አራት የውጭ ድርጅቶች 200 ሺሕ ቶን ስኳር ለመግዛት እየተወዳደሩ ነው

0
405

አራት ዓለም ዐቀፍ የውጪ ድርጅቶች ከስድሰት እስከ 18 ወራት ተጠናቆ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ 200 ሺሕ ቶን ስኳርን ከኹለት ቢሊዮን ብር በላይ ለመግዛት እየተወዳደሩ ነው።

በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የካቲት 21/2011 በተከፈተው ጨረታ ዓለም ዐቀፍ የስኳር ውድድር ላይ በብዛት ተወዳዳሪ በመሆን የሚታወቁት አልካሌጅ፣ ሱክደን፣ አግሮኮፕ እና ኢዲኤፍ የተሰኙ የውጪ አገራት ድርጅቶች እየተጫረቱ ሲሆን፣ አግሮኮፕ የተባለው ድርጅት ዓለም ዐቀፍ የጨረታ ውድድሮችን በተደጋጋሚ በማሸነፍ እንደሚታወቅ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያን የስኳር ግዥ ለማቅረብ ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች ጋር ሲነፃፀር ባቀረበው ዝቅተኛ ዋጋ ምክንያት ጨረታውን ያሸንፋል ተብሎ እየተጠበቀ ያለው አግሮኮፕ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያን መርከብ በመጠቀም ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባ ከሆነና ክፍያውም በስድስት ወር የሚጠናቀቅለት ከሆነ በአጠቃላይ ኹለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር እንዲከፈለው ጠይቋል። በሌላ በኩል ክፍያው በአንድ ዓመት የሚከፈለው ከሆነ ኹለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ጠይቋል። ሙሉ ክፍያው እስኪፈፀምለት 18 ወራትን ለመጠበቅ የሚገደድ ከሆነ ደግሞ ኹለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር እንዲከፈለው ጥያቄ አቅርቧል።

በተያያዘም ድርጅቱ የራሱን ማጓጓዣዎች በመጠቀም ስኳሩን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባ ከሆነ በአንድ ሜትሪክ ቶን 10 የአሜሪካን ዶላር ቅናሽ እንደሚያደርግም ባቀረበው የጨረታ ዋጋ አመልክቷል። ይህም ማለት ከአጠቃላይ ግዢው የኹለት ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ እንደሚያደርግ አመልካች ነው።

ግዢው ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ወጪ የሚሸፈን ሲሆን በአገሪቱ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለውን የስኳር እጥረት በመጠኑም ቢሆን ይፈታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ኢትዮጵያ ለመግዛት ያቀደችው አጠቃላይ የስኳር መጠን 300 ሺሕ ቶን ሲሆን፣ አሁን ላይ ጨረታ ወጥቶ ለውድድር የቀረበው 200 ሺሕ ቶን ስኳር ነው። በመሆኑም ቀሪውን አንድ መቶ ሺሕ ቶን ስኳር ለመግዛት ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ ኹለተኛ ዙር ጨረታ እንደሚያወጣ የኮርፖሬሽኑ የውጪ ግብይት ሥራ አስፈፃሚ ጌታነህ አረጋ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የሚገዛው ስኳር ከሚያዝያ 2011 ጀምሮ ወደ አገር የሚገባ ሲሆን በጅቡቲ ወደብ በኩል እንዲመጣ ታቅዷል። ስኳሩም ለፋብሪካዎች እንዲሁም ለኅብረተሰቡ የዕለት ፍጆታ እንደሚቀርብ የግብይት ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

በግዥ ጨረታ ሒደት ላይ የሚገኘው ስኳር ካለፈው መስከረም ጀምሮ እየገባ ካለው እና እጥረት እንዳያጋጥም በሚል ለመጠባበቂያ ከተገዛውና በአምስት ዙሮች ተከፋፍሎ እየገባ ካለው ኹለት ሚሊዮን ኩንታል ጋር ተደምሮ አቅርቦት ላይ የለውን እጥረት ሊፈታ እንደሚችል ታምኖበታል።

ከስኳር ኮርፖሬሽን ይፋዊ ድረ ገጽ መመልከት እንደሚቻለው አሁን ያለው አገራዊ የስኳር አቅርቦት መጠን በዓመት ከስድስት እስከ ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ነው። ከዚህ ውስጥ ባለፉት ዓመታት ከሦስት ነጥብ 25 እስከ አራት ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ስኳር በአገር ውስጥ የተመረተ ሲሆን፣ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ልዩነትም ከኹለት እስከ ኹለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል እንደሆነ ኮርፖሬሽኑ አሳውቋል። ልዩነቱም ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስኳርን ከዓለም ዐቀፍ ገበያዎች እንድትገዛ አስገድደዋታል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአንድ ሰው ዓመታዊ የስኳር ፍጆታ ከ10 ኪሎ ግራም በላይ እንደሆነ ቢገመትም እየቀረበ ያለው ሰባት ኪሎ ግራም እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here