምድ ይፈጥርለታል። በዚህም ምክንያት አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ ላይ አመኔታ እንዳይኖር ከማድረጉ ባሻገር፣ እሱም በተራው ምሳሌ የሚሆንበት ጊዜን በመፍጠር የቁልቁለት ጉዞውን እንደሚያፋጥን የአዲስ ማለዳ እምነት ነው።
በፊት አገራዊ የሆኑ ‹ማትሪክን› የመሳሰሉ ፈተናዎች እንኳን ሊሰረቁ ይቅርና፣ ተራ የቤት ሥራንም መኮራረጅ አሳፋሪ እንደነበረ የሚያስታውሱት ያውቁታል። እያደር ሰብዕናችን እየተበላሸ አስተሳሰባችን እየቆረቆዘ በመምጣቱ አሁን መሰረቁ ብቻውን ቁጣን መቀስቀስ አልቻለም። እነገሌ ሰርቀው ለጎሳቸው ወይም ለወገናቸው አዳረሱ በሚል፣ ማን ደረሰው ከሚል የመገለል ኹኔታ እንጂ ድርጊቱ በራሱ በጅምላ አለመኮነኑ ምን ያህል ከሰብዕናችን እንደዘቀጥን የሚያሳይ ነው።
ዩኒቨርስቲዎችን ለመቀላቀል የሚያስችል ፈተና ተሰርቆ መልሱ ተሰራጨ መባል ከጀመረ ብዙም አልቆየም። ይህ በግል በተቋሙ ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ መዋቅርን ተከትሎ የሚፈፀም መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ሳይቀር ያምንበታል። የእኔ ክልል የበለጠ ተማሪ ይለፉለት ከሚል የእኩያን አስተሳሰብ በመነጨ ድርጊት ሳቢያ ፈተና ሰርቆ ማውጣትም ሆነ እየመረጡ ማሰራጨቱ አሁን ላይ የሚያሳፍር አልሆነም።
ፈተናውን አግኝተነዋል፤ እንዳናሰራጨው እያሉ ፖለቲከኞች ግባቸውን ማስቆጠሪያ ማድረግ ከጀመሩ አንስቶ፣ ሕብረተሰቡ ከፈተናው ምስጢራዊነት ጋር ተስፋ መቁረጥ ካሳየ ቆይቷል። አሁን አሁን ማን እንደሚያሰራጨው በግልፅ ባታወቅም መዋቅራዊ በሚመስል መልኩ መልስ ተዘጋጅቶለት አብሮ እንደሚሰራጭ ይታወቃል። ይህ ዓይነት ስርቆት አሊያም ዕምነት ማጉደል በማን እንደሚፈፀም መንግሥት በአፋጣኝ አጣርቶ ዕርምጃ ወስዶ ካላስቆመ፣ ውስጥ ደርሶ ውጤትንም ወደመቀየር ላለማደጉ ምንም መተማመኛ ስለማይኖር በአፅንኦት ይታሰብበት ስትል አዲስ ማለዳ ትናገራለች።
በተለያዩ የገጠር ክፍሎች፣ በተለይ በአንድ ስሙን መጥቀስ በማያስፈልግ ክልል የማትሪክ ጥያቄ ወደ አካባቢው ገባ ከመባሉ አንስቶ ውጥረት እንደሚፈጠር የሚያውቁት ይናገራሉ። ችግሩ የሚጀምረው በተማሪዎች ቆስቋሽነት ሳይሆን በወላጆች መሆኑ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል። ይህ መሆን ከጀመረ ዓመታት እንዳስቆጠረ ከወንጀሉ ተጠቃሚ የሆኑትም ጭምር ይመሰክራሉ።
ፈተናው ወደክልሎችና ወረዳዎች እንደተሰራጨ፣ ወላጆች ተሰብስበው ወደሚመለከታቸው ባለሥልጣናትና መምህራን በማምራት የአደራ ልመናቸውን ይጀምራሉ። ልጆቻችን ፈተና ወድቀው ገበሬና ከብት አርቢ ሆነው እንዳይቀሩ ብለው መማፀን ብቻ ሳይሆን፣ ወዮላችሁም በሚል ማስፈራሪያ አዘል ምክር ስለሚሰነዝሩ፣ በተቀናጀ መንገድ ፈተናው ወጥቶ በተመረጡ መምህራን አንዲሠራ ከተደረገ በኋላ ፍጥነት ባለው መንገድ ለታቀደላቸው ተማሪዎች ይሠራጭ ነበር። አሁን አሁን የቴክኖሎጂ መኖር የስርጭቱ አድማስ እንዲሰፋ ከማድረጉ ባሻገር፣ ገደብ ሊበጅለት ስላልተቻለ መንግሥትም ሆነ ሕብረተሰቡ ዘንድ በሠፊው ሊደርስ እንደቻለ ይታወቃል።
