የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መስከረም 4/2011 በቡራዩ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት በተሳታፊነት ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ የሕግ ድጋፍ የለውም በማለት ውድቅ አደረገው።
ከመስከረም 2 እስከ 7/2011 በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማና አካባቢው፣ ተከስቶ በነበረው ኹከትና ብጥብጥ በሰዎች ሞት፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች፣ ከትላንት በስቲያ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረቡትን መቃወሚያ አስመልክቶ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ ነበር። በዚህም ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን የክስ መቃወሚያ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከጥቅምት 20/2011 ጀምሮ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት እየቀረበ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ በተያዙባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ቀርበው በተጠረጠሩበት ‹‹ኹከት፣ ረብሻና ግድያ›› ወንጀሎች ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠየቅባቸው ቆይተዋል። የምርመራ ሒደቱም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሲካሄድ ቆይቷል። ነገር ግን የምርመራው አካል የሆነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የምርመራ ሒደቱና እየተገኙ ያሉ ማስረጃዎች በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (3) ሥር የሚካተቱ በመሆናቸው፣ የምርመራ ሒደቱ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተዛውሮ መቀጠል እንዳለበት ውሳኔ መስጠቱን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱ ይታወቃል።
ችሎቱ በዕለቱ የተከሳሾችን የዕምነት ክህደት ቃል የተቀበለ ሲሆን፣ ሁሉም ‹‹ጥፋተኛ አይደለሁም›› ሲሉ ተከራክረዋል። ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ‹‹ተከሳሾቹ ጥፋተኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥልኝ የሰውና የድምጽ ማስረጃ ያለኝ በመሆኑ፣ በቅድሚያ ይህ እዲታይልኝ›› ሲል ጠይቋል። ዐቃቤ ሕግ በቅድሚያ ያልተያዙ ተከሳሾችን ይዤ እንዳቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮም ይሰጠኝ ብሎ በጠየቀው መሰረት፣ ፍርድ ቤቱ ለመጋቢት 9/2011 ቀጠሮ ሰጥቷል።
በተጨማሪ፣ በዚሁ መዝገብ 12ኛ ተከሳሽ የሆኑ ግለሰብ፣ በከፍተኛ የወገብ ሕመም እየተሰቃዩ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ተገቢው ሕክምና እየተደረገልኝ አይደለም፤ ዶክተሮቹ ከአቅማችን በላይ ነው ቢሉኝም፣ ማረሚያ ቤቱ ግን ድጋፍ እያደረገልኝ አይገኝም›› በሚል ባቀረቡት ክስ መሰረት፣ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱ ተወካይ መጥቶ እንዲያስረዳ አዟል። በዚህም ተወካይዋ ተገኝተው ተከሳሽ የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንና ከሕክምና ባለሙያዎች ቀበቶ (ቤልት) አዘውላቸው፣ በበጀት እጥረት ምክንያት ሳይገዛ ቢቆይም፣ አሁን ግን ከሌላ በጀት ላይ ተነስቶ ግዥ እንደተፈጸመ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱም ማረሚያ ቤቱ ለተከሳሽ ድጋፍ እንዲያደርግ ብሏል።
በተያያዘ የችሎት ውሎ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት እና በሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ተጠርጥረው የቀረቡ ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ተከሳሾቹ፣ ‹‹ጉዳያችን እየተጓተተ ነው፤ ማስረጃ እናቅርብ በሚሉ ሰበቦች በየጊዜው ቀጠሮ እየተሰጠን፣ ያለምንም ፋይዳ እየተመላለስን ነው፤ ከዚህ በፊት የቀረቡት ማስረጃዎች ብይን ለመስጠት በቂ ናቸው›› ሲሉ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 28/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011