123ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ድሉ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ምን ያስተምራል? ከታሪክ በመማር በኩል ምን ጎደለን? በቀጣይስ ምን ማድረግ አለብን? አፍሪካዊያን የአድዋን ድል ‹የእኛ ታሪክ ነው› በሚሉበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን እንዴት እየተማርንበትና የአንድነታችን ማጠንከሪያ እያደረግነው ነው? በተጨማሪም ድሉን የታሪካችን ምርምር አንድ መነሻ ማድረግ ላይ ስለሔድነው ርቀትና ስለሚቀረን የቤት ሥራ የአዲስ ማለዳው ስንታየሁ አባተ የጥናት ሰነዶችን በማገላበጥና ባለሙያዎችን በማነጋገር ከአድዋ ድል ባሻገር ያሉትን ጉዳዮች የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።
‹‹ሞዓ አምበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ። እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፋፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ለእኔ ሞት አላዝንም። ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም።
አሁንም አገር የሚጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚሃብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።››
ይህ ለመላ ኢትዮጵያዊያን የቀረበ አገርን ከወራሪ የማዳን ጥሪ በበርካቶች ዘንድ በተለይም በየካቲት የሚታወስ ነው። የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአድዋ ዘመቻ የክተት አዋጅ ጥሪ የተደረገው ከጦርነቱ ዘለግ ካሉ ወራት በፊት (መስከረም 1888) ቢሆንም በብዙዎች ዘንድ የሚታወሰው የየካቲት 23ቱ የአድዋ ድል በዓል ሲመጣ ነው። አዋጁ በብዙዎች ዘንድ (በማኅበራዊ ትስስር ገፆች) በየካቲት ይታወስ እንጂ ይህን ሰነድ ኅልው አድርገው ያኖሩ ድርሳናትም በርካታ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ‹‹አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት›› የሚሰኘው የተክለ ጻዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ በገጽ 226 ላይ አስፍሮት ይገኛል።
የአድዋ ድል እና አፍሪካ
አድዋ ከአንድ አካባቢያዊ ስም የዘለለና የገዘፈ ትርጉም ያለው ነው። ይህን ግዝፈት የነሳው ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በአድዋ ተራሮች የፈጸሙት ጀብድ ነው። ስፍራው ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቱ ሊደርግ አልሞ የተነሳውና ገፍቶም በዘመናዊ መሣሪያ ታጅቦ ለጦርነት የተሰለፈው የጣሊያን መንግሥት ኋላ ቀር መከላከያን በያዙት ኢትዮጵያዊያን ድል የተደረገበት መሆኑ ዛሬ ላይ አድዋ ኢትዮጵያ ከሚለው ባልተናነሰ ለመላ አፍሪካዊያን የነጻነት ተጋድሎ ተምሳሌት ሆኖ ይነሳል። ለዚህም ነው አድዋ ከአንድ አካባቢ መጠሪያነት ተሻግሮ ዓለም እንዲያውቀው የሆነው።
ከነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ቀጥሎ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት የነበሩት ታቦ ምቤኪ ስለ አድዋ ከፍታ አውርተው ከማይጠግቡት አፍሪካዊያን መሪዎች መካከል ናቸው። በ121ኛው የአድዋ ድል በዓል መታሰቢያ ኢትዮጵያ የነበሩት ምቤኪ ከአድዋው የሶሎዳ ተራራ አናት 121ኛ ዝክር መልስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው የድሉ መታሰቢያ የፓናል ውይይት ላይ ነበሩ። በወቅቱም የአድዋን ድል መነሻ አድርገው አድዋ እንዴት የአፍሪካዊያን የነጻነት ተጋድሎ መስፈንጠሪያ እንደሆነ ያስረዱበት መንገድ ለብዙዎች አግራሞትን ሲፈጥር ነበር።
‹‹የ1888ቱ የአድዋ ድል ያለቀው የኢትዮጵያዊያን እና አፍሪካዊያን የጋራ ድል›› ሆኖ ነው የሚሉት ታቦ ‹‹በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መኮንን እና ሌሎችም ዝነኛ ኢትዮጵያዊያን የተመራው ጀብደኛ የአፍሪካ ጦር አህጉራችን ከኢምፔሪያሊዝምና ቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት የሚታገልና ድልም የሚያመጣ ስለመሆኑ ለመላ አፍሪካዊያን ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፈ ነው›› ሲሉ ድሉ ከኢትዮጵያዊያን አልፎ ለአፍሪካዊያንም የመነቃቃት ክኒን ስለመሆኑ ያስረዳሉ። ድሉ ያመጣው የጥንካሬ መንፈስ ለበርካቶች ‹‹አፍሪካና ኢትዮጵያ የሚሉት ኹለት ስሞች ተመሳሳይ ሆነው እንዲታዩ አድርጓል›› ሲሉም ደቡብ አፍሪካዊው መሪ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያዊነት በአድዋ ጦርነት ውስጥ
ታሪክ እንደሚያስረዳው የአድዋ ጦርነት ከመጀመሩ ቀድሞ በነበሩ ዓመታት በተጠናከረ ማዕከላዊ አገር ምስረታም ይሁን በግዛት ማስፋፋት ሒደት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወዶ ገብ አልነበረም። ይልቁንም በየግዛቱ የሚገኙ መሪዎች ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ተቃርኖ ውስጥ የነበሩበት ወቅት እንደነበር ይነሳል። ተቃርኖዎቹ በማዕከላዊው መንግሥት ላይ መሸፈትንም ያካተቱ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ይሁንና በአድዋው ጦርነት ጠላት የመጣው ለአገር ሆኖ በመገኘቱ ኢትዮጵያዊያን ውስጣዊ ችግራቸውን ቸል ብለው በጋራ ለመቆም አለማቅማማታቸውም ድሉ እንዲገኝ ማድረጉ ይነሳል።
ስለዚህ ጉዳይ በሐምሌ 2009 የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የነበሩት ተሾመ አበራ Ethiopianism principles በሚል ርዕስ ያደረጉት ጥናት የአድዋ ጦርነት ድል ሰብኣዊነት ያለ ቀለም (መልክ) ልዩነት እኩል ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ያትታል። ‹‹ድሉ የሚያሳየውም ወሳኙ ነገር የጦር መሣሪው ዓይነት ሳይሆን ለምን እንዋጋለን የሚለውን ዓላማና ግብ›› ነውም ይላል። እንደ ጥናቱ ዘመናዊ ጦር የታጠቀው ጣሊያን ኋላቀር መሣሪያ ባነገቡ ኢትዮጵያዊያን የተሸነፈው በጦር መሣሪያ ተበልጦ ሳይሆን በኢትዮጵያዊያን አንድነትና በጋራ የመቆም ፅናት ነው።
