ለአማራ ክልል ተፈናቃዮች ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ አስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልጋል ተባለ

0
429

ቁጥራቸው ከ90 ሺሕ ለላቀው የአማራ ክልል ተፈናቃዮች ማቋቋሚያ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

ይህም ከአቅሙ በላይ መሆኑን ያሳወቀው የክልሉ መንግሥት ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የእርዳታ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች አርሶ አደሮች እህል በማሰባሰብ ጭምር ተፈናቃዮቹ ወደሚገኙበት ጎንደር እየላኩ መሆኑ ታውቋል።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችም ድጋፍ እያደረጉ ነው ተብሏል። የተለያዩ ተቋማትም የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። ከተፈናቃዮቹ መካከል 40 ሺሕ የሚሆኑት በማዕከላዊና ምዕራባዊ ጎንደር ዞኖች ከተነሳው የቅማንትና አማራ ግጭት ጋር በተያያዘ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን ‘ኢሮፒያን ሲቪል ፕሮቴክሽን ኤንድ ሂዩማኒቴሪያን ኤድ ኦፕሬሽን’ በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በምዕራብ ጎንደር ለሚገኙ 55 ሺሕ 587 ተፈናቃዮች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል። በዚህም ከ8500 ኩንታል በላይ የምግብ እርዳታ (እህል) ስለመላኩም አክሏል።

በሌላ በኩል በአገሪቷ ባለመረጋጋት ምክንያት በማዕከላዊ ጎንደር የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ ኣሳሳቢ መሆኑን አፋጣኝ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ለተፈናቃዮቹ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ታውቋል።

ዜጎቹም ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ቢፈልጉም እንኳ ከቄያቸው ሲሰደዱ ባዶ እጃቸውን በመውጣታቸው ምክንያት እንዲመለሱ የሚደረግበት መንገድም በራሳቸው ፍቃድ እና ደኅንነታቸው ተረጋግጦ አንዲሁም አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረገላቸው ቢገባም ሊሳካ አለመቻሉ ታውቋል።

በማዕከላዊ ጎንደር የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ45ሺ በላይ መሆኑን ተጠቅሷል። ተፈናቃዮቹ በአደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽን መሥሪ ቤት በኩል ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። ለተፈናቃዮቹ በዋናነት 851 ሜትሪክ ቶን ምግብ የቀረበላቸው ሲሆን በተጨማሪ ዘይት በቆሎ እና ሰንዴ ጨምሮ ሌሎች አላቂ ቁሳቁስ እንደቀረበላቸው ምንጮች ገልፀዋል።

ተፈናቃዮቹን አስመልክቶ የክልሉ መንግሥት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ኃላፊ የሆኑት አሳየኸኝ አስረስ ከዛሬ ኹለት ሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ የአማራ ክልል መንግሥት ተፈናቃዮችን በኹለት ወራት ለማቋቋም እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በባህር ዳር የካቲት 14/2011 በሰጡት መግለጫ የአማራ ክልል መንግሥት በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎችን በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ተናግረው ነበር።

ተፈናቃዮቹን በኹለት ወራት ውስጥ መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነም አሰማኸኝ አስታውቀዋል።

በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር የተቃጠሉ ቤቶችን ለመገንባት ከሚፈለገው የቤት ክዳን ቆርቆሮ 50 ከመቶውን መንግሥት መግዛቱን ያስታወቁት አሰማኸኝ ቀሪውን መንግሥት ከለጋሽ አካላት እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል። በማዕከላዊ ጎንደር 4 ሺሕ 361 ቤቶች እና በምዕራብ ጎንደር 1 ሺሕ 500 ቤቶች ተቃጥለዋል።

በመሆኑም የክልሉ መንግሥት 5 ሺህ 861 ቤቶችን ገንብቶና መንደር መሥርቶ ዜጎችን ሊያቋቁም መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ በሠጡት መግለጫ ገልፀዋል።

የሚገነቡት ቤቶች እንደ ቤተሰብ ብዛት የሚለያዩ ናቸው፤ አራትና ከዚያ በታች አባላት ላሉት ቤተሰብ ባለ 40 ቆርቆሮ፣ ከአራት በላይ የቤተሰብ አባላት ላሏቸው ደግሞ ባለ 60 ቆርቆሮ ቤት እንደሚገነባ ነው የተናገሩት።

በተጨማሪ፤ የክልሉ መንግሥት ተፈናቃዮችን በኹለት ወራት ለማቋቋም እየሠራ መሆኑንና የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ኃላፊነቱን ወስደው በዞኖቹ እየሠሩ እንደሆነ አስታውቀው “ከዚህ በኋላ ወንጀለኞችን ለአንድም ደቂቃ ቢሆን አንታገስም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here