ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2014 በዋለው ችሎት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቅ ውሳኔ አሳልፏል።
የተራራ ኔትዎርክ በይነ-መረብ መገናኛ ብዙሃን ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከታሰረ ዛሬ መቶ 117 ቀናት ሲሆን፤ ክስ ሳይመሰረትበትና የዋስ ይግባኝ ጥያቄውም በጊዜ ቀጠሮ እየተላለፈ ዉሳኔ ሳያገኝ እስከ ዛሬ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ጋዜጠኛው መጋቢት 1 ቀን 2014 በገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት፣ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ አቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ጋዜጠኛው ላይ ክስ እንዲመሰርት ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ጋዜጠኛው በጠበቃው በኩል መጋቢት 02 ቀን 2014 በዋስ እንዲለቀቅ የሚጠይቅ የዋስ መዝገብ ከፍቶ ነበር፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዋስ መዝገቡን ከተመለከተ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ለመጋቢት 08, 13, 15, 20 እና 27 ተለዋጭ ቀጠሮ እየሰጠ ቆይቷል።
በመጨረሻም ዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2014 በዋለው ችሎት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጋዜጠኛው የዋስትና መብት እንዲከበርለት ውሳኔ ማሳለፉን የተራራ ኔትዎርክ ዘግቧል።
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ታህሳስ 01/2014 ከጠዋቱ 4:30 ገደማ ወደ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ በመወሰድ በቁጥጥር ሥር መዋሉ የሚታወስ ሲሆን፤ ከአዲስአበባ ፖሊስ ተላልፎ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንደታሰረም ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