በዚህ ሐሳብ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የምክር ቤት አባሉ ዳኛቸው ተመስገን ይስማማሉ። በአድዋ ጦርነት ጠላት ሊሸነፍ የቻለው ‹‹ኢትዮጵያዊያን ጠላት የመጣ ጊዜ በዘር፣ በጎሳና በሃይማኖት ሳይለያዩ በጋራ ለመመከት በመነሳታቸው ነው›› ይላሉ። ‹‹እምቢ ለአገሬ እና ዱር ቤቴ ብለው›› በአንድነት ጠላትን የገጠሙትም በመሃላቸው ልዩነትና መቃቃር ስላልነበረ ሳይሆን በጋራና በአገር ጉዳይ ላይ የሚለያዩ ባለመሆናቸው እንደነበርም ያክላሉ።
ሌላው የምክር ቤቱ አባል ሻምበል ዋኘው አባይ ‹‹በአድዋው ጦርነት የጣሊያንን ጦር ለማሸነፍ የወሰደው ጊዜ 4 ሰዓት ብቻ ነው። ይህም በአንድ አቋም የፀኑት ኢትዮጵያዊያን ጥንካሬ ተመሳሌት ነው። ያሸነፈውም አንድነትና ፍቅሩ ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ። ‹‹በኢትዮጵያ 13 ሺሕ 500 ጦርነቶች ተካሒደዋል፤ በእነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያዊያን አላፈሩም›› የሚሉት ሻምበል ዋኘው ሁሉንም ጦርነትና የወረራ ሙከራዎች ማሸነፍ የተቻለው ዜጎች በአንድነት መቆም ስለቻሉ እንደሆነም ያምናሉ።
በአድዋ ጦርነት ከሺሕ ኪሎ ሜትሮች በላይ ከየአቅጣጫው በእግር ተጉዘው አድዋ ላይ ድል የነሱት ኢትዮጵያዊያን የጉዟቸው ምክንያት ኢትዮጵያዊነታቸው ስለመሆኑም የሚያነሱት ብዙዎች ናቸው።
በእርግጥም ኢትዮጵያዊያን በጠላት ወረራ ጊዜ ከውስጣዊ ችግራቸው ይልቅ የጋራ ጠላትን መመከትና የአገርን ሉዓላዊነት ማስከበር ላይ ለድርድር እንደማይቀመጡ (ጠላትን በጋራ ለመውጋት እንደማያመነቱ) የሚያሳዩ አብነቶች በርከት ያሉ ናቸው። ለምሳሌ ጳውሎስ ኞኞ፣ ‹‹አጤ ምኒልክ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 167 ላይ “ደጃዝማች ጓንጉል ዘገየ በአጤ ምኒልክ ላይ ሸፍተው ከምኒልክ ጭፍሮች ጋር በጦርነት የተፈታተኑ ሰው ናቸው። በዚህም በትግራይ ዘመቻ ጊዜ በምኒልክ ላይ እንደሸፈቱና በረሃ እንደገቡ ናቸው። ምኒልክ ሕዳር 24 ቀን መርሳ ላይ ሰፍረው ሳሉ የደጃዝማች ጓንጉል መልዕክተኛ ከአጤ ምኒልክ ዘንድ መጣ። መልእክተኛውም ‹ጃንሆይ ከእርስዎ ተጣልቼ በረሃ ገብቻለሁ። አሁን ግን በአገሬ ላይ የውጭ ጠላት ስለመጣባት የእርስዎና የኔ ጉዳይ ቀርቶ ይማሩኝና መጥቼ ከእርስዎ ከጌታየ ጋር ሁኜ ያገሬን ጠላት ልውጋ ብለዋል› ብሎ ተናገረ። አጤ ምኒልክም ተደስተው ‹‹ይምጣ ምሬዋለሁ›› ብለው ላኩ። ደጃዝማች ጓንጉልም መጥተው ከአፄ ምኒልክ ጋር ተገናኙ። ሠራዊቱም መኳንንቱም በእንደዚህ ያለ ጊዜ መጥቼ ከጌታዬ ጋር ልሙት በማለታቸው እጅግ ተደነቁ።” ሲሉ ጽፈዋል። ይህም ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ ያላቸውን ትብብርና አንድነት አስረጂ ሆኖ ይወሰዳል።
ከጉዞ አድዋ መስራችና አስተባባሪዎቹ መካከል የሆነው ያሬድ ሹመቴ ኢትዮጵያዊያን አንድ የሆኑትና የተሰባሰቡት ለአድዋ ጦርነት ሳይሆን ቀድሞ ነው በማለት የተለየ ሐሳብና አረዳድ እንዳለው ይናገራል። ያሬድ ለአዲስ ማለዳ ሲናገር ኢትዮጵያዊያን ቀድመው አንድ ባይሆኑና እንዲያው አገር ተወረረ በሚል ብቻ ለጊዜው የተባበሩ ቢሆን ኖሮ ድሉ የኢትዮጵያዊያን ላይሆንም ይችል እንደነበር ይገምታል። ይልቁንም የወቅቱ መሪ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በግዛት ማስፋፋትም ይሁን በማስገበር ሒደት ጥበብ በተሞላበትና በትህትና መሔዳቸው ኢትዮጵያዊያን ቀድመው አንድ እንዲሆኑ ማድረጉን ያነሳል። ያሬድ ያክልና ኢትዮጵያዊያን ለአድዋ ጦርነት ሲባል ብቻ እንደተሰባሰቡ በሚነገረው ትርክት እንደማይስማማ ያሰምርበታል።
