‘‘ታራሚዎች በአባሎቻችን ላይ ጥቃት እስከመሰንዘር ደርሰዋል’’

0
341

አንዳንድ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞች ሰፈርና ጎጥ ለይተው የሚደባደቡ አልፎም ከውጭ አፍራሽ ኃይሎች ጋር ትስስር ያላቸው ሆነው በአባሎቻችን ላይ ጥቃት እስከመሰንዘር የደረሱበት ሁኔታ ተከስቷል ሲል የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተደደር አስታወቀ።

ይህንን ያደርጉ የነበሩት የቀድሞ አመራሮች ናቸው ያለው፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ በአገራችን ከተጀመረው አዲስ የለውጥ ሒደት ውስጥ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ ለመወጣት፣ በማረሚያ ቤቶች የሕግ የበላይነትን በማክበርና የታራሚዎች ሰብኣዊ መብት ጥሰት ችግሮች በማስወገድ፣ ሕዝብና መንግሥት የሚተማመኑበት ተቋም ለመፍጠር፣ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ በማደራጀትና መዋቅሩን በማስፋት፣ አዲስ አመራሮችን በመመደብ የሪፎርም ሥራዎች እንዲከናወኑ እየሠራ ነው ሲሉ የአስተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አዲሱ ጴጥሮስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በማረሚያ ቤቶች የነበረው ሁኔታ፣ የለውጥ ሒደቱ ሲጀምር በተቋሙ የነበረውን የማረሚያ ቤቶች የጸጥታ ሥጋት፣ አሉባልታና ውዥንብር የተሞላበት፣ በአባላቱና በታራሚው መካከል አለመግባባት እና የሆነ በጥርጣሬ የመተያየት መንፈስ የሰፈነበት እንደሆነ የሚያትተው የተቋሙ የ2011 ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በአመራሩ በማረ/ቤቶች የሚታየውን የታራሚዎች የሰብኣዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን አለመቀበልና ውጫዊ የማድረግ ችግሮች እንደነበሩበት ጠቁሟል።

ሪፖርቱ አክሎም፣ የማረሚያ ቤቱ አባላት በታራሚው ላይ የበቀል ስሜት የማሳየት፣ በሕግ ታራሚዎችም ከዚህ ባልተለየ የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ በይቅርታና በምሕረት አሰጣጥ ሒደቱ ላይ ጫና በመፍጠር ለመፈታት ወይም ለማስመለጥ መሞከር፣ በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶችም መኖሪያ ቤቶችን በማቃጠል በተፈጠረው ኹከት የንብረትና የሰው አካል እስከ መጉዳት ያለፈ ችግር እንደነበርና፣ በተለያዩ ሙያዎች ተመድበው የሚሰሩ አባሎችም ወደ ታራሚው ቤቶች ገብተው ሥራዎቻቸውን ለማከናወን የሰጉበት ሁኔታዎች ተፈጥረው እንደነበር ዘርዝሯል።

በየደረጃው የሚገኘውን አመራርና ፈጻሚ በማረጋጋት ወደ መደበኛው የማረም ማነጽ ሥራና ቀጣይ የሪፎርም ሥራዎች ለመግባት እንዲቻል አጠቃላይ ግምገማ በማድረግ፣ በችግሮቹ ዙሪያ የጋራ መግባባት በመፍጠርና የተዛባውን አመለካከት ለመቅረፍ ሁሉም አመራርና አባል በግምገማዊ ሥልጠና እንዲያልፍ ተደርጓል ያሉት አዲሱ፣ ከችግሮቻቸው በቶሎ ለመታረም ዝግጁ ያልሆኑትን አመራሮች ከቦታ በማንሳት በዲስፒሊን እንዲጠየቁ፣ የከፋ ችግር ያለባቸው በሕግ እንዲጠየቁ ተደርገዋል ብለውናል።

በአባላቱና በታራሚው ዘንድ የሚስተዋለውን የእርስ በርስ መጠራጠርና በጠላትነት የመተያየት አዝማሚያ ለማስወገድ፣ ብሎም የሰብኣዊ መብት ጥበቃ ግንዛቤ ክፍተት ለመቅረፍ ከተለያዩ አጋርና ተባባሪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ፈጻሚ ሠራተኞች በሰብኣዊ መብት ጥበቃ እና በማረም ማነጽ ሥራዎች ተከታታይ ስልጠናዎች መሰጠቱንም አክለው ገልጸዋል።

የሕግ ታራሚዎች የሚያነሱት የፍትሕ ጥያቄ በተሟላ መልኩ ለመመለስ ይቻል ዘንድ ከፍርድ ቤቶች፣ ከፖሊስ፣ ከዐቃቤ ሕግ እና አስተዳደሩ በጋራ ሥራዎች የሚታዩ ክፍተቶችን በጋራ ምክክር መድረክ ለመፍታት ጥረት መደረጉን የሚያብራራው ሪፖርቱ፣ በተከሰተው አለመረጋጋት የአካባቢውን ሰላም ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በማረሚያ ቤቶች ሰላምና ደህንነት ሊፈጥር የሚችለውን የጸጥታ ስጋት አስቀድሞ ለመከላከል ከፌደራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ማረሚያ ቤቶቹ፣ በለውጥ መሳሪዎች አተገባበር ላይ በቂ እውቀት፣ አመለካከትና ቁርጠኝነት አለመኖሩ አደረጃጀቶቹ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ያለመቻል፣ ክልሎችና ማዕከላት ወቅታዊና ጥራት ያለው የሕግ ታራሚዎችና ቀጠሮ እስረኞች ስታቲስቲካዊ መረጃ አለማቅረብ፣ የባለሙያዎች መልቀቅ፣ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኛ የማረም ማነጽ ሥራዎች የኔ ሥራዎች ናቸው፣ ብሎ በእምነት ያለመቀበል ችግሮችና የተፈለገውን ያህል ውጤታማ ያለመሆን ችግሮች እንዳሉባቸው ሪፖርቱ አስረድቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here