ኢትዮጵያ በሺሕ የሚቆጠሩ ዓመታት ታሪክ ያላት አገር ናት። የጥንቷም ሆነ የዘመናዊቷ ታሪክ እና ቅርስ በዜግነታችን የሁላችንም ሀብት እና ንብርት ነው። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የካቲት 23/1888 ታላቅ ትርጉም ያለው ዓመት ነው። ኢትዮጵያውያን ቅድም አያቶቻችን ብዝኀነታቸውን በአንድነት አስተሳስረው ከዛ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሙሉ በአንድነት እና በጋራ የተሳተፉበት የአገር እና የነጻነት መከላከል እርምጃ የተወሰደበት ወቅት ነው። ይህ ወቅት ኢትዮጵያ ራሷን ከጥቃት ተከላልላ እንደ አገር ክብሯን እና ነጻነቷን አስከብራ መቆቀም መቻልዋን ያስመሰከረችበት አኩሪ ታሪክ ነው። ነፃነት በነፃ የሚገኝ ገጸ በረከት እንዳልሆነና መስዕዋትነት የሚጠይቅ መሆኑም የተመሰከረበት ድል ነው።
የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን የቅኝ ገዢነት ህልም ቅዥት ማድረጉ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ድንበር ሳይታጠር በመላው ዓለም ለሚኖሩ ጭቁን ሕዝቦች በተለይ ጥቁር ሕዝቦች የሰብኣዊ ክብራቸውን ያስመለሰ ትዕምርታዊ ፍይዳ ያለው ድል ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ግዛቶች መሳፍንት እና ባላበቶች በየአካባቢው የበላይነትን ለማግኘት ሲሉ ያደርጓቸው የነበሩ የውስጥ ግጭቶች እና ጦርነቶች በዳግማዊ አፄ ምኒልክ አሸናፊነት አብቅተው፥ ሁሉም በጋራ ባህር አቋርጦ የመጣን ጠላት ለመመከት በአንድነት የተሳተፉበት፣ በጋራም ድል የተቀዳጁበት ነው። ይህ የጋራ ድል በአገር ውስጥ የነበረውን የክልልና የብሔርተኝነት ስሜቶች በማዳከም፣ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ በጋራ ድል አድራጊነታቸው ከጎጥ እና ከጎሳ ስሜቶች በላይ ተሸግረው በኢትዮጵያዊ አርበኝነት እና አገራዊ ፍቅር እንዲነከሩ ያደረገ ነበር። በመሳፍንቱ መሃል የነበረው፥ ‘እኛና እነሱ’ የሚለው የውስጥ የግዛት የስሜት ልዩነት ጠብቦ፣ እራሳቸውን በአዲሱ ‘የእኛና የእነርሱ’ የልዩነት ስሜት ውስጥ ያገኙት ነው። ‘እኛ’ ኢትዮጵያውያን ‘እነሱ’ ነጮች፣ ሶላቶች፣ ጣሊያኖች፣ አረቦች እና ወዘተ በሚለው ልዩነት የኢትዮጵያውያን ልዩነት የማንነት መግለጫ ሆኖ ሥር የሰደደ የታሪክ መታጠፊያ ወቅት እንደነበር ተዘግቧል።
ኢትዮጵያን ከውጪ ወራሪ በመከላከል ረገድ የምናሳየውን ያክል ትብብርና መደጋገፍ በውስጥ ፖለቲካቸው ላይ ብዙ አይንጸባረቅም። በተለያዩ ጊዜያት የተገኙ መልካም አጋጣሚዎችን ወደ ተሻለ ዕድል ከመለወጥ ይልቅ ሲከሽፍ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ዕድሎችን የማባከንም ሆነ ካመለጡ በኋላ በቁጭት ከመብሰልሰል ይልቅ የዕጣ ፈንታችንን ወሳኞች እኛው ራሳችን ስለሆን በጥበብ የሚፈለው ውጤት ላይ መድረስ ይገባናል። አሁን የሽግግር በሚመስለው የአገራችን ለውጥ ጅማሮ ሒደት ውስጥ አንዱ የሌላውን ኅልውና መቀበልና እርስ በእርስ በመነጋገር የጋራ ራዕይ ላይ መሥራት ይጠበቃል።
በተለያዩ የአገራችን ስብስቦችና ማኅበረሰባዊ ኃይሎች መካከል ልዩነቶች ለማስተናገድ በመፈክር ‘ልዩነቶታችን ውበቶቻችን ናቸው’ እንደምንለው በተግባርም ጌጥና ውበት እንደሆኑ ማድረግ መቻሉ የግድ ነው። ለብሔራዊ መግባባትም የሚበጀን በትናንቱ ላይ በመቆዘም፣ ባለፉት ከመቆጨት የነገውን ቅርፅና ይዘት አንድ ላይ ሆነን ዛሬ ለመንደፍ እንቀራረብ፣ እንወያይ የሚለውን ጥሪ መቀበል ነው።
ልዩነትን ለማረቅ ደግሞ የዜግነት መብቶች መክበር አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ እስከመወሰን ይደርሳል። አዲስ ማለዳ የጋራ አገራችን አንድትቀጥል ቁርጠኛ አቋም እስካለ ድረስ የመብቶቹ መከበር አስፈላጊነት ችላ ሊባል የሚገባው አይደለምም ትላለች።
አዲስ ማለዳ ከአንድ ዕውቅ ኢትዮጵያ ፀሐፊ የተዋሰችው ቋንቋ ተጠቅማ የዜግነት መብት ማዕከል ያደረገው አሰባሰቢ ማንነት ብቻ ነው ትላለች። የዜግነት መብት አነታራኪ የሆኑ የቅርንጫፍ ማንነቶችን ሁሉ አዋሕዶ ሊያስተሳስረን ብቃት ስላለው ነው፤ የሚያለያየን ሳይሆን የሚያስተሳስረንና የሚያሰባስበን እንሻለን።
የአድዋን ድል ትዕምርት በመጠቀም ኢትዮጵያውያንን ወደ እርስ በእርስ መናቆርና መጠፋፋት ሊያመራ የሚችለውን የአለመረጋጋት ምክንያት ማስወገድ ይገባል። ለመኗኗር መረጋጋት ያስፈልጋል፤ ይቀድማልም። ብሔራዊ መግባበት ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ሰላም ያስፈልገናል።
የአድዋን ድል በማክበር ብቻ ማሳለፍ የድሉን ውጤት ማሳነስ ስለሚሆን የአድዋን እሴቶች ማለትም ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ማጠናከር፣ አንድነት ማጎልበት እና ሉዓላዊነት መጠበቅ ያስፈልጋል። አንድነት ሲባል ግን አንድ ዓይነትነት ለማለት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011