በ7 ትላልቅ ተቋማት ላይ ለሙስና የሚያጋልጡ ከፍተኛ የአሰራር ግድፈቶች ተገኙ

0
700

ጸረ ሙስና ኮሚሽን በ6 ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ በ7 ትላልቅ ተቋማት ላይ ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ አሰራሮች ማግኘቱን አስታወቀ። ከነዚህ ተቋማት ውስጥ፣ ባንኮች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ትልልቅ የመንግሥት ድርጅቶች ይገኙበታል።

ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ሪፖርቱ በተመረጡ ተቋማት የተካሔዱ መደበኛና አስቸኳይ የአሠራር ስርዓቶች ላይ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ጥናት ያካሔደ ሲሆን፣ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ፣ በኅብረት ባንክ፣ በስኳር ኮርፖሬት፣ በዕለት ደራሽ ዕርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲና ሌሎችም ተቋማት ውስጥ ለሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጋልጡ የሚችሉ የተለያዩ የአሠራር ችግሮች ተከስቷል ሲል አስታውቋል።

በነዚህ ተቋማት ውስጥ ለሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጋልጡ የሚችሉ የተለያዩ የአሠራር ችግሮች የተከሰቱ መሆኑን በመለየት፣ እንደ የችግሮቹ ባህሪያት የተለያዩ የማሻሻያ የመፍትሔ ሐሳቦች ለየሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች እንዲደርስ መደረጉንም የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ከበበ ዳዲ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በጂንካ ዩኒቨርሲቲ በተከናወነው የግዥ አፈጻጸም ላይ ንብረትና የሰው ሀይል አስተዳደር በዋጋ ማቅረቢያ (‘ፕሮፎርማ’) ግዥ ዘዴ ከሚፈቀደው በላይ ግዥ ፈጽሟል ያለው ሪፖርቱ፥ በዋጋ ማቅረቢያ ግዥ ለመፈጸም የዋጋ ጥናት አለመደረጉን፣ ለተማሪዎች ምግብ አገልግሎት በሬ ግዥ ክፍተት ያለበት መሆኑን፣ ክፍያ የተፈጸመባቸው ሠነዶች ላይ የተሟላ ፊርማ አለማስቀመጥ፣ የመምህራን ቤት አሰጣጥ በመመሪያ የተደገፈ አለመሆን፣ የሰው ኃይል ቅጥር ክፍተት ያለው መሆኑ፣ በመምህርነት ሙያ የተቀጠሩ ሠራተኞች በተደራቢነት በሌላ ኃላፊነት ላይ ማስቀመጥ፣ ለተማሪዎች ምግብ አገልግሎት የበሬ ተረፈ ምርት ቁጥጥር የማይደረግበት መሆኑን፣ የንብረት ክፍል እና የተማሪዎች የምግብ አገልግሎት ክፍል አሠራር ክፍተት ያለበት መሆኑን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በኅብረት ባንክ አደረኩት ባለው ፍተሻ፣ የሰው ኃይል አስተደደር መመሪያ ክፍተት ያለበት ሲሆን፣ የባንኩ የሰው ኃይል አስተዳደር መመሪያ በሚፈቅደው መሠረት የሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ አለመፈጸም፣ ባንኩ የሠራተኞች ማኅበርን ያላቋቋመ መሆኑንና በባንኩና በሠራተኛው መካከል የኅብረት ስምምነት አለመኖሩን አረጋግጫለሁ ብሏል።

በስኳር ኮርፖሬሽንም በተደረገው ግምገማ፣ ግዥዎች በአስቸኳይ ምክንያት ከአንድ አቅራቢና በፕሮፎርማ የግዥ ዘዴዎች በተደጋጋሚ ግዥ የሚከናወን ሲሆን፣ የቴክኒክ ፍላጎት መግለጫ ግልፅ አለመሆን፣ የአንድን ድርጅት መለያ ምልክት ወይም ብራንድ በመጥቀስ ግዥ መፈፀም፣ በጨረታ ሰነዱ ላይ የተቀመጠውን የመገምገሚያ መስፈርት በመቀየር ግምገማ ማካሔድ ችግሮች እንዳሉበት በኮሚሽኑ ሪፖርት ተገልጿል።

የውስን ግዢን በተመለከተ በደብዳቤ ያልተጋበዘ አቅራቢን ማወዳደር፣ በተለያዩ አካላትና ጊዜ የተካሔዱ የግዥ ሒደት ቃለ ጉባኤዎችን በአንድ ላይ ጨምቆ ማዘጋጀት፣ በፕሮፎርማ ለሚገዙ ግዥዎች ተመሳሳይ አቅራቢዎችን በተደጋጋሚ መጋበዝ፣ ግዥ የተፈፀሙባቸውን ሠነዶች በአግባቡ እና በተሟላ ሁኔታ አለመያዝ የስኳር ኮርፖሬሽኑ ሌሎች ችግሮች ናቸው ተብለው ተጠቅሰዋል።

በአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ የዋና መግቢያ በር እና የሣይት ሥራ፣ ለግንባታው ጨረታ ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ በብር 16 ሚሊዮን 113 ሺሕ 531 ነጥብ 58 አነስተኛ ዋጋ ያቀረበ ድርጅት ቢኖርም፣ ከፍተኛ ዋጋ ያቀረበው ተጫራች አሸናፊ ተደርጓል። ጨረታው ከወጣ ዐሥር ወር አቆይተው በበጀት ዓመት መዝጊያ ወቅት ውል ለማሰር የበቁበት አግባብም በኮሚሽኑ ተጣርቶ፣ በጥናቱ የተገኘው ውጤት በቀጣይ እንዲገለጽ በቀረበው መረጃ መሰረት፣ ዩኒቨርሲቲው ውል ተዋውሎ ሥራ የጀመረ ስለሆነ፣ ጨረታውን ወደ ኋላ መመለስ ስለሚያስቸግር የጨረታ ግምገማ ሒደቱ በጨረታ ሠነዱ ላይ በተገለፀው የቴክኒክ መመዘኛ መስፈርት መሠረት ባለመከናወኑ፣ የሒደቱን ግልጽነትና ፍትሐዊነት ከማዛባቱም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው ከግዥው ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዳያገኝ ያደረገው ስለሆነ ሕጉን ባልተከተለ መንገድ ሥራውን የገመገሙና የተዋዋሉ ሰዎች ዕርምት እንዲወስዱ ለዩኒቨርሲቲው መገለጹ ተጠቁሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here