ከ2002 እስከ 2008 በጀት ድረስ የተሰጡ የኦዲት አስተያየቶችን ያላስተካከሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ከአዲሱ በጀት ዓመት በፊት የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ማሳሰቢያ ተሰጠ።
ማሳሰቢያው የተሰጠው መጋቢት 16 በኦዲት ጉድለቶችና እርምጃዎች ላይ የምክክር መድረክ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሔደበት እለት ነው። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የውይይቱ ዓላማ የኦዲት ግኝቶቹን ያላስተካከሉ የመንግሥት ኃላፊዎችን ለሕግ በቀጥታ ከማቅረብ በፊት ወደእርምት እርምጃ እንዲገቡ ለማሳሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለመንግሥት እንዲመለስ የኦዲት አስተያየት የቀረበበት የገንዘብ መጠን ብር 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን መሆኑን አስታውሰው ገንዘቡን ለማስመለስ ባለው የቁርጠኝነት ማነስ እስከ አሁን ድረስ የተመለሰው ገንዘብ 50 ሚሊዮኑ መሆኑን አሳውቀዋል።
የኦዲት ግኝቶችን የማያስተካክል ኃላፊ ከ10 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ የዋና ኦዲተር ማቋቋሚያ አዋጅ የሚደነግግ ቢሆን እስካሁን አለመተግበሩን ገመቹ ተናግረዋል።
እንደምክርቤቱ መረጃ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ 15 የፌዴራል ተቋማትን በ408 ሚሊዮን ብርና 20 ዩኒቨርሲቲዎችን በ692 ሚሊዮን ብር ጉድለት ለይቶ ለምርመራ ሥራ የሚያግዝ ጭብጥ መለየቱን፣ የምርመራ መዝግብ ማደራጀቱንና ለተቋማት የሚላኩ ደብዳቤዎች መዘጋጀታቸውን አሳውቋል።
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የኦዲት ግኝቱን ለመተግበር መሥሪያ ቤቶች የሚያቅማሙት ምክር ቤቱ እርምጃ ስለማወስድ ነው ሲል አቋሙን አገልጿል።
ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011