ለ8.3 ሚሊዮን ዜጎች 1.3 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

0
348

በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ስምንት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን መድረሱን ያሳወቁት የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት የነዋሪዎችና ሰብኣዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ይፋ አደረጉ።

ድጋፍ ከሚፈልጉት ውስጥ አራት ነጥብ አራት ሚሊዮኑ የተመጣጠነ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 609 ሺሕ 961ዱ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ዋጋ ሳይከፍሉ አስቸኳይ ድጋፍ ሊደርስላቸው የሚገቡ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው።

ኹለቱ ተቋማት ባወጡት ሪፖርት መሰረት ኹለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮኑ ድጋፍ ፈላጊዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ናቸው።

የምግብና ገንዘብ እርዳታው ከሚያስፈልጋቸው ስምንት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ 46 በመቶ በኦሮሚያ፣ 22 በመቶ በሱማሌ፣ 12 በመቶ በአማራ፣ 10 በመቶ በደቡብ፣ 4 በመቶ በትግራይና አፋር ሲገኙ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሀረሪ እና ድሬ ዳዋ ይገኛሉ ሲሉ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ ባለፈው ሳምንት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ሰባት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች በድርቅ ምክንያት አስቸኳይ ድጋፍ ይሻሉ። ከእነዚህም አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮኑ በመንግስት፣ አንድ ነጥብ 79ኝ ሚሊዮኑ በዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮኑ ደግሞ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እየተረዱ ነው ብለዋል።

ለተረጅዎቹ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ መንግሥት 60 በመቶውን ይሸፍናል የተባለ ሲሆን ቀሪው ከዓለም ዐቀፍና ሌሎች የተራድኦ ድርጅቶች ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም ለጋሾች እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ ቀርቧል።

ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ መንግስት ለአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ 342 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የመደበ ሲሆን፥ ለጋሽ ድርጅቶች ደግሞ 595 ሚሊዮን ዶላር አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here