የወልዲያ ሃራ ገበያ-መቀሌ የባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ተቋረጠ

0
502

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባጋጠመው የበጀት እጥረት የወልዲያ ሃራ ገበያ – መቀሌ የባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ተቋረጠ።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከሚያስገነባቸው የባቡር መስመር ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የወልዲያ ሃራ ገበያ-መቀሌ የባቡር መስመር ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት በአንድ ነጥብ 54 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት መጀመሩን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው 53 ነጥብ ስምንት በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪውን ግንባታ ለማከናወን የበጀት እጥረት በማጋጠሙ የፕሮጀክቱ ሥራ በአብዛኛው መቋረጡ ነው የተነገረው።

ፕሮጀክቱ ሲጀመር 40 በመቶ በመንግሥት 60 በመቶው ደግሞ ከውጭ በሚገኝ የገንዘብ ብድር ወጪ ይሸፈናል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ይገኛል ተብሎ የታሰበው ብድር ማግኘት እንዳልተቻለ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ደረጀ ተፈራ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የተሠራው ሥራም ወጪው በመንግሥት የተሸፈነ ነው ተብሏል።

አሁን ላይ ምን እየተሠራ ነው? ስትል አዲስ ማለዳ ላሰነሳችው ጥያቄ፣ ‹‹አዝጋሚ በሚባል መልኩ ተገጣጣሚ ድልድይ እየተሠራ ነው›› ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ‹‹ይህ ማለት ግን ሥራው እየተሠራ ነው ማለት አይደለም›› ብለዋል።

የተጠበቀው ገንዘብ ባለመገኘቱ እና አገሪቱ ባለባት የብድር ጫና ምክንያት ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዳልተቻለ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ያጋጠመው የበጀት እጥረት በኮርፖሬሽኑ አቅም የሚፈታ አለመሆኑን ያስታወሱት ደረጀ፣ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያስቀምጥም ጠይቀዋል። የፕሮጀክቱ አለመጠናቀቅ ጊዜው በገፋ ቁጥርም የተገነባውን በጊዜ ቆይታ ብዛት እንዲፈርስ ሊያደርግ ስለሚችል ትኩረት እንዲሰጠውም ኮርፖሬሽኑ ጠይቋል። ይህ ደግሞ ሌላ ወጪ እና ኪሳራ መሆኑን ያስገነዘበው ኮርፖሬሽ ‹‹የተጀመሩት ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ለውጤት መብቃት አለባቸው›› ም ብሏል።

የበጀት እጥረት የሚፈትነው ይህ ፕሮጀክት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለውን ኮርፖሬሽኑ እስካሁን አለማወቁን ጠቅሶ የመንግሥት ውሳኔን እንደሚፈልግ አሳውቋል ።
ፕሮጀክት በ2007 ወደ ሥራ ሲገባ አራት ሺሕ ሰራኞች ነበሩት ያሉት ደረጀ አሁን ላይ ሥራው በአብዛኛው እየተቋረጠ መምጣቱን ተከትሎ የሰራተኞቹ ቁጥር ወደ 900 አሽቆልቁሏል ነው የተባለው።

216 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውና የአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎችን ያገናኛል ተብሎ የታቀደው ይህ ፕሮጀክት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የካቲት 11/2007 የመሠረት ድንጋይ እንደተቀመጠለት ይታወሳል። በሦስት ዓመት ተኩል ይጠናቀቃልም ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
76 ድልድዮችንና 10 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ዘጠኝ ዋሻዎችን ያካተተው ፕሮጀክቱ ለሕዝብ ጭነት በሰዓት 120፣ ለዕቃ ጭነት ደግሞ 80 ኪሎ ሜትር እንዲያስኬድ ተደርጎ እንዲገነባም እቅድ ተይዞለት ነበር። የባቡሩ አጠቃላይ እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ዋና ጣቢያ መቀሌ ሲሆን በቆቦ፣ አላማጣ፣ መኾኒ እና አዲ ጉደም ተጨማሪና መለስተና አራ ጣቢያዎች እንደሚኖሩት በእቅድ ተይዟል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 18 ባቡሮችን ያሰማራል የተባለ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አራቱ እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ አንድ ሺሕ 416 ሰዎችን መጫን የሚችሉ ሕዝብ አመላላሽ ይሆናሉ። 14ቱ ደግሞ ዕቃ ጫኝ ባቡሮች እንደሚሆኑም እቅድ ወጥቶ ነበር።

‹‹የልማት ማዕከላትን የሚያስተሳስር ከጎረቤት አገራትና ወደቦች ጋር የሚያገናኝ የባቡር መሠረተ ልማት ተዘርግቶና ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በአገሪቱ ተስፋፍቶ ማየት›› የሚል ራዕይ ያነገበው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሥራው በበጀት እጥረት እየተፈተነበት ነው።

በተያያዘ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕዳ አለባቸው ከሚባሉት ከፍተኛ ከመንግሥት ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንደሆነ ይነገራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here