የይቅርታ አዋጁ በክልሎች የአፈፃፀም ችግር እንዳለበት ተገለፀ

0
536

የፌደራል የይቅርታና ምሕረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት ከይቅርታ አሰጣጥ ሒደት ጋር ተያይዞ አፈፃፀሙ ተመሳሳይነት እንደሌለውና ችግር እንደሚስተዋልበት ለአዲስ ማለዳ ገለፀ። ጽሕፈት ቤቱ ጨምሮ እንዳስታወቀው፣ እየታዩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የክልል ፍትህ ቢሮዎች ከፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጋር በመሆን ምክክር ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

በጉዳዩ ላይ የኢፌዲሪ የይቅርታና ምሕረት ቦርድ ዳይሬክተር ዘለቀ ዳላሎ፣ ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ ሲሰጡ ክልሎች የራሳቸው የይቅርታ አዋጅ በክልል ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ ገልፀው፤ ነገር ግን በአፈፃፀም ደረጃ ከፌደራልም ጋር ሆነ በክልሎች መካከል አንድ ዓይነት አፈፃፀም አለመኖሩን ተናግረዋል። አንድ ታራሚ ጉዳዩ በፌደራል እየታየ ግን በክልሎች እንዲታሰር የሚደረግበት አግባብ አለ ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ጊዜ የፌደራል መንግሥት ይቅርታ ለታራሚው በሚያደርግበት ጊዜ አብረው የታሰሩና ጉዳያቸው በክልል ፍርድ ቤት የሚታይ ታራሚዎች ተመሳሳይ ወንጀልም ቢሆን ይቅርታ ላይደረግላቸው እንደሚችል በምሳሌ ተናግረዋል። ይህም በታራሚዎች በኩል ቅሬታ እንዲነሳና በፍትህ አካላትም ላይ ጫና እንዲፈጠር መሆኑን ዘለቀ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የምሕረት አዋጁ ከወጣ በኋላ የፌደራል የይቅርታና ምሕረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት የሚል ስያሜ የያዘው መሥሪያ ቤቱ ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የስርቆትና ግድያ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላት ላይ ምንም ዓይነት ይቅርታ እንደማያሰጥ በፌደራል ደረጃ ቢገለፅም፤ በክልሎች ግን አሁንም በስርቆት ለተጠረጠሩ ግለሰቦች ይቅርታ የሚሰጥበት አግባብ እንዳለ ለመረዳት ተችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ታራሚ የይቅርታ ተጠቃሚ የሚሆነው በፌደራል ደረጃ 1/3ኛ የእስር ጊዜ ሲያሳልፍ መሆኑን የተጠቀሰ ሲሆን አንዳንድ ክልሎች ግን 1/2ኛ ወይም 1/4ኛ የሚሆነውን ለታሰረ ታራሚ የሚሰጡበት አካሔድ መኖሩን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል። የተጠቀሱትን የአፈፃፀም ክፍተቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም ክልሎች አዋጁን ለማስፈፀም በሚተጉበት ጊዜ ተመሳሳይ እና ወጥ የሆነ አፈፃፀም እንዲኖራቸው ከፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጋር እየተመከረበት እንደሆነና በቅርቡ መሻሻሎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

በአዋጅ ቁጥር 840/2006 የተቋቋመው የይቅርታ አዋጅ በዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን የማይመለከት እንደሆነ በግልፅ የተቀመጠ ሲሆን፤ የተፈፃሚነቱ ወሰን ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 78 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ በተቀመጠው መሰረት የፌደራል ጉዳዮችን በሚያስተናግዱ የክልል ፍርድ ቤቶች በሰጧቸው የመጨረሻ የወንጀል ቅጣቶችና የሞት ፍርድ የሰጠ የክልል ፍርድ ቤት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል። የፌደራል ይቅርታ ቦርዱም እንደአስፈላጊነቱ ለክልል ቦርዶች የይቅርታ ጥያቄን እንዲመረምሩ ለተመደቡ አካላት የሥልጣንና የተግባር ውክልና እንደሚሰጥም በአዋጁ ላይ ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here