ሚፍታህን እንደማሳያ የአዲስ አበባን የጎዳና ላይ ንግድ

0
577

ዕለቱ ሰኞ፣ መጋቢት 9 አስራ አንድ ሰዓት፥ ቦታው በተለምዶ ʻቦሌ ድልድይʼ ወይም ብራስ በመባል የሚታወቀው አካባቢ ነው። ሰርክ እሁድን ብቻ ሳይጨምር ቦታው ጠዋትና ከሰዓት በኋለ በተለይ ከ10 ሰዓት ጀምሮ ከሥራ በሚወጡ ሰዎች፣ በተማሪዎችና በተላላፊ መንገደኞች ይጨናነቃል። የጎዳና ላይ ʻነጋዴዎችምʼ ለመንገዱ መጨናነቅ የራሳቸውን ጡብ ከሚያኖሩት መካከል ይመደባሉ።

የጎዳና ላይ ንግድ የሚያካሒዱት አብዛኞቹ ሰማያዊ በነጭ የሆነ ዝርግ ፕላሲቲክ ውስጥ አልባሳት፣ ካልሲዎች፣ ፎጣዎች፣ አንሶላ፣ ጫማ፣ መመገቢያ ሳህኖች፣ ምሳቃ፣ ማንኪየዎች፣ የሻይ ቅመሞች፣ የሞባይል ማዳመጫ ገመዶች፣ ʻሜሞሪዎችʼ ወዘተ ይዘው በአንድ ወገን ገዢ ፍላጋ በሌላ ወገን ደግሞ ደንብ አስከባሪዎችን በዓይነ ቁራኛ ይከታተላሉ።

̋ላለው በቅናሽ፥ ለሌለው በዱቤ˝ ይላል የ26 ዓመቱ ወጣት ሚፍታህ ሙኸዲን ጎላ ባለ ድምፅ፤ እንኳን ለመሸመት የወጣውን መንገደኛውን ቀልብ በሚገዛ ድምጽ። መንገድ ዳር ዘርግቶ የሚሸጠውን የሴቶች ጫማ በግማሽ ልብ እየተከታተለ ቀሪውን አትኩሮቱን ፖሊስ ወይም ደንብ አስከባሪ ʻመጣ አልመጣʼ በሚል ግራ ቀኝ እየተገላመጠ።

በኻያ ዓመቱ ነበር በታላቅ ወንድሙ ጥሪ ተወልዶ ካደገበት ጉራጌ ዞን፣ እነሞር ወረዳ ወደ አዲስ አበባ የመጣው። ታዲያ አዲስ አበባ ለሚፍታህ ገጠር ሆኖ እንደሳላት ጥሩ እየተለበሰ፣ ጥሩ እየተበላ የሚኖርባት ከʻጀነትʼ የምትጠጋጋ የሐሴት ምድር አልሆነችለትም። ˝ወደ አዲስ አበባ እንደመጣሁ ከሳምንት በኋላ ነው ሥራ የጀመርኩት˝ ይላል ሚፍታህ ።

ከወንድሙ ሱቅ በዱቤ የሚረከባቸውን የመኪና ጌጣ ጌጦችን በየመንገዱ እያዞረ ሲሸጥ ነው ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ጋር የተዋወቀው። ˝ሥራውን እንደጀመርኩ ውሃ ጥም በጣም ያስቸግረኝ ነበር ̋ የሚለው ሚፍታህ ኹለት ጊዜ በሥራ ላይ እያለ በመኪና ከመገጨት እንደተረፈም ፈጣሪውን እያመሰገነ ይናገራል።

ሚፍታህ እረፍት የለውም። እኔን እያናገረ ሐሳቡ ከአሁን አሁን ፖሊስ መጥቶ ዕቃዬን ይወስድብኝ ይሆን በሚል ፍራቻ ግራ ቀኝ ያማትራል። ለሚፍታህ ሥራ ክቡር ነው፤ ነገር ግን የሚሠራው ሥራ ሕጋዊ አይደለም። የመኪና ጌጣጌጦችን እያዞረ መሸጥ አቁሞ ወደ መንገድ ዳር የሴቶች ጫማ ሽያጭ ከገባ ኹለት ዓመት ተኩል ሆኖታል። አሁን አሁን ሥራው እየቀዘቀዘ እንደሔደ የሚናገረው ሚፍታህ ከኹለት ዓመት በፊት ወደ ሥራው ሲገባ በቀን ደህና ገቢ ያገኝ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዕቃ የሚያመጣበት ቦታ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው ገቢው እንደ ድሮው አይደለም።

