የመንግሥት የበጀት ጉድለት ወደ 99 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሊያድግ ነው

0
614

– በአገሪቷ ታሪክ ትልቁ የሆነው ጉድለቱን ለማሟላት መንግሥት ብድር ውስጥ መግባቱ እንደማይቀር ተገልጿል
– የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሥጋታቸውን ገልፀዋል

የሚኒስቴሮች ምክር ቤት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ክፍያ ለመፈፀምና ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች 33 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ማፅደቁን ተከትሎ የመንግሥት በጀት ጉድለት ወደ 99 ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ሊያሳደገው እንደሚችል ተጠቆመ።

ጉድለቱ የአዲስ አበባን በጀት ኹለት እጥፍ ጋር የሚስተካከል ሲሆን መንግሥት ባለፈው በጀት ዓመት አስመዝገቦ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ33 ቢሊዮን በር ከፍ ያለ ነው። በታሪክ እስከ ዛሬ ከተመዘገበው ትልቁ ጉድለት የአሁኑ በጀት ዓመት ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ጠቁመዋል።

ጉድለቱ በ2011 በጀት ዓመት አገሪቷ ታስመዘግባለች ተብሎ ከታቀደው አጠቃላይ ምርት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ 5 ነጥብ 3 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ማወቅ ተችሏል። ይህ መንግሥት በኹለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ካስቀመጠው ዕቅድ ጋር የሚፃረር ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አንደሚገልፁት ይህ ዓይነቱ ጭማሪ የመንግሥት በጀት የማረቀቅ ሒደት መፈተሸ እንዳለበት የሚጠቁም ነው።
ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በዚህ ከሚያምኑት ባለሙያዎች መካከል ሲሆኑ በዚህም የተነሳ በፓርላማ የሚፀድቀው ወጪ ከአገሪቷ ገቢ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ ለባለፉት አራት ዓመታት ተጨማሪ በጀት መንግሥት ለማፀደቅ መገደዱን አውስተዋል።
ይህም አሁን በአገሪቷ ካለው የምግብና ሌሎች ዕቃዎች የዋጋ ንረት ጋር ተዳምሮ የዋጋ ግሽበትን ሊያባብስ እንደሚችል ዓለማየሁ ተናግረዋል።

በርግጥ፤ የዋጋ ግሽበት በዚህ ዓመት ትንሽ መረጋጋት ቢያሳይም ባለፈው ወር 10 ነጥብ 9 ሆኖ መመዝገቡ አሳሳቢ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በተጨማሪም፤ ለባለፉት ኹለት ዓመታት እየተመዘገበ ያለው ባለኹለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት መንግሥት በኹለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ካቀደው ጋር የሚፃረር ነው።

ይህንን ታሳቢ ያደገረ አይደለም ተብሎ የተተቸው ሰኞ፣ የካቲት 25 የፀደቀው ተጨማሪ በጀት ተሰርተው ክፍያቸው ላልተከፈሉ ፕሮጀክቶች ለማዋል፣ የሕዝብ ቆጠራ ወጪን ለመሸፈን፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለማካሔድና የፕሮግራም በጀት ግቦችን ለማሳካት እንደሚውል ተገልጿል።

ይሁን እንጂ በፓርላማ እንዲፀድቅ የተላከው በጀት አገሪቷ ከሰበሰበችው ገቢ አንፃር የተጋነነ ነው ተብሏል።

ባለፈው ዓመት ከፀደቀው ተጨማሪ በጀት ጋር ሲነፃፀር ከ20 ቢሊየን ብር ልዩነት መኖሩ መንግሥት ካለው ታክስና ሌሎች ገቢዎች የመሰብሰብ አቅም አንፃር መንግሥትን ሌላ አማራጭ እንዲያይ ሊገፋፋው ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች ይገለፃሉ።

በተለይም እንደ ፋይናንስና ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ ገለፃ መንግሥት የበጀት ጉድለቶች ለመሙላት ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ አልያም በተዘዋዋሪ በልማት ባንክ ወይም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ሊበደር ይችላል። ብድሩም ለመንግሥት በጊዜው ፍላጎቱን ለሟሟላት ቢጠቅም የዋጋ ግሽበትን ሊያባብስ ይችላል ብለዋል።

በታኅሣሥ ወር ለመጨረሻ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው መንግሥት ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ከአገር ውስጥ አበዳሪዎች ወስዷል። በተጨማሪም ባለፈው ወር አጋማሽ የወጣው የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንደሚያሳየው እስከ መስከረም 2011 መንግሥት ከባንኩ የወሰደውን ብድር 103 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መድረሱን አመላክቷል። ይህ ከባለፈው በጀት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር 16 ቢሊየን በር ጭማሪ አለው።

ይህ ዓይነቱ ጭማሪ በቅርቡ በፓርላማ ያፀድቃል ተብሎ ከሚበቃው ተጨማሪ በጀት ጋር ተደምሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያደርስ ይቸላል ያሉት ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዓለማየሁ ናቸው ።

በተቃራኒው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ተኬኤ አለሙ (ዶ/ር) መንግሥት ተጨማሪ በጀት ማፅደቁን በሚገባ እስካዋለው ድረስ ችግር የለውም ይላሉ። እንደ ባለሙያው ገለፃ ገንዘቡ የቀዘቀዘው ኢኮኖሚ ለማነቃቀት ከዋለ እና ወደፊት የሚያወጣው ውጤት በቂ ከሆነ የከፋ አሉታዊ ተፅዕኖ አያመጣም ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here