ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች የበረራ ትኬት ክፍያን በቴሌብር እንዲፈጽሙ የሚያስችል ስምምነት ተስማሙ

0
854

ዕረቡ ሚያዚያ 12 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮ ቴሌኮም እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል የአገር ውስጥ መንገደኞች የበረራ ትኬት ግዢ ክፍያዎችን በቴሌብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት ተደርጓል።

ስምምነቱም የአየር መንገዱ ደንበኞች የጉዞ ትኬት ግዢ ክፍያዎችን በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ በሆነው በቴሌብር እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸው የክፍያ አማራጭ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች በዓመት ውስጥ ከ2 ነጥብ 52 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተጓዦችን ለማስተናገድ በዕቅዱ ይዞ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ከ17 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ከመድረሱ አኳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደንበኞቹ ቀላል እና አስተማማኝ የክፍያ አማራጭ በማቅረብ እቅዱን ለማሳካት እንደሚያስችለውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሙከራ ደረጃ በቴሌብር የአገር ውስጥ ትኬት ክፍያን ከጀመረበት ከየካቲት 7 ቀን 2014 ጀምሮ 6 ነጥብ 67 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የአገር ውስጥ የበረራ ትኬቶችን በቴሌብር አማካኝነት መሸጥ መቻሉም ተነግሯል፡፡

እንዲሁም የቴሌብር አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገበት ግንቦት ወር 2013 ጀምሮ ከ12 ነጥብ 58 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ የአገር ውስጥ የገንዘብ ዝውውር ወይም ግብይት ማከናወን የተቻለ ሲሆን፤ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር (528 ነጥብ 4 ሺህ ዶላር) በላይ በስምንት የቴሌብር ዓለም አቀፍ ሀዋላ አጋሮች በኩል ከ34 አገራት ገንዘብ መቀበል መቻሉን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም የቴሌብር የዲጂታል ግብይት አገልግሎት ተደራሽነት እና የአገልግሎት ሰጪ አጋሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎቱ በ353 የሽያጭ ማዕከላት፣ በ80 ማስተር ኤጀንቶች/ዋና ወኪሎች፣ በ64 ሺህ ወኪሎች እና ከ16 ሺህ በላይ ነጋዴዎች የሚሰጥ ሲሆን ከ12 ባንኮች ጋርም አገልግሎቱን የማስተሳሰር ሥራ ተከናውኗል፡፡

የቴሌብር አገልግሎት የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን ጨምሮ ከ52 በላይ የቀጥታ ግብይትን (online merchants) ከሚያከናውኑ፣ ወርሃዊ የአገልግሎት ክፍያን በቴሌብር ከሚቀበሉ እና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡም ከ20 በላይ ከሚሆኑ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የአገልግሎት ክፍያን በቴሌብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል፡፡
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

     

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here