ኢትዮጵያኒዝም /Ethiopianism/
ኢትዮጵያኒዝም የሚለው እሳቤ ለብዙኃኑ ጆሮ ባዳ ይምሰል እንጂ በታሪክ አዋቂዎች ዘንድ እንግዳ ፅንሰ ሐሳብ አይደለም። የተሾመ አበራ ጥናት ኢትዮጵያኒዝም ስለሚለው እሳቤ ሲያስረዳ ‹‹ኢትዮጵያኒዝም የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ለአፍሪካዊያን እና በመላ ዓለም ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን የትእምርታዊነትና ማነሳሳት ሚና የሚገልጽ ነው›› ይላል። ፅንሰ ሐሳቡ ‹‹ኢትዮጵያዊያን በፋሽት ጣሊያን ላይ በ1888 ለተቀዳጁት የአድዋ ድል እውቅና የሚያገለግል›› እንደሆነም ጥናቱ ያስገነዝባል። ጥናቱ ሐቲቱን ሲቀጥል ኢትዮጵያኒዝም የሚሰኘው እሳቤ የጥቁር ሕዝቦች የፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ትምሕርታዊ ንቅናቄዎች ሞተር ሆኖ እንደሚያገለግልም ይዘረዝራል። እሳቤው አፍሪካዊያን ዘረኝነትንና ፋሽስታዊ ሥርዓትን ለመታገል ጥንካሬን እንዲያገኙ የሚያነሳሳ መሆኑን በመጥቀስም ዳሩ ግን አሁንም በዴሞክራሲ፣ በነፃነትና ሰላም እጦት እንዲሁም በድኽነት ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ትግላቸው አለማብቃቱን ያትታል።
ታቦ ምቤኪ በ121ኛው በዓል መታሰቢያ ንግግራቸው ሮበርት አሌክሳንደር ያነግ በኒዎርክ በአውሮፓዊያኑ 1829 ላይ የሳተመውን ‹‹the Ethiopian manifesto: issued in defence of the black man’s right in the scale of universal freedom›› እንደአብነት በመጥቀስ ‹‹እኛ አሁን ያለነው ከዚህ ጉዳይ ጋር በጣም ቅርርብ አለን›› ይላሉ።
‹‹የኢትዮጵያ ማኒፌስቶ›› በአሜሪካ የነበሩ የአፍሪካዊያን ‘ባሪያዎች’ም ይሁን በየትኛውም ክፍል የሚገኙ አፍሪካዊያን ለነፃነታቸው በጠንካራ መንፈስ እንዲታገሉ እርሾ የሆናቸው እሳቤ መሆኑን ነው ታቦ የሚያስረዱት። አክለውም ጸሐፊው ‹‹የኢትዮጵያ ማኒፌስቶ›› የሚለውን የመረጠው በኹለት መንገድ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
አንዱ ከአህጉሩ ውጭ በተለያዩ አገራት የሚኖሩትን አፍሪካዊያን ዲያስፖራዎች ጨምሮ ሁሉንም አፍሪካዊ እንደኢትዮጵያዊ የመመለከት ጉዳይ ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ የአፍሪካዊያንን የነጻነትና የፍትሕ ፍለጋ ተነሳሽት ከኢትዮጵያ ጋር ማዛመዱ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
ታቦ በባርነት ውስጥ ለነበሩ ዜጎች ኢትዮጵያ የነጻነትና የልዕልና ምሳሌ፣ የመታገያም መነሻ ሆና ስለማገልገሏ ሮበርት አሌክሳንደር ከ190 ዓመታት በፊት የጻፈውን በማሳያነት ያቀርባሉ። ኋላም ለተቀነቀነው የፓን አፍሪካንና የአፍሪካዊ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ዋጋ ከፍ ያለ እንደነበር ነው የሚያስረዱት። ይህ ዓይነቱ አፍሪካዊ ብሔርተኝነትም ‹‹ኢትዮጵያኒዝም›› ይባላል የሚሉት ታቦ ጽንሰ ሐሳቡ በደቡብ አፍሪካዊያን ዘንድ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪዎቹ 10 ዓመታት እንደተቀነቀነም ይጠቅሳሉ። የደቡብ አፍሪካው ‹‹አፍሪካን ናሽናል ኮንግረንስ/ ኤኤንሲ/›› ፓርቲ የኢትዮጵያኒዝምን ፅንሰ ሐሳብ በማራመድ ከቀዳሚዎቹ መካከል እንደነበርም ያስረዳሉ።
ከደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ፕሬዘዳንትነት ባሻገር የነፃነት ታጋይ በመሆናቸው ዓለም የሚያውቃቸው ኔልሰን ማንዴላ ስለ አድዋ ድል ሲናገሩ የጣሊያንን የግዛት ማስፋፋት ልክፍት በመወንጀል ‹ሞሶሎኒ ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ሲሰነዝር የ17 ዓመት ልጅ ነበርኩ፤ ኢትዮጵያ በዐይነ ኅሊናዬ ውስጥ ሁሌም የተለየ ቦታ አላት፤ በአንድ ጊዜ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ሔጀ ከምጎበኘው በላይ ኢትዮጵያን መጎብኘት ይበልጥበኛል፣ የራሴን ዘር መገኛ ብጎበኝ እመርጣለሁ፣ ኢትዮጵያ እኔን አፍሪካዊ ያደረገች ምድር ነች፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን ማግኘት በራሱ ታሪክን በእጅ እንደመጨበጥ (ለሰላምታ) ነው› ሲሉ ለኢትዮጵያና ኢትጵያዊያን ያላቸውን ክብር ስለመግለፃቸው ያገራቸው ልጅና የሥልጣን ተተኪያቸው ታቦ ምቢኬ ያስታውሳሉ።
ኢትዮጵያዊያን ይህን ያህል የነፃነት ተጋድሎ ተምሳሌቶች ሆነው ለመሳል ያበቃቸው ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄም ዋናው መለያ የአድዋ ጦርነት ድል ይሁን እንጂ ከዚያ ቀድሞ በነበሩትም ሆነ ቀጥሎ በመጡት የታሪክ ዓመታት ለነፃነታቸውና ለአገራቸው ሉዓላዊነት የነበራቸው አርበኝነት፣ አንድነት፣ ልዩነትን ማቻቻል እና ያላስደፈሩት ነፃነት የብዙ አገራትን ቀልብ መግዛቱን የተሾመ ጥናት በዝርዝር ያስረዳል።
ከአድዋ ድል ምን ተማርን? እና ስጋት
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት ከአድዋ ትልቁን ትምህርት መማር ያለባቸው ወጣቶች ናቸው ይላሉ። አርበኞችም ለዚህ መስራት አለባቸው የሚሉት ዳኛቸው ወጣቱ ‹‹ሊማር የሚገባው ከአባቶቹ ነው፣ ማኅበሩ ደግሞ ይህን ማስተማር አለበት›› ይላሉ። በተያያዘም ‹‹ታሪክ እየጠፋ ነው፣ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፣ በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ መጻሕፍት እየጠፉ ነው፣ ትምህርት ሚንስቴር የታሪክ ሥርዓተ ትምህርቱን ሊከልስና ታሪክን በወጉ ትኩረት ሰጥቶ ለትውልዱ ሊያስተምር ይገባል›› ሲሉ እየተስተዋሉ ያሉ ግድፈቶችን ይዘረዝራሉ። በእርግጥ በዩኒቨርሲቲዎች ላይ በቀደሙ ዓመታት ይሰጥ የነበረውን የታሪክ ትምህርት እንዲዳከም በማድረግና በብዙ ዩኒቨርሲቲዎችም ታሪክ የሚለው ትምህርት እየቀረ ታሪክና ቅርስ አስተዳደር በሚል መተካቱን የሚያነሱ ኢትዮጵያዊያን ኢሕአዴግ መራሹን መንግሥት ሲወቅሱ ይሰማል። አሁን ያለው መንግሥት ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጀግና እንዳይኖራቸውና ታሪካቸውን እንዳይማሩበት እንዲሁም ለነገ በጓቸው እንዳይጠቀሙበት አድርጓልም በሚል ይወቀሳል።
