˝የአማራን ሕዝብ መብት፣ ጥቅም፣ ክብርና ነፃነትን ለማስከበር ፍቱን መፍትሔው መደራጀትና መወያየት ነው˝ ሲሉ አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደድር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) አስታወቁ።
የአማራን ሕዝብ መብት፣ ጥቅም፣ ክብርና ነፃነትን ለማስከበር ፍቱን መፍትሔው መደራጀትና መወያየት መሆኑን የክልሉ መንግሥት እንደሚያምን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ለዚህ ምቹ እንዲሆንም አበክረው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
ባለፉት ዓመታት በነበረው የሰብኣዊ መብት ጥሰትና የፍትሕ መጓደል የአማራ ሕዝብ ገፈት ቀማሽ ነበር ያሉት አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር በሕዝቡና በድርጅት የውስጥ ትግል ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል። ሆኖም ዛሬም ያልተመለሱ ጥያቄዎችና የፖለቲካ ትኩሳቶች አሉ ያሉም ሲሆን ለዚህም መንግሥትና ሕዝብ መተባበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
˝ከትግራይ ጋር የቆየውን ዘርፈ ብዙ አንድነትና ወንድማማችነት በማሳደግ ለጋራ ሰላማችንና ብልፅግናችን ተግባብተንና ተደጋግፈን እንድንሰራ የአማራ ሕዝብ ጠንካራ እምነትና ፍላጎት አለው˝ ሲሉም ለትግራይ ክልል በተለየ መልዕክት አስተላፈዋል።
ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክትም ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የክልሉን ሰላም እንዲያስጠብቁና ከክልሉ አልፎም በአገር ደረጃ ˝ወንድማማችነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን የምትዘሩ ብርቅዬና ተናፋቂ እርግቦች ሆናችሁ እንድትዘልቁ˝ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተንታኝና ምሁራንም የሚያንፀባርቋቸው ሐሳቦች አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ መልክ እንዲቀረፁ ጠይቀዋል።
ጠንካራ የመንግሥት አደረጃጀትን መፍጠር ቀዳሚ አጀንዳቸው መሆኑን የገለጹት አምባቸው ድክመት የታየባቸውን ተቋማትና ኃላፊዎች የማጠናከሩ ሥራም በቅርቡ እንደሚካሔድ አሳውቀዋል።
በሌላ በኩል ሕዝቡ ሕግን እንዲያከብርና እንዲያስከብር በማድረግ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራበታል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወደኋላ እንደማይሉም ተናግረዋል።
ላለፉት ወራት የጠቅላይ ሚንስትሩ የመሰረተ ልማት አማካሪ ሚንስትር ሆነው የከረሙት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ትናንት የካቲት 29 በአማራ ክልል ምክረ ቤት አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።
ክልሉን ከታኅሣሥ 2006 ጀምሮ በርዕሰ መስተዳድርነት ሲያገለግሉ የቆዩት ገዱ አንዳርጋቸው ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ የክልሉ መሪ ድርጅት፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጥያቄውን በመቀበሉ ነው አዲስ ርዕሰ መስተዳድር እንዲሾም ያደረገው። በዚህም አምባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆኑ ምክር ቤቱ ሾሟቸዋል።
አምባቸው መኮንን የአማራ ሕዝብን የትጥቅ ትግል ከመቀላቀል ጀምሮ በተለያዩ የድርጅትና የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ቆይተዋል። በፌደራል ደረጃ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስትር እንዲሁም ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ጠቅላይ ሚንስትርነት ሲመጡ በሚያዚያ 2010 የኢንዱስትሪ ሚንስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል። የጥቅምት 2011 አዲስ ካቢኔ አወቃቀርን ተከትሎ ከኢንዱስትሪ ሚንስትርነታቸው የተነሱት አምባቸው ለሳምንታት የሚመደቡበት ቦታ አለመታወቁ ሲያወዛግብና የብዙዎችን ቀልብ ሲስብ ነበር። ኋላም አምባቸው በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የጠቅላይ ሚንስትሩ የመሰረተ ልማትና ከተማ ልማት አማካሪ ሚንስትር ሆነው ኅዳር 18 መሾማቸው ይታወሳል።
አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው አምስት ጥናቶችን በምርምር ጆርናል ላይ ማሳተማቸው፣ ኹለት የኹለተኛ ድግሪ ያላቸው እንዲሁም የሦስተኛ ዲግሪ ምሩቅ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011