ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍልና የአዲስ አበባ ይገባኛል ጥያቄ

0
930

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ የሚሾርባት ከተማ ነች። አንድ ጊዜ ጋም ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚለው ከአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ የልዩ ጥቅምም ሆነ የባለቤትነት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት ከሚነሱ አነታራኪ ጉዳዮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ሳምሶን ኃይሉ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታን መሰረት አድርገው ከሚነሱት ጥያቄዎች ባሻገር እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠውን የአዲስ አበባ ሀብት ምንጭና የዚሁ ሀብት ፍትሓዊ ክፍፍል ጉዳይ እንደሌሎች ትርክቶች ሁሉ ተገቢውን ቦታ ማግኘት አለበት ሲሉ መከራከሪያ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአዲስ አበባ ላይ የሚነሳው የልዩ ጥቅም እና የይገባኛል ጥያቄ የፖለቲካውን እንድምታና ትኩሳት ሲቆጣጠረው ይስተዋለል። በመገናኛ ብዙኀንም ሆነ ማኅበራዊ ትስስር አውታሮች የሚቀርቡ የመከራከሪያ ነጥቦች በአብዛኛው ታሪክን እና የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ማዕከል ያደረጉ ናቸው።

ታሪክን የሚያጣቅሱ ፖለቲከኞችም ሆኑ የመብት ተሟጋቾች አዲስ አበባ የምትገባው ለቀድሞ ባለቤቶቿ መሆኑን ይስማማሉ፤ ነገር ግን የቀድሞ ባለቤቶቿ ማንነት ላይ ልዩነት አላቸው። በአንድ በኩል ያለው አካል ከአፄ ሚኒሊክ ዘመን በፊትም ቢሆን ከተማዋ የኢትዮጵያ መናገሻ ሆና መገልገሏን በማስረዳት አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኗን ያስረዳሉ። የሁሉም ስለሆነች የትኛውም አካል ለብቻው የይገባኛል ጥያቄ ማንሳት አይችልም ብለውም ይደመድማሉ። የተቀሩት ደግሞ በሚኒሊክ ዘመን በተካሔደው የአገር ማስፋፋት ዘመቻ ቀድሞው የነበሩት ሕዝቦች ማለትም ነባር የኦሮሞ ሕዝቦች ቀስበቀስ ከከተማዋ መፈናቅቀላችውን በመግለፅ የቀደሙት ሕዝቦች የማያወላውል ባለቤትነትን አጉልተው ይናገራሉ።

በሌላ በኩል የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ተንተርሰው የሚሞግቱት ደግሞ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ነች ይላሉ። ስለዚህም ኦሮሚያ ክልልም ሆነ ሌላ ክልል ምንም ዓይነት ጥቅም ሆነ የባለቤትነት ጥያቄ አዲስ አበባ ላይ ማንሳት አይገባቸውም ብለው ያምናሉ። ይህንን አቋም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓሪቲ (አዴፓ) እናየመብትተሟጋቾች ሲያንፀባርቁት ይስተዋላል።

አሁን ያለውን የከተማዋን የሕዝብ አሰፋፈር መሰረት አድርገው የሚከራከሩም አልጠፉም።

የአዲስ አበባን ጥያቄ ለመመለስ ከላይ የተጠቀሱትንም ጨምሮ ሌሎች ነጥቦች በስፋት እየተነሱ ቢሆንም በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚገባቸው ጉዳዮች ማለትም የከተማዋ የሀብት ምንጭ እና የሀብቱ ተጠቃሚወች ማንነት እስካሁን ድረስ የሚገባቸውን ቦታ አላገኙም። በእኔ ዕይታ የከተማው የይገባኛል ጥያቄም ሆነ ልዩ ጥቅም የመሻት አካሔድ በመሰረቱ የሚመነጨው የተለያየ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍልን በአዲስ አበባ ላይ ለማስጠበቅ ካላችው ፍላጎት የተነሳ ነው።

