በሐረር መሬቱ የእኛ ነው ያሉ ቡድኖች ሕጋዊ ቤቶችን ማፍረሳቸው አስቆጣ

0
956

• የመንጋ አካሔድ ተስተውሏል ያለው ክልሉ ቤት ፈረሳው የእኔ ፍላጎት አይደለም ብሏል

በሐረር ከተማ ቀበሌ 16 ቤቶቹ የተሰሩት በእኛ መሬት ላይ ነው ያሉ ሕገ ወጥ ቡድኖች መጤ ናቸው ያሏቸውን ነዋሪዎች ሕጋዊ ቤቶችንም ጭምር ማፍረሳቸውን ተከትሎ አለመረጋጋት መከሰቱ ተገለጸ። የሐረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ቤት ፈረሳው የክልሉ ፍላጎትና እርምጃ አለመሆኑን ገልፆ የመንጋ አካሔድ ነው ሲል ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል።

አዲስ ማለዳ ሐረር ከተማ ከሚገኙ ምንጮቿ እንደሰማችው ባለፈው እሁድ የካቲት 24/2011 ቀበሌ 16፣ ከሐረር ቢራ ፋብሪካ እስከ ሃኪም ጋራ በሚሰኙ አካባቢዎች ‹መሬቱ የእኛ ነው› የሚሉ ቡድኖች ተሰብስበው የነዋሪዎችን ቤት የማፍረስና ደንን የመጨፍጨፍ ድርጊት መፈፀማቸውን ተከትሎ በከተማዋ አለመረጋጋት ተከስቶ ነበር።

ቡድኖቹ ‹ቤቶቹ የተሰሩት የእኛ የቀደመ መሬት ላይ ነው እና ቤት የሰሩት ሰዎች ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰፋሪዎች ናቸው› በሚል ከመንግሥት እውቅና ውጭ በሕገ ወጥ መንገድ ቤት የማፍረስ ዘመቻ መክፈታቸውን የገለጹት ምንጮቻችን ይህን ተከትሎ በከተማዋ የጸጥታ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል። ስለ አፍራሽ ቡድኖቹ የጠየቅናቸው ምንጮች ቡድኑ በግልጽ ባይታወቅም ‹መሬቱ ከዚህ ቀደም የእኛ ነበር፣ ስለዚህ መሬታችን ላይ ቤት የሰሩት ከሌላ አካባቢ የመጡ በመሆናቸው መሬቱን ነጥቀን እንደገና እንሸጣለን› የሚሉ እንደሆኑም አክለዋል።

ከቤት በተጨማሪም በመንግሥትና ሕዝብ ትብብር የለማን ደን በመጨፍጨፍ መሬቱን እንሸጣለን በሚል የወሰዱት እርምጃ ከነዋሪው በኩል ቁጣን ቀስቅሶ እንደነበር፣ ኋላም የፌደራል የፀጥታ ኃይል አባላትም ጭምር ጣልቃ ገብተው አፍራሾቹን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረጋቸውም ተሰምቷል። የተወሰኑትንም በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ ምንጮች አክለዋል። ይህን ተከትሎም የነበረው ቤት ፈረሳ ሊቆም መቻሉን ተናግረዋል።

ስለጉዳዩ አዲስ ማለዳ ማብራሪያ የጠየቀቻቸው የሀረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽ ቢሮ ኃላፊ አብዱልሀኪም አብዱልመሊክ ‹‹የመንጋ አካሔድ እየተኬደ ነበር›› ያሉ ሲሆን፣ ቤቶችን የማፍረስ እርምጃው ከክልሉ መንግሥት እውቅናና ፍላጎት ውጭ እንደሆነም አስረድተዋል። ቤት ሲያፈርሱ የነበሩት ሕገ ወጥ ቡድኖችና መሬቱ ድሮ የእኛ ነው የሚሉ ወገኖች መሆናቸውን ያረጋገጡት ቢሮ ኃላፊው ስለዝርዝር ማንነታቸው ግን መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል። ቤት የማፍረሱ ሕገ ወጥ ተግባር ለአንድ ቀን የተካሔደ እንደነበርና አሁን ላይ መቆሙን ያነሱት አብዱልሃኪም ከፈረሱት ቤቶች መካካል በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ሊኖሩ ቢችሉም ሕጋዊ ቤቶች እንዳሉበት አስገንዝበዋል። ሕገ ወጥም ቢሆኑ እንኳን እርምጃ የመውሰዱ ድርሻ የመንግሥት ብቻ እንደሆነም አንስተዋል። ስለፈረሱት ቤቶች ቁጥር መረጃው ገና እንዳልደረሳቸውም አክለዋል።

በሀረር 150 ሄክታር መሬት ሲወረር 150 ቤቶች ደግሞ በሕገ ወጥ ግንባታ መገንባታቸውን የገለጹት አብዱልሃኪም ይሁንና በመንግሥት ደረጃ የተጀመረ እርምጃ አለመኖሩን አሳውቀዋል። የክልሉ መንግሥት ሕገ ወጦቹ ቤቶችና መሬት ወረራ ላይ ከነዋሪው ጋር በመወያየት መፍትሔ ለማስቀመጥ ግብረ ሃይል ማቋቋሙን በመግለፅም ሕዝቡን ሳያወያይ ምንም ዓይነት እርምጃ እንደማወስድ አረጋግጠዋል።

ሰው ቤት የመገንባትና መጠለያ የማግኘት ሰብኣዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ያሉት ቢሮ ኃላፊው በሕገወጥ መንገድ ቤት የገነቡ ዜጎችም ሆኑ ሌላው ቤት ፈላጊ ቦታ ተመቻችቶላቸው ሕጋዊ ቤት እንዲገነቡና ሕገወጥ ቤታቸውን በራሳቸው እንዲያፈርሱ አማራጭ ይቀመጥላቸዋልም ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ዜጎች መኖሪያ ቤት እንዲገነቡ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን መመሪያ የማውጣት ሥራ መከወኑን ያነሱት ኃላፊው በሕገወጥ ቤት ያሉ ነዋሪዎች በሕጋዊ መንገድ ቤት እንዲገነቡ ክልሉ እያመቻቸ መሆኑንም አስረድተዋል።

የክልሉ መንግሥት ቤቶችን አፍርሶ ነዋሪዎቹን ሜዳ ላይ እንደማይጥልና ፍላጎቱም እንደሌለው የገለጹት አብዱልሃኪም በሕገወጥ መንገድ የተገነቡት ቤቶች ግን ከሚፈለገው የከተማ መሪ እቅድ ጋር ካልተስማሙ በምንም መልኩ ሕጋዊ አይደረጉም ብለዋል። ክልሉ ‹‹የፖለቲካ ትኩሳትን በሚፈጥር አግባብ ቤት እንደማያፈርስም›› ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። ይልቁንም ነዋሪዎቹ አምነውበትና የሚቀርብላቸውን ሕጋዊ አማራጭ መርጠው ሕገወጥ ግንባታዎቹን በራሳቸው እንዲያፈርሷቸው ይደረጋል ሲሉም አክላዋል።

የሰሞኑ ድርጊት ግን የክልሉን መንግሥት እንደማይወክልና ፍላጎቱም እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here