የሱሉልታ ነዋሪዎች መንግሥት ይድረስልን እያሉ ነው

0
711

የሱሉልታ አካባቢ ነዋሪዎች ቤታችሁ በሰባት ቀናት ውስጥ ይፈርሳል መባሉ ስጋት ውስጥ እንደጨመራቸውና ቀጣይ እጣ ፈንታቸውም አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
ቤቱ የሚፈርስበት ምክንያት ለመንገድ ግንባታ ነው ቢባልም እንዲፈርሱ ምልክት የተደረገባቸው ቤቶች እዚህም፣ እዚያም ቤት እየተመረጠ በመሆኑ ለመንገድ የሚለው ምክንያት እንዳላሳመናቸው ገልፃዋል።

በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በኩል መንግሥት እንዲደርስላቸውና ቤታቸው ከመፍረሱ በፊት እንዲታደጋቸው እየተማፀኑ ያሉት ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን ይዘው ወደ ሱሉልታ ከተማ አስተዳደር ቢሔዱም ከንቲባዋ ሊያናግሯቸው አለመፍቀዳቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።

የተመረጡ ቤቶች ለማፍረስ ምልክት ማድረጉ ግለፅ አይደለም በሚል ልዩነቱን ያመጣው ምንድነው? ለሚሉት ነዋሪዎች መልስ የሚሰጥ የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊ አለመገኘቱን በምሬት ገልፀዋል።

የሱሉልታ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ትናንት ረፋድ በፌስ ቡክ ገጹ እንዳስነበበው ከሆነ የከተማ መሬት ወረራን ለማስቆምና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሲባል ህገ ወት ተብለው በሚለዩት ላይ ወደ ቤት ማፍረስ እርምጃ እንደሚገባ አሳውቋል።

‹‹የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር አሁን ላይ በከተማው እየተስፋፋ ያለውን የመሬት ወረራ በማስቆም የሕግ የበላይነትን በማስከበር ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል›› ያለው ጽሕፈት ቤቱ ሕገ ወጥ በተባሉት ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ሕዝቡን የማወያየት ሥራ መከናወኑን አንስቷል።

ነዋሪዎቹ የሚያወያቸውና ለጥያቄያቸው መልስ የሚሰጣቸው አካል እንዳጡ ቢናገሩም ጽሕፈት ቤቱ በበኩሉ ‹‹ሕዝብ ከተወያየ በኋላ የሕገ ወጥ ግንባታ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሕገ ወጥ ግንባታዎችን የመለየት የመጀመሪያ ሥራ ውስጥ ተገብቷል›› ሲል አስተባብሏል።

ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው ግለሰቦች መረጃቸውን እንዲያቀርቡም እየተነገራቸው ስለሆነ ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል። ሊፈርስ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል የሚሉ ነዋሪዎቸ ግን የተለያዩ ማስረጃዎች ቢኖሩንም ተቀባይ አልሆንም ሲሉ ቅሬታ በማሰማት ቤት የማፍረስ ዝግጅቱ አንዱን ከአንዱ የለየና አግላይነት ነውም ሲሉ አክለዋል።

ጽሕፈት ቤቱ በበኩሉ ‹‹ብሔርን ከብሔር የሚለይ ሳይሆን ሁሉንም በሕገ ወጥ ግንባታ ላይ የተሰማራን ሰው ያጠቃልላል›› ሲል ጽፏል።
በተያያዘ የከተማዋ ከንቲባ ለሸገር ራዲዮ ትናንት ሲናገሩ 7 ቀን የሚለው ሰዎች አለን የሚሉትን ማስረጃ እንዲያቀርቡ እንጂ ለማፍረስ አይደለም ያሉ ሲሆን፣ ለመንገድ በሚል የአንዱን ቤት አልፎ ሌላውን መቀባቱ ትክክል አይደለም ይታረማል ብለዋል። አስተዳደሩ ቤቶቹን ለማፍረስ ሳይሆን ሕጋዊዎቹን ለመለየት ያደረገው ተግባርም ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ከዚህ ቀደም በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ ተገንብተዋል የተባሉ መኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ የተደረጉ ሲሆን፤ ይህንም ተከትሎ ነዋሪዎች በተለይም ሴቶችና ህፃናት በአሁኑ ወቅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ሲገልፁ ሰንብተዋል። ከምግብና መጠጥ አቅርቦት እጥረት ባለፈ በተጠለሉበት ድንኳን ሳይቀር ጫና እያደረባቸው ምሆኑንም ይታወቅልን ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን አቤት ብለዋል። የድጋፍ እጥረቱን በተመለከተ የተጠየቀው የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃቹ ተጠልለው የሚገኙት በአዲሰ አበባ አስተዳር ውስት በመሆኑ አይመለከተኝም ብሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here