ይህን ለመረዳት በኢትዮጵያ የሚገኘውን የከተሞች ስብጥርና እድገት መመልከት ያስፈልጋል። በማዕከላዊ ስታትስቲስ ኤጀንሲ መስፈርት መሰረት 100,000 ሰዎች በላይ የሰፈሩበት ቦታ ሁሉ ከተማ ተብሎ ሊጠራ ይችላል በዚህ መስፈርት ከሔድን በኢትዮጵያ 16 የሚጠጉ ከተሞች አሉ። በኦሮሚያ ክልል ብቻ ቢሸፍቱ፣ አዳማ፣ ጅማ እና ሻሸመኔ የመሳሰሉ ከተሞች ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ተደምረው የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር ጋር አይደርሱም። በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል። ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ደሴ የሚኖረው የሕዝብ ብዛት ተደምሮ ከአንድ ሚሊዮን አይበልጥም። በሌላ ቋንቋ አንድ እንኳን አዲስ አበባን ሊወዳደር የሚችል ከተማ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም።

 

ከውስጥም ሆነ ከብድር የሚገኘው ገንዘብ የተሰበሰበው ወይንም ወደፊት የሚሰበሰበው ግን በመሰረተ ልማቶቹ ተጠቃሚዋች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዜጎች ነው

 

ከሕዝብ ብዛት በዘለለ የእነዚህ ከተሞች የምጣኔ ሀብት፣ ዓመታዊ በጀት፣ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የመዋዕለ ነዋይ (ʻኢንቨስትመንትʼ) ፍሰትም ሆነ የመሰረተ ልማት እድገት ከአዲስ አበባ ጋር በትንሹም እንኳን ሊወዳደር አይችልም። ለምሳሌ አዲስ አበባ ግማሹን የአገሪቱን ዓመታዊ ጥቅል ምርት ታዋጣለች። በተጨማሪም 40 እስከ 45 ፐርሰንት የሚሆነውን አጠቃላይ የአገሪቱ ኢንቨስትመንት አዲስ አበባ ላይ ፈሷል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከተማዋ ግማሽ የሚሆነውን የአገሪቱ ንግድ መተላለፊያ ማዕከል ከመሆኗም በላይ አብዛኛው የመሰረተ ልማት ግንባታ ተጠቃሚ ነች። ከአዲስ አበባ በእድሜ የሚበልጡ ከላይ የተጠቀሱትንም ጨምሮ ብዙ ከተሞች በአገሪቷ ውስጥ ቢኖሩም ይህንን እድል ግን አንዳቸውም ለማግኘት አልታደሉም።

ይህ የሚያሳየው በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አውራ ከተማ ብቻ እንዳለ ነው። ይህ የአንድ አውራ ከተማ (urban primacy)ብቻ መኖር የሚመነጨው ከባለፉትና አሁን ካለው መንግሥታት ካራመዱት የዘገየና የተዛባ የከተሞች ዕቅድና የእድገት ፖሊሲ ነው። ችግሩ የሚጀምረው የከተሞች ማስፋፊያ መርሃ ግብር በቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ መጨረሻው የግዛት ዘመን መተግበር ቢጀመርም ደርግ በተከተለው አሃዳዊ ስርዓት ምክንያት ውጥኑ ተስተጓጉሏል። ከደርግ የ17 ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በኋላ የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥትም ቢሆን የከተማ ማስፋፊያ መርሃ ግብር በሰፊዊ ለመተግበር ከዐሥር ዓመታት በላይ ፈጅቶበታል። ከተጀመረም በኋላ በተንሸዋረረና በተዛባ አቅጣጫ በመጓዙ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም።