ከመገናኛ እስከ አራት ኪሎ፣ ከ22 እስከ ቦሌ፣ ከስታዲየም እስከ ሜክሲኮ ሚፍታህ ሸቀጦቹን ዘርግቶ ከፖሊስና ከደንብ አስከባሪ ጋር እየተሯሯጠ ያልሠራባቸው የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የሉም። የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ለሚፍታህ የዕለት ጉርሱን የሚሰጡት፣ በየቀኑ የሚጥለውን ዕቁቡን የሚሸፍኑለት፣ ገጠር ያሉ ዘመዶቹን እንዲረዳ የሚያስችሉት የገቢ ምንጮቹ ናቸው። ̋ቁጥጥሩ ጠንከር ሲል አካባቢ እንቀይራለን˝ የሚለው ይህ ወጣት፤ በርካታ ሸማች ያለባቸውን አካባቢዎች ላለመልቀቅ ብርቱ ጥረት እንደሚያደርጉ እና አንዳንዴም ገንዘብ አሰባስበው ለተቆጣጣሪዎች በመስጠት ለጥቂት ቀናትም ቢሆን እፎይ እንደሚሉ ሚፍታህ አጫውቶኛል። ሚፍታህ ሥራ ከጀመረ ጀምሮ አብዛኛውን ጊዜ የሠራው መገናኛ አካባቢ ቢሆንም አሁን ግን ቦሌ ተመራጭ መዳረሻው ሆኗል።

ቦሌ ብራስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደ ቦሌ መድኀኔዓለም የሚወስደውን መንገድ ግራና ቀኝ በመያዝ የእግረኛ መንገድ ላይ በብዛት የሚከወነው የጎዳና ላይ ንግድ፤ አዲስ አበባ ውስጥ ከተጧጧፈባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በዚህ ጎዳና ላይ ታዲያ በርካታ ዓይነት ዕቃዎች ለሽያጭ ይቀርባሉ፤ ገዢም ያሻውን ያነሳል፣ ዋጋ ይከራከራል ከተስማማ ይገዛል ካልሆነ ይፋረሳል። ሚፍታህ ታዲያ በዚህ አካባቢ ከሚከወነው የጎዳና ንግድ ላይ ቀዳሚ ተሰላፊ ነው ። ሕጋዊ ሱቅ ከፍተው የሚሰሩ ግለሰቦችም ፀሐይ ዘቅዘቅ ማለት በምትጀማምርበት ጊዜ ሱቅ የሚሸጡትን ይዘው ጎዳና ላይ ለመሸጥ እንደሚወጡ የጎዳና ʻነጋዴዎችʼ ለአዲስ ማለዳ ሹክ ብለዋታል።

ሰዓቱ ደንገዝገዝ ማለት ሲጀምር ሚፍታህ ከዋለበት ውሎ ወደዚህ ሥፍራ ሸቀጡን ሸክፎ ብቅ ይላል፤ ከዛም በጆሮ ገብ ድምጹ ̋ላለው በቅናሽ፥ ለሌለው በዱቤ ̋ ሲል ይጀምራል የወጪ ወራጁን ቀልብ ለመግዛት። ና እልፍ ሲልም ። የሚፍታህንም ሆነ የመሰሎቹን የግዙኝ ማስታወቂያ ለመሸመት አቅደው የሚንቀሳቀሱትንም ሆነ ድንገቴ አላፊ አግዳማዎቹን በማማለል ኪሳቸውን በመፈታተሽ ወደ ግብይቱ ጎራ እንዲሉ ያደርጋል፤ ግብይቱም ይደምቃል፣ ይጋጋላል።

