ድኅረ ቅኝ ግዛት የዴሞክራሲ ግንባታ

0
733

በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገራት ነጻ ከወጡ በኋላ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አለመቻላቸው ከቅኝ ግዛት አሉታዊ ዳፋዎች አንዱ ይሆን ወይ የሚለው ጥያቄ አወዛጋቢ ሆኖ ከርሟል። በተለይም ደግሞ የእንግሊዝ የቀድሞ ቅኝ ተገዢዎች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስኬት አስመዝግበዋል መባሉ ችግሩ ከቅኝ ግዛት ላይሆን ይችላል አስብሎ ነበር።

“The Legacy of Western Overseas Colonialism on Democratic Survival” በሚል ርዕስ ማይክል በርናንድ (ከፔንሲሊቫንያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ)፣ ክርስቶፈር ሬኖክ (ከፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ) እና ቲሞቲ ኖርድስትሮም (ከሚሲሲፒ ዩኒቨርሲቲ) በጋራ የሠሩት ጠለቅ ያለ ጥናት ለጥያቄው በርካታ መልሶችን ሰጥቷል። አጥኚዎቹ እ.ኤ.አ. ከ1951 እስከ 1995 ድረስ የተሞከሩ 136 የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታዎች ላይ ተመሥርተው በርካታ አወዛጋቢ ጥያቄዎችን በተጨባጭ ማስረጃ መርምረዋቸዋል። በመጨረሻም የደረሱበት በጥቅሉ ባሕር ተሻጋሪ ቅኝ ግዛት (Overseas Colonialism) በድኅረ ቅኝ ግዛት ዘመን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባት እንቅፋት እንደሆነ ነው።

አጥኚዎቹ፣ ቅኝ አገዛዝ ለድኅረ ነጻነት የዴሞክራሲ ግንባታ እንቅፋት የሚሆንባቸውን ሦስት መንሥኤዎች ለይተዋል። አንደኛው፣ ቅኝ ግዛት ልማትን ማዳከሙ ነው። ይህም በልማት እና በዴሞክራሲ መካከል መዛመድ በመኖሩ በቅኝ ተገዢ አገራት ዘንድ ዴሞክራሲ መፅናት እንዳይችል አድርጎታል ብለዋል። በኹለተኝነት ደረጃ፣ ብዙ ትልልቅ የዘውግ ቡድኖችና ሃይማኖቶች በተለያዩ ቅኝ ገዥዎች በመከፋፈላቸው (social fragmentation) እና እርስ በርስ የጠላትነት ስሜት እንዲያፈሩ ስለተደረጉ በጦርነት እና ፀብ ተጠምደው ዴሞክራሲ መገንባት እንዳይችሉ ሆነዋል። ከዚህም በላይ ደግሞ በቅኝ አገዛዝ ወቅት የነበረው አንባገነናዊ ስርዓት የየአገራቱን ልኂቃንም ይሁን ብዙኃን ለዴሞክራሲ እንዳይዘጋጁ (civil society እንዳይገነቡ) አድርጓቸው ነበር።

ይሁን እንጂ ተፅዕኖው እንደቅኝ ገዢ አገራቱ፣ እንደ ገዙበት ጊዜ ርዝመት የተለያየ መሆኑም በጥናቱ ታውቋል። በሚገርም ሁኔታ ለረዥም ዓመታት በቅኝ የተገዙ አገራት፣ ለአጭር ጊዜ ከተገዙት ይልቅ ለረዥም ጊዜ መዝለቅ የቻለ ዴሞክራሲ መገንባት መቻላቸው ተነግሯል። እንግሊዝ የገዛቻቸው (እና እንዲሁም ስፔን የገዛቻቸው) አገሮች የተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት ከነጻነት በኋላ መገንባት መቻላቸው ተነግሯል።

የሆነ ሆኖ ክርክሩ አሁንም ቀጥሏል። የሚያስገርመው ግን እንደኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዙ አገራት ሳይቀሩ ዴሞክራሲ መገንባት አለመቻላቸው ነው። ለዚህ መልስ አዳም ጎልድስቴይን የተባሉ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ምሁር በቅኝ ገዢ አገራት፣ በእጅ አዙር የሚደገፉት እና ረዥም ዓመታት የሚገዙት አምባገነን መሪዎቻቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑ ኦባማ ኢትዮጵያን በጎበኙ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ድረገጽ ላይ መጻፋቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here