የሃይማኖት ተቋማት መሬት እንዲያገኙ የሚያስችል መመሪያ ያለመኖር ክፍተት ፈጥሯል ተባለ

0
627

የሃይማኖት ተቋማት በምን ዓይነት ሁኔታና ስታንዳርድ መሬቱን ማግኘት እንዳለባቸው የሚገልፅ የአሰራር መመሪያም ሆነ ማንዋል ያለመኖር፣ የአሰራር ክፍተት መፍጠሩን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተናግሯል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የመሬት ዝግጅት የሥራ ሒደት የሥራ ማንዋል የሌላቸው መሆኑ፣ ሌላው የአሰራር ክፍተት መሆኑን ነው የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዘውዱ ወንድም፣ የ2011 የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን መሰረት አድርገው ለዝግጅት ክፍላችን የገለጹት፡፡

ይህንን ተከትለው የሚመጡ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለማክሰም፣ ምንም እንኳ የተለዩ ዕቅዶች ቢኖሩም፣ አሁንም ቢሆን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን ለመታገል የሚደረገው ጥረት አናሳ መሆናቸው፣ በአመለካከት የተስተካከለ እና የሰለጠነ ልምድ ያለው የሰው ኃይል እጥረት መኖር፤ አገልግሎቶችን ተቋማት ባስቀመጡት ስታንዳርድ መሰረት ያለመስጠት ችግሮች መኖራቸውን ሪፖርቱ አትቷል፡፡

በወረዳና በክፍለ ከተሞች ያለው የቅንጅት ሁኔታ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ፣ በሥራ ቅልጥፍና ላይ የሚስተዋል ችግር መኖር፣ የአርሶ አደሮች የመሬት መጠቀሚያ ፈቃድ ካርታ ስለሌላቸው በካሳ አከፋፈልም ሆነ፣ በምትክ ቦታ አሰጣት ላይ ችግር የሚፈጥር መሆኑ፣ የፕላን ሕጉን የማክበር በተለይም፣ አካባቢ ልማት ላይ የሚስተዋሉ የግለሰቦችን ጥቅም የመጠበቅ ችግሮች አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

ሪፖርቱ አያይዞ ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሠራተኞች አስተዳደር ላይ በራስ ተነሳሽነት ምርመራ ለመሥራት ቢታቀድም የተቋማችን መርማሪዎች ወደ ግቢው ገብተው እንዲሠራ ፈቃደኛ ባለመሆኑ መሥራት አለመቻላቸውን አስታውቋል፡፡

በአዋጅ 211/1992 መሰረት ሁሉም አስፈጻሚ አካላት የመተባበር ግዴታ እንዳለባቸው ቢደነገግም፣ አንዳንድ አስፈጻሚ አካላት በማይተባበሩበት ጊዜ ተቋሙ ተጠሪ ለሆነው ምክር ቤት ይልካል፤ ሆኖም ግን ባለፉት ዓመታት ከአማራ ክልል 7፣ ከኦሮሚያ 5፣ ከደቡብ ክልል 15፣ ከጋምቤላ 1፣ ከትግራይ 1፣ ከአዲሰ ከተማ አስተዳደር 7፣ ከፌዴራል ተቋማት 2፤ በአጠቃላይ 39 ጉዳዮች በልዩ ሪፖርት ምክር ቤት የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለመንግሥት ተጠሪ ተልከው አልተፈጸሙም እንደተቋሙ ሪፖርት። በ2011 የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በዜጎች የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን የመመርመርና ለአስፈጻሚ አካላት የመፍትሔ ሐሳብ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት ያወሱት ዘውዱ፣ ከዚህ አንጻር በ6 ወራት ውስጥ ወደ ተቋሙ በአካል፣ በፖስታ፣ በፋክስ 1954 አቤቱታዎች ይቀርባሉ ተብሎ በዕቅድ ተይዞ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ በዋናው መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች 1783 (ወንድ- 21061 ሴት- 10751 በጾታ ያልተለዩ 2587 በድምር- 34,399 አቤት ባዮች) የያዘ የአቤቱታ መዝገቦች ቀርበዋል፡፡ ከነዚህ አቤቱታዎች መካከል፣ በተቋሙ ሥልጣን ሥር የማይወድቁ 920 ጉዳዮች ላይ የሕግ ምክር አገልግሎት በመስጠትና በሌሎች ተቋማት የሚታዩትን የማስተላለፍ ሥራ መሰራቱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ የአስተዳደር በደል ምርመራን በተመለከተ ከቀረቡት አቤቱታዎች ውስጥ 863 መዝገቦች ተቀባይነት ያገኙ እና ከ2010 በጀት ዓመት የዞረ 247 መዝገቦችን ጨምሮ በአጠቃላይ በ1 ሺሕ 110 የአቤቱታ መዝገቦች ላይ ምርመራ ተካሒዶ 859 (77.4%) መዝገቦች ላይ እልባት ሲሰጥ ቀሪ 251 መዝገቦች ምርመራቸው ባለመጠናቀቁ በሒደት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከቀረቡት አቤቱታዎች ውስጥ የይዞታ ይከበርልኝ፣ ከሥራ ጋር የተያየዘ ክርክር፣ ተገቢውን አገልግሎት አለማግኘታቸውን ዘውዱ አክለው ገልጸዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here