እንዲህ ባለ የተዛባና ለብዙ ዓመታት በተንቀረፈፈ የፖሊሲ ትግበራ ምክንያት አዲስ አበባ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት፣ የንግድ እና የመዋዕለ ነዋይ ብቸኛ መናኻሪያና መዳረሻ ብቻ ሳትሆን ዋነኛዋ የመሰረት ልማቶች ባለቤትም ሆናለች። ይህም የተገኘው ከከተማዋ ነዋሪዎች በተገኘ ሀብት ብቻ ሳይሆን መንግሥትና ሁሉም ዜጎች ቢያንስ ላለፉት 50 ዓመታት አዲስ አበባ ላይ ትልቅ ሀብት ፈሰስ ሲያረጉ በመቆየታችው ነው። ይህን ለመገንዘብ የአዲስ አበባን የመጣኔ ሀብታዊ፣ የንግድ፣ የመዋዕለ ነዋይ እና የመሰረተ ልማት እድገት ምንጮች መቃኘት ያስፈልጋል።

ትልቁ የአዲስ አበባ ኢኮኖሚ የሚመነጨው ውስጧ ካቀፈቻቸው የንግድ፣ የፋብሪካዏች፣ ቱሪዝምና የመሰረተ ልማት አውታሮች ነው። እያንዳንዱ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ወደ ከተማዋ የሚገቡ ዕቃዎች ሁሉ ቀረጥ የሚጣልናቸው አዲስ አበባ ነው። ይህ ማለት አንድ በምeራብ ኢትዮጵያ ጥግ የሚኖር ሰሊጥ የሚያመርት ገበሬ ለከተማይቱ ገቢ መጨመር አስተዋፆ አለው ማለት ነው።

በአብዛኛው ወደ አዲስ አበባ ተስበው የመጡ ፍብሪካዎች ከመንግሥት ድጎማ በማበረታቻና በቀረጥ እፎይታ መልክ ያገኛሉ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥም የመንግሥትና የአገር ገቢ መቀነስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ እኩል ተፅዕኖ ሲያሳድርበት ፋብሪካዎቹ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል ግን ጥቂቶችን ብቻ ይጠቅማል።

በተጨማሪም አዲስ አበባ ውስጥ የሚታየው የመሰረተ ልማት ግስጋሴ ከመንገዶች እና እንደ ባቡር የመሰሉ የትራንስፖርት አማራጮች የተሠሩትም ሆነ የሚሠሩት በራስ አቅምና ከውጭ በብድር በተገኘ ገንዘብ መሆኑ ሊጤን ይገባዋል። ከውስጥም ሆነ ከብድር የሚገኘው ገንዘብ የተሰበሰበው ወይንም ወደፊት የሚሰበሰበው ግን በመሰረተ ልማቶቹ ተጠቃሚዋች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዜጎች ነው። በሌላ ቋንቋ አዲስ አበባ አሁን የምትገኝበት ደረጃ ለማድረስ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋፅኦ አድርጓል። አዲስ አበባ የሁሉም አሻራ ቢኖርባትም ፍሬዋን ግን ለመቅመስ የታደሉት በከተማዋና በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦች ናችው።

ይህንን እውነታ ከግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ አይደለም በታሪክና በሌሎች ምክንያቶች ከአዲስ አበባ ጋር ቁርኝት ያላችው የኅብረተሰብ ክፍሎች በአራቱም ጥግ የሚኖሩ የአገሪቱ ሕዝቦች ጭምር ከተማዋ ከምታፈራው ፍሬ የተቋዳሽነት ጥያቄ ቢያነሱ የሚያስገርም አይሆንም።

ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የአንድ አውራ ከተማ መፈጠር ተከትሎ ለሚመጡ ችግሮችን ተዳርጋለች የሚባለው። የአገሪቱ ሀብት ወደ አንድ አቅጣጫ በብዛት እንዲፈስ ስለተደረገና ሌላ ከአዲስ አበባ ጋር የሚወዳደር ከተማ ስለሌለ ከከተማዋ ውጭና በርቀት የሚኖሩ ዜጎች ጭምር አዲስ አበባን ብቻ እንዲያበለፅጉ ተፈርዶባቸዋል። አዲስ አበባ የምትለግሰውን ዕድል ለማግኘትም በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በማይታይ ሁኔታ ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማዋ ይጎርፋሉ።

