ምክር ቤቱ በጋምቤላ 36 የእርሻ ፕሮጀክቶች ጠፉ አለ

0
516

በጋምቤላ ክልል ከ654 ሚሊዮን ብር በላይ የብንክ ብድር ያለባቸው 36 የእርሻ ፕሮጀክቶች መጥፋታቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ።
የግብርናው ዘርፍ መንግሥት ትኩረት በማግኘቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ዓመታት የመንግሥትን የልማት አቅጣጫ ትኩረት በመከተል በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎች ብድር ሲሰጥ ኖሯል።

ባንኩ ከአውሮፓዊያኑ 2010 ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ለ189 በዝናብ የሚለሙ የእርሻ ፕሮጀክቶች ማቋቋሚያና ማልሚያ የሚሆን የረጅም ጊዜ ብድር ሦስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር መፍቀዱንም የምክር ቤቱ የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳውቋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ፕሮጀክቶች ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች ያሉበትን ሁኔታ የመስክ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን ብድርና መሬት ወስደው ሥራ ያልሰሩ እንዲሁም ብድር ሳይወስዱ ሥራ የሰሩ ፕሮጀክቶችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ቡድኑ በጋምቤላ ወረዳ የሚገኙ 6 ሳይቶችን ሲመለከት ኹለቱ በትክክል ሲሰሩ ቀሪዎቹ ግን ሥራቸውን በትክክል ያልሰሩ ናቸው ተብሏል።

በቡድኑ ምልከታው ጥሩ እየሰሩ ያሉ 20 ፕሮጀክቶች ሲኖሩ 323 ሚሊዮን ብር ብድር እንዳለባቸው አረጋግጧል። 133ቱ ደግሞ ሥራ ላይ ቢሆኑም የተለያየ ድክመትና ኹለት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብድር እንዳለባቸው ታውቋል።

እርሻቸውን ጥለው ጠፉ የተባሉት 36 የእርሻ ዘርፍ ፕሮጀክቶችም የሚፈለግባቸው 654 ሚሊዮን 320 ሺሕ 44 ብር ብድር አለባቸው ነው የተባለው።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድር ሁኔታ ትንተና 117 ፕሮጀክቶች የብድር አመላለስ ሁኔታቸው አጠራጣሪ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን 2.5 ቢሊዮን ብር ብድር አለባቸው። ብዛታቸው 44 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ደግሞ በኪሳራ ላይ ይገኛሉ፣ የተበደሩትም 902 ሚሊዮን ብር በላይ ነው ተብሏል።

የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር ኡጁሉ ኦኬሎ በበኩላው በብድር መልክ የተሰጠው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል ገንዘቡን የወሰዱት ሰዎች በሪል ሰቴትና በሆቴል ግንባታ ላይ እንደተሰማሩ ተናግረዋል።

ባለሀብቶች መሬቱን ከተረከቡ በኋላ የምንጣሮ ሥራ ሰርተው ጥለው እየጠፉ መሆናቸው መሬቱ ጦሙን እንዲያድርና ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ እንዲከተል ማድረጉን በዚህም ነዋሪዎች ቅሬታ እንዳለባቸው የክልሉ አመራሮች ለኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here