ጋምቤላን ከፍተኛ የኮንዶም እጥረት ገጠማት

0
851

– 900 ሺሕ ኮንዶም ቢሰራጭም እጥረቱ አልተቀረፈም

በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት በቻ 900 ሺሕ ኮንዶም ቢሰራጭም በክልሉ የኮንዶም እጥረት መከሰቱ ተሰማ። እጥረቱ በኤችአይቪ /ኤድስ ስርጭት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አሳሳቢ መሆኑም እየተነገረ ነው።

የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ካን ጋልዋክ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በጋምቤላ ክልል አንዳንድ ወረዳዎች የኮንዶም እጥረት አጋጥሟል። እንዲህ ዓይነት እጥረት በክልሉ በተደጋጋሚ የሚከሰት መሆኑን ያሳወቁት ቢሮ ኃላፊው ‹‹ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከክልሉ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሥራት ላይ ነን ሲሉ አክለዋል።

በክልላችን የኮንዶም ተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ነው የሚሉት ካን አንዳንድ ጊዜ በሚፈጠሩት የሥርጭት ችግሮች ተጠቃሚው በሚፈልገው ልክ እንዳያገኝ አድርጎታልም ይላሉ። አክለውም የስርጭት ችግር አለ ሲባል ግን የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የፌደራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዳንኤል በትረ የኮንዶም እጥረት በአንዳንድ ክልሎች እየተፈጠረ መሆኑን አምነው፤ እጥረቱ ከስርጭት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እንደ አማራ ክልል ያሉ አንዳንድ መንግሥታት በክልላቸው የኮንዶም እጥረት ሲፈጠር በክልሉ በጀት ግዢ በመፈጸም እንደሚያከፋፍሉም ገልፀዋል።

ክልሎች የኮንዶም እጥረት መከሰቱን ሲያሳውቁ ተቋማቸው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስታወቁት ዳንኤል፣ ‹‹ተቋማችን የስርጭት ስራ አይሰራም፤ የኛ ሥራ ክልሎች የኮንዶም አቅርቦት እንዲኖራቸው ግዢ እንዲፈጸም የማስተባበር ነው›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በበኩሉ ምንም ዓይነት የኮንዶም እጥረት የለም ሲል አስተባብሏል። አሁን ላይ ያለው የኮንዶም ስርጭት ባለፉት ኹለት ዓመታት ከነበረው የኮንዶም አቅርቦት በእጅጉ የተሻለ ነው ሲልም ለአዲስ ማለዳ ምላሽ ሰጥቷል።

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ በፀሎት የማነ በጋምቤላ ክልል እጥረት ተከስቷል መባሉ አግባብ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።

በ2008 በጀት ዓመት በአገሪቱ 407 ሺሕ 520 ኮንዶም ሲሰራጭ፣ በ2009 ደግሞ ስድስት ሚሊዮን 637 ሺሕ 200 እንዲሁም በ2010 በጀት 22 ሚሊዮን 863 ሺሕ 700 ኮንዶም መሰራጨቱን በፀሎት ይናገራሉ። በ2008 እና 2009 በጀት ስርጭቱ የቀነሰበት ምክንያትም የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በኮንዶም ላይ ባገኘው የጥራት ችግር እንዳይሰራጭ በማድረጉ ነው ብለዋል። ባለሙያዋ አክለውም ለጋምቤላ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ 900 ሺሕ ኮንዶም መሰራጨቱን አሳውቀዋል። ይህም በ2008 በጀት ዓመት ለመላው ኢትዮጵያ ከተሰራጨው እጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ በአውሮፓዊያኑ 2016 ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ዓመት ካሉት ዜጎች 54 ከመቶ የሚሆኑት ወንዶች ኮንዶም ተጠቃሚዎች ናቸው። ይህ አሃዝ፣ በአውሮፓዊያኑ 2010 ከነበረው የቀነሰ መሆኑን የሚያሳየው ሪፖርቱ፣ በ2010 ዓመት 67 በመቶዎቹ የኮንዶም ተጠቃሚዎች እንደነበሩ አስታውሷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከ21 ሺሕ በላይ አዳዲስ ሰዎች በኤችአይቪ እንደሚያዙና በየዓመቱ 26 ሺሕ ሰዎች በኤች አይቪ ኤድስና ከእርሱ ጋር ተያያዥ በሆኑ የጤና እክሎች እንደሚሞቱ የኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍ) ሪፖርት ያመለክታል።

ከኹለት ዓመት በፊት በተከሰተው የኮንዶም እጥረት፣ በአንዳንድ ከተሞች ምሽት ላይ አንድ ፍሬ ኮንዶም እስከ 40 ብር ይሸጥ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here