በአማራ ክልል ጎጃም፣ ደምበጫ ወረዳ ሊገነባ ታስቦ የነበረው የ‹‹ካናቢስ›› ማምረቻ ፋብሪካ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትምንት ቢሮ ፈቃድ አለማግኘቱ ተሰማ። ቢሮው በደብዳቤ እንዳስታወቀው በአገርና በዜጎች ላይ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ጉዳት ሊያደርስ ለሚችል ማምረቻ ድርጅት እንዲገነባ እንደ ክልልም ሆነ ከተማ የተሰጠ ሕጋዊ ፈቃድ የለም።
ማምረቻ ድርጅቱ ከቀናት በፊት በደምበጫ ወረዳ ሊያከናውነው ስላሰበው ካናቢስ የማምረት ሥራ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ማካሔዱ የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ የድርጅቱን እንቅስቃሴ ተከትሎ ባለድርሻ አካላት አቋማቸውን ግልፅ አድርገዋል። የፌደራል ጤና ሚንስትሩ ዶክተር አሚር አማን በትዊተር ገጻቸው ለ‹‹ካናቢስ›› አምራች ድርጅቱ የተሰጠ ፍቃድ እንደሌለና ወደፊትም እንደማይኖር አስታውቀዋል። የሚከለከልበት ምክንያትም ከሕብረተሰቡ ጤናማነት ጋር የሚኖረው አሉታዊ መስተጋብር ታሳቢ ስለሚደረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ማምረቻው በአራት መቶ ሄክታር ማሳ ላይ የሚያርፍና ለአምስት ሺሕ ሰራተኞች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሎ ነበር። ምርቶቹም ሙሉ በሙሉ በከፍተኛ ጥበቃ ወደ ውጭ አገራት ገበያ እንዲላኩ የሚደረግበት አግባብ ታሳቢ መደረጉ ቢነገርለትም በመንግሥት በኩል ተቀባይነት አላገኘም።
ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011