በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻይዝድ ሆስፒታል ከፍተኛ የመድኀኒቶች እጥረት እንዳጋጠመውና የታካሚዎቹ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።
በአገራችን ካሉ ጥቂት አንጋፋ የሕክምና ተቋማት መካከል ግንባር ቀደም እና በሚሠጠው የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት የሚታወቀው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፥ መድሃኒቶቹ በአገሪቷ ባሉ አቅራቢዎች እጅ አለመገኘቱ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ እንዳደረገው ገልጿል።
በሆስፒታሉ የማኅበረሰብ ፋርማሲ ኃላፊ የሆኑት አበራ ገላን እንደገለጹት የኢትዮጵያ መድኀኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ በሰዓቱ መድኀኒቶችን እንዳቀረበላቸው እና በዚህም የተነሳ ከፍተኛ እጥረት አንዳለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ታካሚው ይታዘዝለታል፣ ያጣል፣ ይንከራተታል፤ የትም ቢሔድ ከተቋሙ ውጭ ሊያገኝ አይችልም፤ አማራጭም የለውም›› ሲሉም ተናግረዋል።
‹‹በብዛት መድኀኒቶቹ ከውጭ የሚመጡ ሲሆን የዶላር እጥረት እና በጉምሩክ ሒደት አማካኝነት ይቆያል›› ሲሉ አክለዋል።
“ከአገር ውስጥ መድኀኒት አምራች ድርጅቶች ለምን አትጠቀሙም?” ብላ አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ ኃላፊው ምላሽ ሲሰጡ “የአገር ውስጥ መድኀኒት አምራቾች በምናወጣው ጨረታ ላይ መሳተፍ አይፈልጉም” ብለዋል።
‹‹በአገሪቱ የሚመረቱ መድኀኒቶች ግዢ የሚፈፀም ሲሆን ይህም የሚሆነው በጨረታ ነው ፤ ነገር ግን ጨረታም ወጥቶ የአገር ውስጥ መድኀኒት አምራቾች መሳተፍ አይፈልጉም፤ ምክንያቱም ገንዘብ እጅ በእጅ እንጂ የዱቤ አገልግሎት መስጠትን አይፈልጉም›› ብለዋል።
የፌዴራል መድኀኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አድና በሬን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም።
በሌላ በኩል፤ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተገልገይ በኩል ተያያዥ ቅሬታዎችም ቀርበዋል። የመድኀኒት አቅርቦት እጥረትን ጨምሮ የቀጠሮ ርዝመት፣ የአልጋ ዕጥረት የመሳሰሉት ችግሮች እንዳሉ ተገልጋዮች እና ሠራተኞች ይገልፃሉ።
በዚህም ምክንያት ታካሚዎች ከተለያዩ ከተሞች በመምጣት ለእንግልት ተጋልጠዋል። በወረፋ መጠበቅ ምክንያት ታካሚና አስታማሚ ለእንግልት ዳርጓቸዋል። ለዚህም ምክንያት የተቋሙ ሠራተኞች የተለያዩ ሐሳቦችን ይሠነዝራሉ።
በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አብይ የኔአለም እንደገለፁት፤ ይህ የተከሰተው ተቋሙ በአገራችን ብቸኛ በመሆኑ ብዙ ታካሚዎች ያሉት በመሆኑና የአዕምሮ መመርመሪያ ማሽን ‘ኢኢጂ’ (Electroencephalography) እጥረት መኖሩ ነው።
አማኑኤል የአዕምሮ ሕክምና ተቋም አንድ የመመርመሪያ ማሽን የነበረው ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስቴር ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አማካኝነት አራት ‘ኢኢጂ’ ማሽን እና ኹለት አልጋ በልገሳ ለተቋሙ ሰጥተዋል ያሉን አብይ አክለውም ወረፋው የሚበዛው ታካሚዎቹ ስለሚያስቸግሩ ኹለት ወይም ሦስት ሰው በላይ ተይዘው ስለሚመጡ ከታካሚው ይልቅ የአስታማሚው ብዛት ወረፋ እንደሚመስል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተቋሙ የ‘ኢኢጂ’ ማሽን ለመመልከት ወደ Neuro-epilepsy case ክፍል በገባንበት ወቅት በተቋሙ እየሠራ ያለው ብቸኛ ማሽን በመስራት ላይ አንደሆነ ታካሚው እየተመረመረበት እንደነበር ለማየት ችለናል።
በአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጭንቅላት ምርመራ ‘ኢኢጂ’ ሕክምና የሚሠጠው ዕድሜያቸው ከ7 ዓመት በላይ ለሆኑ ታካሚዎች ሲሆን ባለው የግብዓት እጥረት ችግር ምክንያት በአሁኑ ጊዜ አገልግሎቱን ለሕፃናት እየተሰጠ እንዳልሆነ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በዚህ ዓመት ለተቋሙ የተፈቀደው በጀት 197 ነጥብ 2 ሚሊየን ሲሆን ይህ በቂ አይደለም ሲሉ አብይ ይገልፃሉ። የታካሚዎችን ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት ተግዳሮትም እንደሆነባቸው ገልፀዋል። በተቋሙ ያሉ ታካሚዎች ብዛት በዝርዝር ሲያስረዱ ተመላላሽ አዲስ ታካሚ በቀን 50፣ ተመላሽ ቀጠሮ ያላቸው ከ400 በላይ ይኖራሉ ብለዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011