ሐሙስ መጋቢት 22 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቀድሞ የኦነግ ሊቀመንበር ገላሣ ዲልቦ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ገላሣን ያጣናቸው ይበልጥ በሚያስፈልጉን ጊዜ ነው” ብለዋል።
ገላሳ ዲልቦ ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት እና እኩልነት መታገላቸውንም አንስተዋል።
በተለይም ሶማሌ በነበራቸው የትግል ቆይታ ብዙ መከራ እና ችግር እንዳሳለፉ አጫውተዋቸው እንደነበርም ገልፀዋል።
“በቅርቡ በለውጡ አመራር በተደረገላቸው ግብዣ የሰላማዊ ትግል ጉዞ መርጠው ወደ አገራቸው ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ መታገል ከመጀመራቸውም ባሻገር በ2013 ምርጫ በግል ተወዳድረው የፓርላማ አባል ለመሆንም ችለዋል።” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
አክለውም፤ በትግል ውጣ ውረድ ውስጥ የገጠማቸውን በጎ እና ክፉ ለማሄስ እና ወጣቶች ከኹለቱም እንዲማሩ ለማድረግ ይተጉ እንደነበርም ገልፀዋል።
“ገላሳ ዝምተኛ፣ አስተዋይ፣ ምክንያታዊ እና ለሰላማዊ ንግግር እጅግ የሚያመች ሰብእና የተላበሱ ግለሰብ ነበሩ።” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ገላሳን ያጣናቸው ይበልጥ በሚያስፈልጉን ጊዜ ነው። ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር።” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




