እነ በረከት ስምዖን ደርሶብናል ያሉትን የመብት ጥሰት የክልሉ ፖሊስ እንዲከታተል ታዘዘ

0
700

በጥረት ኮርፖሬት ላይ ሙስና ተፈጽሟል በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉት በረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ ጉዳያቸውን ለመከታተል የባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የመብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው መሆኑን ለአንደኛ ወንጀል ችሎት አስረድተዋል።

በረከት ለችሎቱ ሲናገሩ መጋቢት 2 እና 3/2011 ጠበቃ ቢያቀርቡም በጠበቆቹ ላይ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

‹‹የአማራ ክልል ሕዝብ ታላቅ ነው፣ ሕግ አዋቂና የተከበረ ኩሩ ሕዝብ ነው፤ ነገር ግን ይህን እያደረጉ ያሉት ሆን ተብሎ የተሰማሩ ጉልበተኞች ናቸው›› ሲሉ መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በመደበኛ ችሎት ጭምር ሲወጡና ሲገቡ ክብረ ነክ ስድብ እየደረሰባቸው በመሆኑ ችሎቱ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲያስጠብቅላቸውም ጠይቀዋል።

አቤቱታውን ያዳመጠው ችሎቱ ድርጊቱ አግባብ አለመሆኑን አሳውቆ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ተከታትሎ እርምጃና ማስተካከያ እንዲወስድ አዟል።

በተያያዘ የመርመራ ቡድኑ ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው መጠየቁን ተከትሎ ተጠርጣሪዎቹ ተደጋጋሚ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው መሆኑን ጠቅሰው ተቃውመዋል።
ታደሰ ካሳ ‹‹እኛን የከሰሰን የክልሉ ከፍተኛ አመራር በመሆኑ ምርመራው ሆን ተብሎ በማጓተት እስር ቤት እንድንቆይ አላማ ተደርጎ እየተሰራ ነው›› ብለዋል። ቡድኑ በበኩሉ የዳሽን ቢራ አክሲዮን የሽያጭ ጉዳይና የኦዲት ሥራን ለማጣራት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አመልክቷል።

ችሎቱ በበኩሉ ተደጋጋሚ ቀጠሮ የሚሰጠው ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠትና ጉዳዩን በሚገባ ለማጣራት እንዲያመች ነው ብሏል። በዚህም የስምንት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመፍቀድ መጋቢት 20 ከሰዓት በኋላ የኦዲት ሥራው ተጠናቆ እንዲቀርብ አዟል።

ችሎቱ በመጋቢት 02 ውሎው ከዳሽን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ሽያጭ ጋር በተያያዘ ያላለቁ መረጃዎችን አሰባስቦ መርማሪ ቡድኑ እንዲያጠናቅቅ የስምንት ቀን ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here