አራጣ አበዳሪው በይቅርታ ተፈቱ

0
940

• ከበደ ተሰራ 15 ዓመት የእስር ጊዜያት እየቀራቸው መፈታታቸው ቅሬታ አስነስቷል

በአራጣ ፣ ግብር ስወራ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ በማቅረብ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተከሰው በፍርድ ቤት 25 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ከበደ ተሰራ በይቅርታ መፈታታቸው ተሰማ።

አዲስ ማለዳ ከዐቃቤ ሕግ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው ሐሙስ፣ የካቲት 14/2011 ለቃል ክርክር ቀጠሮ እያላቸው ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ከእስር ከተለቀቁ አንድ ወር እንደሞላቸው ጠበቃቸው ለፍርድ ቤቱ ማሳወቃቸውን እና ፍርድ ቤቱም ይቅርታውን ማፅናቱን ለመረዳት ተችሏል።

በመረጃው መሰረት ከበደ ተሰራ የተከሰሱባቸው ወንጀሎች በተለይ ከአራጣ ጋር በተያያዘ የጌታነህ ትሬዲንግ ባለቤት ዩሐንስ ጌታነህ ራሳቸውን እንዲያጠፉ ምክንያት እንደሆኑና በርካታ ንብረቶቻቸው በሕገ ወጥ መንገድ በከበደ ተሰራ እንዲወረስ መሆኑ በራሱ ይቅርታ የሚያሰጥ ጉዳይ እንዳልሆነ ያብራራል። በዚህም ምክንያት የሟች ዩሐንስ ጌታነህ ቤተሰቦች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ባለድርሻነት ፍርድ ቤቱ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደነበረበት የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ዐቃቤ ሕግ እንደተቃውሞ የሚያነሳው ከበደ ተሰራ የተፈረደባቸውን የእስር ጊዜ 2/3ኛ የሚሆነውን ያልታሰሩ በመሆኑ የይቅርታ ሕጉ አይመለከታቸውም ብሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ቢያንስ 16 ዓመታትን በእስር ማሳለፍ እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል።

ከበደ ተሰራ በተከሰሱባቸው ክሶች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በድምሩ የ41 ዓመታት እስር የሚያስፈርድባቸው ቢሆንም በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት የእስር ጊዜ ጣራው 25 ዓመት በመሆኑ 25 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር ። ይሁን እንጂ የተሻሻለውን የግብር ሕግ ጋር ተያይዞ ቅጣቴ ይቅለልልኝ በሚል ያቀረቡት አቤቱታ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ በነበረበት ወቅት ፤ በጊዜው በነበሩት ርዕሰ ብሔር ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ለ92 ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ይቅርታ ቦርዱ ካቀረባቸው ታራሚዎች ውስጥ ከበደ ተሰራ ተካተውበት ነበር። በዚህም ምክንያት ከ9 ዓመታት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ በ2009 ከእስር ሊፈቱ እንደቻሉ የሚታወስ ነው።

በወቅቱ ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞውን በደብዳቤ በዝርዝር ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አሰምቶ ነበር። ታራሚው የተከሰሱበት ወንጀል የይቅርታ አዋጁ 840/2004 ውስጥ እንደማይካተት፣ ጉዳዩም ገና በእንጥልጥል ላይ በመሆኑ እና 2/3ኛ የፍርድ ጊዜውን ባለመፈፀማቸው በይቅርታ ሊፈቱ አይገባም በሚል የተቃውሞ ድምጽ ማሰማቱ ይታወሳል። ተቃውሞውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የቀረበልኝ የታክስ ስወራ ወንጀል ብቻ ነው፤ የተሳሳተ እና ያልተሟላ መረጃ ነው የደረሰኝ በማለት ያለአግባብ ተፈተዋል በሚል እንደገና ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ ተደርገው ነበር ።

በወቅቱም ተከሳሹ በፍርድ ቤት ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው በሥማቸው የተመዘገበው ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሕንፃን ጨምሮ ተሽከርካሪዎች፣ የአክሲዎን ድርሻዎችና በሥማቸው በባንክ የተቀመጠ 2 ሚሊዮን ብር እንዲወረስ መደረጉን አዲስ ማለዳ ከዐቃቤ ሕግ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

አዲስ ማለዳ ከዐቃቤ ሕግ ምንጮቿ ያገኘቸውን መረጃ በመያዝ ወደ ከበደ ተሰራ አንደኛው ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ጋር በመደወል መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here