ረጅም ዓመታትን ታሪክ ሲያስተምሩ የነበሩትና አሁን ላይ በመከላከያ ስልጠና መምሪያ የሜጀር ጀኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ኮሌጅ የስነ ዜጋ መምህር እንዲሁም የሥርዓተ ትምህርትና ትምህርት ጥራት ባለሙያው አዲስ አለማሁ እንደሚሉት ያለንበት ወቅት የካፒታሊስት ሥርዓት የበላይ የሆነበት በመሆኑ ሰዎች በተለይም ወጣቱ ወደኪሱ የሚገባውን ቁስ እንጂ በአድዋ ድል ማድረግን እንደትልቅ ቁም ነገር እንዳይቆጥር አድርጓል። ታሪክን ሲያስተምሩ ከተማሪዎቻቸው በኩል ከሚነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል ‹‹ቅኝ አልተገዛንም የሚለው ያለፈ ታሪክ አሁን ምን ጠቀመን? ቅኝ ባለመገዛታችን ምን አተረፍን? ቅኝ ብንገዛ ኖሮ እንደዛሬው ድኻ አገር እንሆንስ ነበር ወይ? የተገዙት እኮ ዛሬ አልፎላቸዋል›› የሚሉ መሆኑን ያስታውሳሉ። ስለሆነም መንግሥት ስርዓተ ትምህርቱን መፈተሽና በወጉ ትውልዱን ታሪክ ማስተማር እንዳለበት ይመክራሉ።
ሻምበል ዋኘው በበኩላቸው ወጣቱ ታሪኩን በማወቅ የአባቶቹን የጀግንነትና የአንድነት ታሪክ መድገም እንዳለበት ያስቀድማሉ። አሁንም ኢትዮጵያዊነት እንዳለ ነው የሚሉት ሻምበል ዋኘው ወጣቶች የጀመሩት የአድዋ የእግር ጉዞ የአባቶችን ኢትዮጵያዊ አደራና መስዋዕትነት የማስታወስ ማሳያ እንደሆነም ያስገነዝባሉ። በሌላ በኩል አሁን ላይ ቄሮና ፋኖ እየተባለ ስም ይቀያየር እንጂ ወጣቱ ሁሌም የኢትዮጵያ ዘብ መሆኑን እያስመሰከረ ነው በማለትም ‹‹በወጣቱ የታየ ጉድለት የለም፤ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው የሚሉ መሪዎችም ተፈጥረዋል›› ሲሉ ኢትዮጵያዊነት በየማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች እንደሚባለው አለመጥፋቱን ያስረዳሉ።
እንደዳኛቸው እምነት ጠላት በጦርነት አልሆን ሲለው በራሳችን ሰዎች (‘ባንዳዎች’) አገርን በተለያየ መንገድ ለመከፋፈል ሴራ እየሸረበ ነው። በብሔርና በሃይማኖት ለመከፋፈል የሚባትሉ ወገኖች አሉ የሚሉት ዳኛቸው ወጣቱ ሊመክታቸውና ጆሮ ሊነፍጋቸው ይገባል ይላሉ። ‹‹የፌስቡክ ፕሮፖጋንዳዎችን ቆም ብሎ ማሰብና ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፤ ዛሬ ላይ ያልተጋባና ያልተዋለደ ኢትዮጵያዊ ስለሌለ ማን በማን ላይ እጁን ያነሳል›› ሲሉም ይጠይቃሉ። አክለውም የአድዋ ተጓዥ ወጣቶችም በየመንገዳቸው ታሪክን እያወቁና የሕዝብን ትክክለኛ ስሜት እየተረዱት መሔድ አንዳለባቸው ከተመለሱ በኋላም ያዩትን እውነታና ኢትዮጵያዊነት መስካሪና ለቀሪው ሕዝብም አስተማሪ መሆን አንደሚጠበቅባቸው በመግለፅ ከመጓዝ የሚሻገር አደራ እንዳለባቸው ይመክራሉ።
ያሬድ በበኩሉ በአድዋው የእግር ጎዞ ሒደት ከሚያገኙት ሕዝብ መማር ብቻ ሳይሆን ተጓዞቹም ስለኢትዮጵያ ያላቸውን አረዳድ ላገኟቸው ሁሉ እያስተማሩ ዛሬ አድዋ ላይ መድረሳቸውን ይናገራል። ከአድዋ የአንድነትንና ኅብረት (ለጋራ አላማ በጋራ መቆም) ግብ አሳኪነትን፣ ከምንም በፊት ነፃነትና ሰውነት መቅደምን፣ ጥበበኛነትን (ከጦርነት ቀድሞ አገርን አንድ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎችና በጦርነት ወቅትም ከሕዝብ ያለመለየትን ብልሃት የተሞላበት ጥበበኛ የመሪ አካሔድ) እንዲሁም አድዋ ዛሬ ናትን (ዛሬም አገርን አንድ ለማድረግ ፍፁም ትህትና እንደሚፈልግ) መማራቸውን ያሬድ ይዘረዝራል።
