መንግሥት የአፋርና ኢሳ ጎሳዎችን የግጭት ምንጭ እፈታለሁ አለ

0
595

በአፋርና ሱማሌ ኢሳ ጎሳዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉት ምክንያቶች ከወሰን ማካለል፣ መሬትና ማንነት ጥያቄዎች ጋር የተያያዙ መሆኑን የገለፀው የሰላም ሚንስቴር መንስኤዎቹን በታሪክና ጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት እንደሚሰራ አሳውቋል።

ከሰሞኑ ሚንስቴሩ ግጭቶቹን ማስቆም በሚቻልበት ዙሪያ ከአፋርና ሱማሌ ክልል ርዕሳነ መስተዳሮች እና የሃይማኖት አባቶች ጋር መክሯል። በምክክሩ እልባት ያስገኛሉ የተባሉ ሦስት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን በጋራ በሰጡት መግለጫ የተናገሩት ባለሥልጣናቱ በታሪክና ጥናት መሰረት መፍትሔ እስኪመጣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ እንዲጠናከር የሚያደርጉ ሥራዎች እንዲከወኑ መስማማታቸውን ገልፀዋል። በተጨማሪም በኹለቱም ክልሎች በኩል የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለእርቅና የሕዝብ ቅርርብ እንዲሰራ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል። በተቀመጡት አቅጣጫዎች እንደሚስማሙና ለተግባራዊነታቸውም እንደሚሰሩ የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጦፋ ዑመር እና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ ቃል ገብተዋል።

የግጭቶቹ መነሻዎች የመሬትና ማንነት ጥያቄዎች ስለመሆናቸው የጠቆሙት የሰላም ሚንስትር ዴኤታው ዘይኑ ጀማል ግጭቶቹን እያባበሱ ያሉት ‹‹የኮንትሮባድ ነጋዴዎችና የለውጡ አደናቃፊ ኃይሎች ናቸው›› ሲሉም ተደምጠዋል። ግጭቶቹ የሚነሳባቸው ቦታዎች ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ስፍራዎች መሆናቸውም ‹‹ለውጥ አደናቃፊዎቹ መጠቀሚያ አድርገውታል›› ሲሉ ከሰዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ከአንድ ወር በፊት በአፋር ክልል በሚገኙት አዳይቱ፣ ኡንደፎኦ እና ገዳማይቱ እያጋጠመ ያለውንና ለሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ግጭት ለማስቆም በሚል ከኹለቱ ክልሎች የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር ተወያይቶ የነበረ ቢሆንም ግጭቱ አለመቆሙን መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here