በተቃራኒው ደግሞ ብዙ ዓመታት ያስቆጠሩ እንደ ጅማና ጎንደር የመሳሰሉ ከተሞችን ጭምር ባሉበት እንዲረግጡ ወይንም ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ ተፈርዶባችዋል። ሌሎች አዲስ አበባን ሊወዳደሩ የሚችሉ ከተሞች ቢኖሩ ኖሮ የአገሪቱ ሀብት ፍታሓዊነትና እኩልነት በተላበሰ መልኩ በሁሉም አቅጣጫ ማሰራጨት ይቻል ነበረ። ይህም አዲስ አበባ ላይ አሁን የተጫነውን የይገባኛልና ልዩ ጥቅም ጋር ተያይዞ የመጣውን ችግር ለማቅለል የራሱ የሆነ ሚና መጫወት በቻለም ነበር።

እዚህ ላይ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ጉዳይ ለምን ጎልቶ እንደወጣ ማብራራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የመጀመሪያው ምክንያት እየቀረበ ካለው የ2012ቱ አገራዊ ምርጫ ጋር ይገናኛል። በሌሎችም አገሮች ሆነ በኢትዮጵያ እንደታየው ሁሉ የምርጫ ውጤት በአብዛኛው የሚወሰነው በከተሞች አካባቢ በሚደመጥና ቀስ በቅስ በሚግል የፖለቲካ ትኩሳት ነው። ይህ እውነታ በከፊልም ቢሆን በ97 ምርጫ ጊዜ ታይቷል። ኢሕአዲግ መሰረቴ የገጠሩ ሕዝብ ነው ቢልም በከተሞች አካባቢ በነበረው የፖለቲካ ጡዘት መወሰዱ አልቀረም። የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ በአንድ ጀምበር ሲዘዋወር አይተናል። በቅርቡ እንኳን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ የከተማ ፖለቲካ ችላ ሊባል እንደማይገባና የዚህን አገር ምርጫ በአብዛኛው የሚወስነው በከተማ ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ መሆኑን ማውሳታቸው ይህንን ሐሳብ የሚደግፍ ይመስለኛል። ይህን ጊዜያዊ እና እንደ የምርጫ ሰሞን ጉዳይ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን።

ነገር ግን ኹለተኛው ምክንያት ብዙ ትኩረት የሚያሻው ነው። ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ሲንከባለል የመጣውና ከአዲስ አበባ ሀብት የፍትሓዊ ክፍፍል ጥያቄ ጋር የተያያዘው በመሆኑ ነው። ይህን ጉዳይ በአግባቡ ለማስረዳት ከሦስት ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቅሰውን የሕዝብ ዐመፅ መነሻ ምክንያት ማጤን ተገቢ ነው። የአዲስ አበባ አስተዳደር አዲሱን የከተማ ዕቅድ ሲያወጣ በኦሮሚያና የአዲስ አበባ አጎራባች ቦታዎች ላይ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅሬታ ማንሳት የጀመሩት ዕቅዱ ተጨማሪ ሰዎችን ከመሬታቸው በማፈናቀል የሀብት ክፍፍሉን ልዩነት የበለጠ ያባብሰዋል በሚል ግንዛቤ ነበረ።

የፍትሓዊ ሀብት ክፍፍል እንደ አንድ ጉልህ ምክንያትነት በስፋት የቃኘኹት ሌሎቹ እንደ ታሪካዊ ሆነ የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ያማከሉ ትርክቶች ቦታ የላቸውም ለማለት አይደለም፤ የአዲስ አበባ ሀብት ምንጭና የዚሁ ሀብት ፍትሓዊ ክፍፍል ጉዳይ እንደሌሎች ትርክቶችሁሉ ተገቢውን ቦታ ማግኘት እንዳለበት ለማሳሰብ ነው።

ሳምሶን ኃይሉ የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት Ethiopian Business Review ምክትል መረሔ አርታኢ ናቸው።

በኢሜል አደራሻቸው ebr.magazine1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here