በኢትዮጵያዊነት በኩልም አየር ላይ የሚናፈሰውና መሬት ላይ ያለው አይገናኝም የሚለው ያሬድ ጉዞው ከመጀመሩ በፊት ከተለያዩ ወገኖች ዛቻዎች ስለነበሩ ስጋት እንደነበረባቸው በተግበር ሲጓዙ ግን ስጋቱ እውን ሆኖ እንዳልገጠማቸውና በሕዝቡ ፍቅር እየተላቀሱ 58 ተጓዦች (ከሐረር የተነሱ 4፣ ከአዲስ አበባ ጉዞ የጀመሩ 44፣ መቀሌ ላይ የተቀላቀሉ 5፣ በ15 ቀን ሩጫ ገስግሰው የደረሱባቸው 2 እንዲሁም 3 አስተባባሪዎች) ደስ በሚል የፍቅር ጉዞ አድዋ ላይ መድረሳቸውን ተናግሯል።
ያሬድ ቀድሞ ስለነበረው ዛቻና ስጋት ሲያስረዳ አንዱ ‹‹የአድዋንና የምኒልክን ታሪክ አንፈልግም (አንቀበልም) በእኛ ክልል ውስጥም አታልፏትም› የሚል ሲሆን ኹለተኛው ‹የአድዋ በዓል መከበር ያለበት አድዋ ሳይሆን አዲስ አበባና አንኮበር ነው› የሚል ነው። ሦስተኛው ደግሞ ‹በእኛ ክልል አልፋችሁ አድዋ ላይ አትገቧትም› የሚል እንደነበር ይጠቅሳል። ይህም ስጋት ፈጥሮ እንደነበር በመጥቀስ በተግባር ስላጋጠማቸው ሲናገር ከአዲስ አበባ ከወጡ ጀምሮ ባሉት 80 ኪሎ ሜትሮች ውስጥ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ደግሰው እንደተቀበሏቸውና በሰላም እንዲገቡ ተመኝተው እንደሸኗቸው፣ በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ሲያልፉም ሕዝቡ በደስታ ሲቀበላቸው እንደነበር እንዲሁም በትግራይ ክልልም ነዋሪው በፍቅር ሲያስተናግዳቸው እንደነበር በመግለፅ የሕዝቡን አንድነት ስለማረጋጋጣቸው ይመሰክራል።
‹‹በምቾት የሚያንገላታ ሕዝብ ነው የገጠመን›› የሚለው ያሬድ በየደረሱበት ደስታ እንደነበርና ሲለዩዋቸው በፍቅር ተቃቅፈው የሚያለቅሱ ኢትዮጵያዊያን ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ እንደገጠሟቸው ያስረዳል። ‹‹በረገጥንበት መሬት በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ተቀብለውናል ሙሉ የጉዞ ቀናት የአድዋ በዓል ይመስል ነበር›› ሲልም ስላጋጠማቸው ኢትዮጵያዊ አንድነት ያነሳል። ሕዝቡ አንድ መሆኑን በመጥቀስም ሌሎች የፖለቲካና የልማት ጥያቄዎች በራሳቸው መንገድ እንዲመለሱ ሕዝቡ ግን በኢትዮጵያዊነት ላይ ልዩነት እንደሌለው ማስተዋላቸውንም ያክላል። ‹‹ስንቅ በብዛት የነበረው ከሕዝቡ ነው፣ በቀጣይ ዓመታት ምንም ስንቅ ሳንይዝ ብንወጣ ኢትዮጵያዊያን በየመንገዱ እንደሚሸፍኑት እናምናለን›› የሚለው ያሬድ የሕዝብን ኢትዮጵያዊነት መረዳታቸውን በመግለፅም ተጓዦቹ ሲመለሱ በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር እንደሚሰሩ ተናግሯል። የምን ጫና ለሚለውም ‹ከክልሌ ውጡልኝ፣ የእኔ አይደላችሁም›› እና መሰል የመለያያ ተግባራት እንዲቆሙ መንግሥት በትኩረት እንዲሠራ ስለመሆኑ ነግሮናል። ያሬድ በየማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚስተዋሉት ከፋፋይ እሳቤዎችና ችግሮቹ የሚመጡት ለራሳቸው ፍላጎት ሲሉ ሕዝቡን መጠቀሚያ በሚያደርጉ ፖለቲከኞች ነው የሚል እምነትም አለው።
እንደአዲስ እምነት በአድዋ ታሪክ ላይ የጠራ አንድነትና መግባባት የለም። ከምክንያቶቹ አንዱ ታሪክ ጸሐፊዎች የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ በግልፅና በሚዛናዊነት ያለማስፈራቸው ነው ይላሉ። የታሪክ መዛግብቱ በጦርነትና በድል ታሪኩ ላይ የእያንዳንዱን የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕዝብ ታሪክ በሚዛናዊነትና በግልፅ ከማስፈር ይልቅ አፄዎቹን ጨምሮ የጦር መሪዎቹ ላይ ብቻ ማትኮራቸው ሕዝብ የእኔ ነው ብሎ ትኩረት እንዳይሰጠው አድርጓል ብለውም ምናሉ።
