የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለማቀፋዊ ስርጭት

Views: 461

ከቻይናዋ ሁቤ ግዛት ዉሃን ከተማ የተነሳው እና ዓለምን በከፍተኛ ፍጥነት እየዳረሰ የሚገኘው ኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ 19 በሽታ አሁንም ግስጋሴውን አጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። በወረርሽኙ የመጀመሪያዎቹ ቀናት እና ሳምንታት በቻይና እና በጥቂት የሩቅ ምስራቅ አገራት ብቻ ሲስተዋል የነበረው ኮቪድ 19 በአሁኑ ሰዓት አንታርቲካ ሲቀር የስድስቱ አህጉራት የቀን ስጋት የሌት ቅዠት ሆኗል።

ይህንንም ተከትሎ በተለይም ደግሞ በቴክኖሎጂ እና በምጣኔ ኃብት ደረጃቸው ግንባር ቀደምት ነን ያሉት አገራት ላይ ጠንካራ ጉዳት አድርሶባቸው ከፍተኛ ውጥረት እና የዜጎቻቸውን ሞት አስተናግደዋል። በመላው ዓለም ከ1 ሚሊዮን በላይ የተረጋገጡ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች መመዝገባቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን እስካሁን በተደረገው ሒደትም ከ55 ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ ከ220 በላይ ከበሽታው ጋር የነበራቸው ትንቅንቅ በድል ተደምድሞ አገግመው ወጥተዋል።

በአሁኑ ሰዓት ቀዳሚ የህመምተኞች ቁጥር የተመዘገበባት አሜሪካ ስትሆን ይህ ጽሁፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ245ሺሕ 4 መቶ በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ ተጠቅተው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ እስካሁን ድረስ በአሜሪካ 6 ሺህ 98 ሰዎች ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በቀጣይ በርካታ ዜጎቿ በቫይረሱ የተጠቁባት አገር ስፔን ስትሆን 117ሺህ 7 መቶ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ 10 ሺሕ ዜጎችም ሕይወታቸው አልፏል። ቫይረሱ በአሰቃቂ ሁኔታ የጎዳት አውሮፓዊቷ አገር ኢጣልያ 115 ሺሕ በላይ ዜጎቿ በበሽታው የተያዙ ሲሆን ይህም ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደትቀመጥ አድርጓታል። በኢጣልያ የተመዘገበው ሞት ግን ከኹሉም የላቀ በመሆን 13 ሺህ 9 መቶ በላይ ሆኗል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ እስከ ሦስት ያሉትን አየን እንጂ ወረርሽኙ በአፍሪካም ገብቶ የዜጎችን ሕይወት አጥፍቷል። በርካቶችም በበሽታው ተይዘው ተገልለው እንዲቀመጡ እና በጽኑ የህሙማን እንክብካቤ እንዲቆዩም አድርጓል። በዚህም ሳቢያ ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ደቡብ አፍሪካ አልጀሪያ እና ሞሮኮ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይይዛሉ። በአፍሪካ 7ሺሕ 80 የተረጋገጡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ50 አገራት ላይ የተመዘገበ ሲሆን 290 የሞት ቁጥርም ተመዝግቧል።

ከአንድ እስከ ሦሰት ከፍተኛ የሕመምተኞች ቁጥር የተመዘገበባቸው አገራት ደቡብ አፍሪካ 1 ሺህ 4 መቶ 65 ሰዎች የተያዙ ሲሆን (ይህ ጽሑፍ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) በአልጀሪያ ደግሞ 986 ሰዎች ተይዘዋል። በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠችው ሞሮኮ 735 ዜጎቿ በበሽታው መያዛቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።
በአገራችን በኢትዮጵያም ዐርብ መጋቢት 25 በጤና ሚኒስቴር ይፋ በተደረገው ሪፖርት መሰረት ባለፈው 24 ሰዓት የቫይረሱ ተጠቂዎች እስከዛሬ በአንድ ቀን ከታዩት ቁጥር ከፍ በማለት ስድስት ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው እና ጠቅላላ የተያዙ ሰዎችንም ቁጥር ወደ 35 ከፍ እንዳደረገው ተጠቅሷል።

በየጊዜው በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ሰዓት ጀምሮ መንግሥት በርካታ ጥንቃቄዎችን ሕዝቡ እንዲከተል በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን፣ የንጽሕና አጠባበቅ እንዲሁም ማኅበራዊ ፈቀቅታውን እንዲጠብቅ አበክሮ ሲያስገነዝብ ቆይቷል፤ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ቫይረሱ ኢትዮጵያ ከከተመበት ከሦስት ሳምንታት ወዲህ ሐሙስ መጋቢት 24 ሦስት ሰዎች ማገገማቸው ተገልጿል።

በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከሚሊዮን በላይ በሔደበት በዚህ ወቅት ቫይረሱ 200 አገሮች ውስጥ ተሰራጭቶ የሚገኝ ሲሆን ከፍተኛ የተረጋገጠ የቫይረሱ ተጠቂነት እና ሞት የታየባቸው በጣት የሚቆጠሩ አገራት ናቸው፡፡ እንደ ቻይና፣ ጣልያን እና ስፔን ያሉ አገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን አጥተውም ቢሆን ክፉው ቀን ከኋላቸው እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋባት የምትገኘው አሜሪካ ደግሞ የመስፋፋቱ ጫፍ ላይ ለመድረስ እስከ ሁለት ሳምንት እንደሚቀራት ይጠበቃል፡፡ ይህም ማለት ቢያንስ እስከዛው ድረስ የሚያዘው እና የሚሞተው ሰው ቁጥር እያሻቀበ ይሔዳል ማለት ነው፡፡ የዓለም ኋያሏ አገርም ከ100 ሺህ እስከ 240 ሺህ የሚሆኑ ዜጎቿን በበሽታው ልታጣ እንደምትችል ግምቷን አስቀምጣለች፡፡

በአፍሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የቫይረሱ ስርጭት እንደ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና ምስራቅ እሲያ አይደለም፡፡ በአንዳንዶቹ የአፍሪካ አገሮች እንደውም ከውጭ የመጡ ሰዎች ቫይረሱን የሚያስገቡበት የመጀመሪያው ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የቫይረሱ ስርጭት ባደጉት አገራት ያሳየውን ዓይነት ዑደት የሚከተል ከሆነ እና ነገሮች ያንን ያህል የሚከፉ ከሆነ እስከ አሁን ብዙም ያልተጠቁት ድሃ የዓለም ክፍሎች ያላቸውን የሕክምና ስርዓት ግምት ውስጥ በማስገባት ሌሎች ሚሊዮኖች በዓለም ዙሪያ ሊጠቁ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com