የመንግሥት ተቋማትን የስድስት ወር እቅድ አፈፃፀም ስትገመግም የሰነበተችው ሀረር የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ለችግር መንስኤ የሆኑ ተያየዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጋ እንደምትከርም አሳውቃለች።
ክልሉ የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት በተሻለ እንዲረጋገጥ የማድረጉን ተግባር ቅድሚያ እንደሚሰጥ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ኦርዲን በድሪ የሥራ ዕድል ፈጠራውም ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል። ሆኖም ብድር ከማመቻቸት ባሻገር ክትትል እንደሚፈልግ አንስተዋል፡፡ በክልሉ የመንግሥት ሰራተኞችም ጭምር እየተደራጁ ብድር በመውሰድ ወደጎንዮሽ ሥራ እየገቡ ነው የተባለ ሲሆን ይህን ለማረም ይሰራል ተብሏል፡፡
የመሬት አቅርቦትን ማሟላት እንደሚያስፈልግ ሁሉ ሕገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን መከላከል ቁልፉ ሥራ ስለመሆኑም ኦርዲን አንስተዋል።
በከተማ ልማት መሰረታዊ ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የሚስተዋለውን ሙስናና ሌብነት መታገል፣ ተጠያቂነትንም ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለውሃ፣ መንገድና መብራት የተመደበው በጀት ጥቅም ላይ እንዲውል መከታተልም ትኩረት ይፈልጋል ተብሏል። ለአብነትም በዚህ ዓመት ለገጠር መንገድ ግንባታ 40 ሚሊዮን ብር ቢመድብም እስካሁን ወደ ሥራ አለመገባቱ ተነግሯል።
ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011