የሆቴል ዘርፍ ላይ ያተኮረ ጥናት በ590 ሺሕ ብር እየተካሔደ ነው

0
491

የኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሆቴል ኢንዱስትሪው የሰው ኃይል ዘርፍ ላይ ያተኮረን ጥናት በ590 ሺሕ እያካሄደ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አስቴር ኃይለ ገብርኤል እንደገነገሩን የ50ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን መሰረት አድርገው ከሚከወኑ መርሀ ግብሮች አንዱ ጥናት ማካሔድ ነው።

በመሆኑም የኢንስቲትዩቱ ተማሪዎች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው፣ በሆቴል ዘርፍ የሠለጠኑ ባለሙያዎችስ ምን ያህል በዘርፉ ተሠማርተዋል የሚለው ጉዳይ ጥናት ይደረግበታል።

የሰው ኃይል ጥናቱ ዋነኛ የቦታ ትኩረት ባለ ኮከብ ሆቴሎች በሚበዙባት አዲስ አበባ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉትም ቦታው ድረስ እየተኬደ የጥናቱ ናሙና እንደሚሆኑ ተነግሯል።

ለሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ሲሰራ አንዱ መስፈርት የቀጠራቸው ሰዎች ምን ያክል በዘርፉ የሠለጠኑ ናቸው የሚለውን የሚጠይቀ መሆኑ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም የኮከብ ደረጃ ምደባ ሊሰጥ ነው ሲባል ሆቴሎች እርስ በእርሳቸው የሰለጠኑ ሰዎችን የመዋዋስ ተግባር ውስጥ እንደሚገቡ የጠቆሙት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ሆቴሎች የውጭ ዜጎችም ጭምር የሚስተናገዱባቸው በመሆኑ ሁሉንም ሊያስተናድ የሚችል ብቁ ባለሙያ እንደሚያስፈልጋቸው ያነሳሉ። ይሁንና ሆቴሎች ከሰለጠነ ሰው ይልቅ የራሳቸውን የቅርብ ሰው በመቅጠር እንደሚታሙም ይነሳል።

በተያያዘ የ50ኛ ዓመት ምስረታ በዓሉ ጥናት የደቡብ ኦሞ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት የሚለካ ጥናትም ያደርጋል ተብሏል።
እነዚህን ጉዳዮች ይዳስሳል የተባለው ጥናቱ ከወር በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ በመጪው ግንቦት ይጠናቀቃል ተብሏል። ሙሉ ወጪውም በኢንስቲትዩቱ ይሸፈናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here