በእመጓ፣ ዝጓራ እና ሌሎችም መጻሕፍት ደራሲነታቸው የሚታወቁት አለማየሁ ዋሴ ከወር በፊት ጦቢያ በተሰኘው ዝግጅት ላይ ተገኝተው ሲናገሩ የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የሚታዩትና በብዙኃኑ (እነ ፌስቡክ ከነመፈጠራቸውም በማያውቁ ኢትዮጵያዊያን) መካከል ያለው ስሜት እንደማይገናኝ አስረድተዋል። አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ ቢበዛ ከመቶ ሺሕዎች የሚያልፉ ተከታዮች እንደሌሉት በመጥቀስ የእሱ ሐሳብ ግን ከመቶ ሚሊዮን የሚልቀውን ኢትዮጵያዊ ሊወክል እንደማገባ ያስገነዝባሉ። ስለሆነም ‹ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ሆኑ› ለማለት ብዙኃኑን ማወቅና መረዳት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
በኢትዮጵያ የበይነ መረብ ተጠቃሚው ከአጠቃላይ ሕዝብ ቁጥሩ ጋር ሲነፃፀር ጥቂት መሆኑን የሚያነሱ አስተያየት ሰጪዎች ኢትዮጵያ ዛሬም በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ግዝፈት እንደነሳች መኖሯን ይናገራሉ። በሌላ በኩል ‹በጥባጭ ካለ› እንዲሉ ጥራዝ ነጠቅና ከፋፋይ ሐሳብ ያላቸውን (ጥቂትም ቢሆኑ) ወገኖች ማስተማርና መግባባት ላይ መድረስ ሊናቅ እንደማይገባ የሚያስገነዝቡ አሉ። ባለፈው ዓመት በወጣ ሪፖርት በኢትዮጵያ 16 ነጥብ አራት ሚሊዮን የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ሲኖሩ ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተጣቃሚዎች አሉ፡፡
መለያየት ለሰላም ዋስትና አይሆንም ብሎ የሚያምነው ያሬድ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲሁም ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ‹እንለያይ› ብለው ከተለያዩ በኋላ ወደ ጦርነት ለመግባት ዓመታት አልወሰደባቸውም ሲል በምሳሌ ያስረዳል። መከራ ከመምጣቱ በፊት መሰባሰቡና አንድነትን ማጠንከሩ ይበጃል ሲልም ይመክራል። እንዲህ ዓይነት በዓላት ከአደባባይ ተሻግረው ከቤተሰብም ጋር በየቤቱ ቢከበሩ የበለጠ የኢትዮጵያዊነት አጠንካሪ እንደሚሆኑም ያምናል።
ታሪኩ አሁንም የሕዝቡን ተሳትፎ መሰረት አድርጎ ቢጻፍ የሚሉት አዲስ ታሪኩን የበለጠ ለማኸዘብና በሕዝቡ ውስጥም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ልዕልናን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን ከምዕራባዊያኑ እያገኘች በአድዋ ጦርነት ምዕራባዊያንን እንዳንበረከከች በስፋት ለመናገር የሥነ ልቦና ዝግጅቱም አይኖራትም፣ ድጋፍ አድራጊዎቹ ምዕራባዊያንም ደስተኛ አይሆኑም ከሚል ነው።
ይሁንና ለዚህ ተብሎ ታሪክ መደበቅ የለበትም የሚሉት መምህሩ ኢትዮጵያ ታሪኳን ከማኸዘብ እኩል በፖለቲካውና በምጣኔ ሀብቱ ረገድ በራሷ መንገድ አሸንፋ መውጣትንም መቻል እንዳለባት ይመክራሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011