ይህን የመሰለ ተያይዞ የመጥፊያ መንገድ በሠፊው ሳይለመድና ሳይንሰራፋ በፊት እንደነበረው አሁን የሚቃወመውም ሆነ የሚፈራ ባለመኖሩ፣ ስለተለመደ ተሰብስቦ መለመንም ሆነ እንደአዲስ ማስፈራራት እንደማያስፈልግ ያጋጠማቸው ተጠቃሚዎችም ሆኑ በሒደቱ የተካፈሉ ምስጢር ብለው ሲናገሩ ይደመጣል። ይህ ዓይነቱ አስነዋሪ ተግባርን የመንግሥት አካላት ስለሚያውቁት ዕርምት ለመውሰድም ሆነ ለማስቆም አለመቻሉን ይናገራሉ።
የዚህ የስርቆት መዘዝም ሆነ ችግር በቀላሉ የሚቀረፍ አይደለም። ተጠቃሚዎቹ ተማሪዎች በዚህ መንገድ አላግባብ አልፈው ዩኒቨርስቲ እንደሚገቡ መተማመናቸው ምንም እንዳያጠኑ ከማድረጉ ባሻገር፣ በዩኒቨርስቲ ሕይወታቸው ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። እዛም ገብተው በተለያየ መንገድ በመደራጀትና ቡድን በመመስረት እንደማትሪኩ ሳያጠኑ እንደሚያልፉ ይሰማል። ለዚህ ዓላማቸው መሳካት ደግሞ በዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ እኩይ ዓላማ ያላቸውና ተማሪን በማንነታቸው ለይተው ለመጥቀም የሚሞክሩ መምህራን መኖራቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል።
በተማሪ ቤት የጀመረ የማጭበርበርም ሆነ አላግባብ የመጠቀም ልምድ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ችግር የሚያስከትለው በሥራውም ዓለም እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በራስ ልፋት አለማደግን እንደልምድ ስለሚወስዱት የሚጠበቅባቸውን አለመስራት ብቻ ሳይሆን፣ የሌላውን ጉልበት በዝብዘው ጭምር በሌላው ላብ ለመኖር ያስባሉ። ያንንም ለማሳካት የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይፈጽሙት አሻጥር አይኖርም።
“እናቴ በመሀረቡ ጊዜ በቀጣሽኝ” የሚል የሚፀፀትም ትውልድ ስለማይኖር ምነው ብንቀጣቸው ብለን ዕድሜ ልካችንን ከመቆጨት ልንድን ይገባል። አሁን ጊዜው ሙሉ በሙሉ ስላልረፈደ፣ የተማሪውም ተስፋ ሙሉ በሙሉ ስላልጨለመ፣ ጭላንጭሉን ፈልገን ወደብርሃኑ አቅጣጫ መሔድ አሊያም ‹አርቲፊሻሉን› ብርሃን በመቀየር እውነተኛው ዓላማ ጋር ለመድረስ መሠራት ይኖርበታል። የታዳጊ ሕልም እንዳይጨነግፍና የወላጆችም ሕልም እንዳይከስም ኹሉም ፍትሐዊ እንዲሆን ትኩረት ይሰጥ ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
በተማሪ እንቅስቃሴና አመጽ ብዙ መከራን ያየች አገር ላይ ተቀምጠን፣ ከሦስት አራተኛው በላይ ተማሪ ተስፋህ ተሟጧል ብለን ሜዳ ላይ እንዲቀር ማድረጉ በሠላማዊ ሠልፍ ብቻ ተቃውሞን አስምቶ የሚቆም ከመሰለን ተሳስተናል። ሥራ የፈታ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ የሚሰፋው ሥራ መፍታት የሚያመጣውን ጉዳት ስለተረዳው እንደሆነ ያልተረዱ ባለሥልጣናትም ሆኑ በዚህ እኩይ ተግባር ላይ እጃቸውን ያስገቡ አካላት ጦሱ ለእነሱም ከመትረፉ በፊት ሊያስቡበት ይገባል።
ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014



