የኢሕአዴግ መዋሐድ ለዴሞክራሲ

0
802

ኢሕአዴግ እስካሁን አራት ክልሎችን እንወክላለን የሚሉ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት ነበር። ይሁንና አሁን በመዋሐድ ሁሉን ዐቀፍ ፓርቲ ለመሆን እየሠራ ነው። በኢሕአዴግ ነባር የፖለቲካ ፍልስፍና የኢትዮጵያ ችግር የብሔር እና መደብ ድርብ ጭቆና ነው ተብሎ ስለሚታመን በብሔር መደራጀት ያልተጻፈ ሥምምነት ነበር። ይሁንና አሁን ውሕደቱ ሲፈፀም፥ ግንባሩ ከዚህ ፍልስፍና ጋር ፍቺ እንዲፈፅም ያስገድደዋል። ለመሆኑ ውሕደት ኢሕአዴግን የማንነት ፖለቲካ እንዳይጫወት ያግደዋል? የማንነት ፖለቲካ መጫወት/አለመጫወቱስ ለዴሞክራሲ እንቅፋት ይሆናል?

ዕውቁ የሶስዮሎጂ ምሁር ፍራንሲስ ፉኩያማ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብዙ ያነጋገረ መጽሐፋቸውን ስለማንነት ፖለቲካ ጽፈዋል። በመጽሐፋቸው የማንነት ፖለቲካን በሦስት ደረጃዎች አስቀምጠውታል። የመጀመሪያው የማንነት ጥያቄ “ዕውቅና” ማግኘት ነው፤ እንደ ቡድን ዕውቅና ይሰጠን በሚል የሚደረግ። ቀጣዩ ደረጃ “እኩል ዕውቅና” ማግኘት ነው። በሦስተኛ ደረጃ “የበላይነት ዕውቅና” ማግኘት ይሆናል።

ፉኩያማ ያነሱት የማንነት ፖለቲካ ሒደት ላይ ተንተርሰን የራሳችንን ትንታኔ ስናስቀምጥ፣ ይህ የማያቋርጥ የማንነት ፖለቲካ ጥያቄ በብሔርተኝነት ሲታገዝ የበላይነት ዕውቅና ይሰጠን ባዮች እንደሚበዙ ለመገመት አያዳግትም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዘውግ ብሔርተኝነትን ተቋማዊ ያደረገ በመሆኑ ለዚህ የበለጠ ተጋላጭ ነው።
ኢሕአዴግ መዋሐዱ የብሔርተኝነት ተቋማዊነትን ቢያንስ በፓርቲው ደረጃ ስለሚወስነው፣ የማንነት ፖለቲካው በእኩል ዕውቅና ማግኘት ጥያቄ ሊገደብ ይችላል።

ይህም ለዴሞክራሲ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ነገር ግን የኢሕአዴግ መዋሐድ ለዴሞክራሲያዊነት የሚያቀርበው ሌላም ትልቅ ሥጦታ አለ።

በኢሕአዴግ ግንባር ውስጥ አራት ክልሎች ብቻ በመወከላቸው የዴሞክራሲ ዋነኛ መርሕ ተጥሶ ከርሟል። ይኸውም ዴሞክራሲ ለማንኛውም ዜጋ ትልቁ የመንግሥት ኃላፊነትን ለመውሰድ መንገዱን (የሕዝብ ይሁንታን በምርጫ ማግኘት እስከቻሉ ድረስ) ክፍት ማድረግ መቻሉ ነው። በኢሕአዴግ አሠራር ግን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታው በአባል ድርጅቶቹ ብቻ የሚወሰን እንጂ አጋር ድርጅቶች እንኳን የመመረጥ ዕድል እንደሌላቸው ይታወቃል።

ኢሕአዴግ ሲዋሐድ ቢያንስ በውስጠ ፓርቲ መርሕ ደረጃ ከየትኛውም ክልል ውስጥ ለትልቁ የመንግሥት ሥልጣን መታጨት የሚችሉ ዜጎች ሊወጡ ይችላሉ። ከዚህ በፊት የነበረው አሠራር ኢ-ዴሞክራሲያዊ እና ከሰብኣዊ መብቶች አንፃርም ቢሆን አግላይ የነበረ ገዢውን ፓርቲ በትልቅ ቅሌት ሊያስወቅሰው የሚገባ ነገር ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here