141 የሞት ፍርደኞች ምሕረት እየጠበቁ ነው

0
883

• የ141 የሞት ፍርደኞች መረጃ ተደራጅቶ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቀርቧል

በኢትዮጵያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 141 ታራሚዎች ምሕረት እንዲደረግላቸው ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቤት አሉ።

ከሞት ፍርደኞቹ ውስጥ 137ቱ ወንዶች ሲሆኑ፣ ቀሪ አራቱ ሴቶች ናቸው። አዲስ ማለዳ መረጃ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው የሞት ፍርዱ ምሕረት ይደረግላቸው ዘንድ የጠየቁት 141 ፍርደኞች መረጃ ተደራጅቶ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀረበ ሲሆን፣ ምህረቱን በመጠባበቅ ላይ ናው። የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው አሁን ላይ ምሕረትን ከሚጠባበቁት መካከልም ከ20 ዓመታት በላይ በእስር ላይ የሚገኙ እንዳሉበት ታውቋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገረመው አያሌው፣ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው የ141 ታራሚዎች መረጃ ለዐቃቤ ሕግ መላኩን አረጋግጠዋል። ዐቀቤ ሕግም መረጃውን ከመረመረ በኋላ አዲስ ለተዋቀረው የይቅርታና አመክሮ ኮሚቴ እንደሚልከው የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ምሕረት የመስጠቱን ተግባር ማከናወን የኮሚቴ ድርሻ ስለመሆኑም አክለዋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቱ ተጠሪነት ለፌደራል ዐቃቤ ሕግ መሆኑን የተናገሩት ገረመው፣ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የታሰሩ ታራሚዎች ለውጥ ካመጡ አመክሮ እንደሚታይላቸው ጠቁመዋል። ለዚህም የይቅርታና አመክሮ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስለሆነ፣ ጉዳዩን አጥንቶና መርምሮ ለኮሚቴው አባላት ያቀርባል ሲሉም የአሰራር ሒደቱን አስረድተዋል።

ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በቆየባቸው 28 ዓመታት የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው ፍርዱ ተፈፃሚ የሆነባቸው ኹለት ሰዎች ስለመኖራቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በተጨማሪም፣ በተለያየ ወንጀል የተፈረደባቸው ታራሚዎች ይቅርታ እንዲፈቀድላቸው እና ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ ለሚመለከተው አካል እንዲቀርብላቸው የጠየቁ 276 ታራሚዎች እና ተከሳሾች መኖራቸውን ኃላፊው አክለዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤት አስተዳደርም የእነዚህን ቅሬታ በማጣራት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያስተላለፈ ሲሆን፣ ለ65 ታራሚዎች እና ተከሳሾች ምላሽ መሰጠቱን ገረመው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከስድስት ወር እስከ ሦስት ዓመት በቀጠሮ ላይ የሚገኙ አንድ ሺሕ 49 ወንድ እና 72 ሴቶች በድምሩ አንድ ሺሕ 121 በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ወገኖችን በመለየት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ለፌደራል ጠቅላይ፣ ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በማቅረብ እየታየ ነው። ገረመው ‹‹በዚህም ተከማችቶ የነበረውን የፍትሕ መጓተት ችግር በቅንጅት በመሥራት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል›› ብለዋል።

የሕግ ታራሚዎችን በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የማረምና የማነጽ አገልግሎት በመስጠት፣ የተረጋጋ የእርምት ጊዜ እንዲኖራቸው ለማድረግና የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት፣ የባህሪይና የስብዕና ለውጥ በማምጣት ለመታረምና ለመታነጽ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግን የሚያልመው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በበቂ ዕውቀት፣ ልምድና ከታራሚው ቁጥር ጋር በሚመጣጠን ደረጃ የማረምና ማነጽ ሥራን የሚከውን ባለሙያ ባለመኖሩ እየተቸገረ መሆኑም ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here