ነገር ግን ይህ አጭር፣ ሰላማዊ ትዕይንት ብዙም ሳይቆይ ድንገት መልኩን ይለውጥና ወደ ግርግር ይቀየራል። በዚህ ሰዓት እርግጠኛ መሆን የሚቻለው በአካባቢው ፖሊስ ወይም ደንብ አስከባሪ ታይቷል ማለት ነው። በግብይቱ ወቅት ይዘውት የነበረውን ዕቃ አንድ እግር ጫማ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ቦርሳ ወይም ቀሚስ ብቻ ምንም ሊሆን ይችላል ነጋዴው እሱን ለመቀበል ጊዜ አይኖረውም ቀሪ ዕቃዎቹን ሸክፎ እግሬ አውጪኝ ይላል። ምክንያቱም ሕጋዊ አይደሉም፣ ከተያዙ የሚወሰድባቸው እርምጃው ዕቃውን እስከመውረስ ስለሚደርስ መሸሽ ዓይነተኛ መፍትሔ ነው፤ ባይሆን ግርግሩ ከተረጋጋ በኋላ ዕቃዎቻቸውን ፍለጋ ይመለሳሉ።

ከፖሊስ እና ደንብ አስከባሪዎች በሚደረገው ሽሽት በመኪና እስከመገጨት የሚደርሱት የጎዳና ላይ ነጋዴዎች፤ ሲያዙ በልመና እንዲለቋቸው ይማጸናሉ ከፍ ሲል ደግሞ የገንዘብ ድርድር ይደረጋል ከዚህ ባስ ሲል ግን ወደ ቡጢ የሚገባባቸው አጋጣሚዎችም አሉ። ቦታው በውል ባይታወቅም የሰው ነብስ የጠፋበት አጋጣሚም እንዳለ ለመስማት ችያለሁ።

̋አንድ ጊዜ የምሸጠውን ዕቃ ይዘውብኝ፥ ብዙ ብር ከፍዬ በድርድር ነው የተለቀቀልኝ ̋ የሚለው ሚፍታህ ከዛ ቀን በኋላ ላለመያዝ የሚያደርገው ጥረት ክፍተኛ እንደሆነ ይናገራል። ሚፍታህ ̋አሁን ግን በጣም እየሰለቸኝ ነው ወደ ሕጋዊ መስመር ብገባ ነው የምመርጠው ̋ ይላል ʻሌባና ፖሊስʼ መጫወቱ ባታከተው ድምጸት። በቅርቡ የሚጠብቀው ዕቁብ አለ ፤ እሱ እጁ ላይ እንደገባ የመጀመሪያ ሥራው የሚሆነው ወደ መርካቶ ጠጋ ብሎ ሱቅ መክፈት ነው። ይሁን እንጂ በተመሳሳይ ሰዓት መፈፀም ያለበት ነገር አለ። አገር ቤት ወላጆቹ ትዳር እንዲይዝ በማሰብ ሚስት አጭተውለታል፤ ማግባት ይኖርበታል ማለት ነው። ለዚህም ሚፍታህ ገንዘብ ያስፈልገዋል። እንዴት ኹለቱንም ነገሮች ማስኬድ እንዳለበት ግን ግራ የተጋባ ይመስላል።

ሚፍታህን አድንቄዋለሁ፤ ʻደንበኛʼ የሚላቸውን አልፎ ሒያጅ ገበያተኞቹን እያስተናገደ፣ በሌላ በኩል ፖሊስ ወይም ደንብ አስከባሪ እየተከታተለ፣ ዕቃዎቹን ዓይን ከማያሰናዝሩት ቀማኞች እየጠበቀ የምጠይቀውን ከበቂ ማብራሪያ ጋር እየመለሰልኝ ነው። የሥራ መውጫ ሰዓት መሆኑ ደግሞ ሥራውን ይበልጥ በወከባ የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል።

ከዚህ በላይ ትኩረቱን እና ጊዜውን ልሻማበት አልፈለኩም፤ ለነገሩ እሱም ትንሽ ብቆይ የሚታገሰኝ አይመስልም። ሥራው እየበዛባት፣ ግብይቱ እየተሟሟቀ ነው። ከምስጋና ጋር ተሰናበትኩት በዚህ ጊዜ ግን ፈገግ የሚያደርግ ጥያቄ ጠየቀኝ ̋ሲቪል ፖሊስ አይደለህም አይደል? ̋ የሚል፤ ፈገግታዬ ነገረው መሰለኝ በተዝናና መልኩ ተሰነባበትን – እሱም ቀልቡን ሰብስቦ ወደ ንግዱ ሲመለስ እኔም በበኩሌ ወደ ጉዳዬ በዝግታ አዘገምኩ።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here