የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች የተጨፈጨፉባቸው በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸው ተገለፀ

0
1478

ሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2014 የህወሃት ቡድን ከ1975 ጀምሮ በርካታ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ላይ የዘር ፍጅት የፈጸመበት “ሀለዋ ወያነ” በመባል የሚታወቁ የጅምላ እስር እና የጅምላ ቀብር የሚፈጸምባቸው ቦታዎችን ማግኘቱን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን አስታወቀ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ በርካታ የቡድኑ የጉድጓድና የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶች ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ከተጠቆሙት የጅምላ መቃብሮች መካከል ለሙከራ አምስቱን አስቆፍሮ ጭካኔ በተሞላበት ግፍ የተረሸኑ ንጹሃንን አፅም አስወጥቷል።

አካባቢውን የጀርመኑ ናዚ 1 ሚሊዮን 4 መቶ ሺ በላይ እስራኤላውያንን ከጨፈጨፈበት “ኦሽዊዝ” የተባለ ማጎሪያ ጋር አነጻጽረው “የኢትዮጵያው ኦሽዊዝ” ሲሉ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አባላት፤ “ገሃነም” በተባለው የትህነግ የድብቅ እስር ቤት በርካታ ሺህ ንጹሃን ማለቃቸውን በወቅቱ በእስር ላይ የነበሩና ከሞት የተረፉ የወራሪ ቡድኑ የጥቃት ሰለባዎችን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።

ህወሃት ይህን ድብቅ እስር ቤት የመረጠበት ምክንያት አካባቢው ሰው ከሚኖርበት ርቆ የሚገኝ ዙሪያው በከፍተኛ ሰንሰለታማ ተራራ የተከበበ ከመሆኑም ባሻገር በኃይል ይዟቸው የነበሩትን የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች አማካኝ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከሁሉም አካባቢዎች ንጹሃንን እያፈነ ወስዶ ለማጎርና ለመጨፍጨፍ ምቹ በመሆኑ ነው ተብሏል።

በዚህ አሰቃቂ እስር ቤት የታሰሩ ንጹሃን በሚደርስባቸው ሰቆቃ ምክንያት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን፣ የቡድኑ ታጣቂዎች በየቀኑ ታሳሪዎችን እየወሰዱ ይገድሉ እንደነበርና የብዙዎቹ አስከሬን በአካባቢው የሚገኝ ቃሌማ ወንዝ ላይ ይጣል እንደነበር ከሞት የተረፉት አዛውንቶች ለጥናት ቡድኑ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የድብቅ እስር ቤቱ ውስጥ በበሽታና በርሃብ፣ በድብደባ ተሰቃይተው እንዲሁም በቡድኑ ታጣቂዎች ለሚገደሉት እስረኞች ቀብር ይቆፍሩ የነበሩት እስረኞች እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም የአካባቢው ተወላጆች ወንጀሉ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ይፈጸም እንደነበር ለጥናት ቡድኑ አስረድተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ለረዥም ጊዜ መረጃ ከሰበሰበ በኋላ ገሃነም በተባለ አካባቢ በሚገኙ በርካታ እስር ቤቶች ጭፍጨፋ ከተፈጸመባቸው መካከል የተወሰኑት ሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሟች ቤተሰቦችና የአካባቢው ፀጥታ ኃላፊዎች በተገኙበት አፅማቸው እንዲወጣ መደረጉን ከአማራ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የጅምላ መቃብሮች በመቆፈር የወጣው የንጹሃን አፅም መጋቢት 21 ቀን 2014 አዲስ ዓለም ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተቀበረ ሲሆን፤ በአካባቢው ካሉት በርካታ ድብቅ እስር ቤቶችና የጅምላ መቃብሮች በቀጣይ የበርካታ ንጹሃን አፅምን ለማውጣት እቅድ መያዙም ተገልጿል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን “ገሃነም” በተሰኘው አካባቢ በነበሩት ድብቅ እስር ቤቶች የተፈፀመውን ጨምሮ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ላይ የተፈፀመውን የዘር ፍጅት ወንጀል የሚያሳይ መረጃ አሰናድቶ ለማቅረብ በመሥራት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here